የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በ2015 ዓ.ም. የበጀት ዓመት በደቡብ፣ በደቡብ ምዕራብ እና በሲዳማ ክልሎች በሚገኙ 75 ፖሊስ ጣቢያዎች እና 21 ማረሚያ ቤቶች የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ዙሪያ ባደረገው ክትትል ግኝቶች ላይ ሰኔ 23፣ 24 እና 26 ቀን 2015 ዓ.ም. ከባለድርሻ አካላት ጋር በሻሸመኔ እና በቦንጋ ከተሞች የውይይት መድረኮች አካሂዷል፡፡

በውይይት መድረኮቹ የሦስቱ ክልሎች የፖሊስ ኮሚሽን፣ የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ኮሚሽን፣ የፍትሕ ቢሮ፤ ተገቢነት ያላቸው የምክር ቤት አባላት እና ክትትል የተደረገባቸው ተቋማት ተወካዮች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

ክትትል በተደረገባቸው ፖሊስ ጣቢያዎች ከተለዩ አወንታዊ መሻሻሎች መካከል አብዛኞቹ ተጠርጣሪዎች በሕግ አግባብ በወንጀል ተጠርጥረው እንዲሁም ክስ ቀርቦባቸው በቁጥጥር ሥር የዋሉ መሆናቸው፤  በቁጥጥር ሥር ሲውሉ መረጃቸው በተገቢው መንገድ መሰነዱ፤ በቁጥጥር ሥር ሲውሉ እንዲሁም በምርመራ ወቅት አካላዊም ሆነ ሥነ-ልቦናዊ ጥቃቶች የማይደርሱባቸው መሆኑ፤ በቤተሰቦቻቸው፣ በሃይማኖት አባቶች፣ በሐኪሞች እና በሕግ አማካሪዎቻቸው በፈለጉት ቀናት ያለገደብ እንዲጎበኙ መፈቀዱ፤ ለሴት ተጠርጣሪዎች ከወንዶች የተለየ የማቆያ/ማደሪያ ክፍሎች መዘጋጀታቸው እና በፍርድ ቤት የሚሰጡ ትእዛዞች እና ውሳኔዎች በፖሊስ ኀላፊዎች መከበራቸው የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

በተመሳሳይ ኢሰመኮ በሦስቱ ክልሎች በ21 ማረሚያ ቤቶች በታራሚዎች የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ዙሪያ ባደረገው ክትትል የታራሚዎችን መረጃ በኮምፒውተር ለማደራጀት ጅምሮች መኖራቸው፤ ታራሚዎች ወደ ማረሚያ ቤቶች ሲገቡ መብቶቻቸውን እና ግዴታዎቻቸውን እንዲያውቁ መደረጉ በመልካም አፈጻጸም የተጠቀሱ ናቸው። በታራሚዎች ላይ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በፈጸሙ የማረሚያ ቤት ፖሊስ አባላቶች ላይ የሕግ እና የዲስፕሊን እርምጃዎች መወሰዳቸው፤ ታራሚዎች የቀለም እና የሙያ ስልጠና እንዲያገኙ እንዲሁም ገቢ በሚያስገኙ ሥራዎች እንዲሳተፉ መደረጉ ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም ኮሚሽኑ በ2014 ዓ.ም. ባከናወናቸው የማረሚያ ቤቶች ክትትል ግኝቶች መሠረት የተሰጡ ምክረ ሐሳቦችን ለመተግበር ጥረቶች መደረጋቸው በአወንታዊነት ከተጠቀሱት ግኝቶች መካከል ይገኛል፡፡

በሌላ በኩል ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር በዋሉ በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት ያለማቅረብ፤ በፖሊስ ጣቢያዎች የምግብ፣ የፍራሽ እና የአልባሳት አቅርቦት ያለመኖር፤ የተጠርጣሪዎች የማደሪያ ክፍሎች በእስረኞች የተጨናነቁ፣ በቂ አየር እና ብርሃን የማያስገቡ እንዲሁም ተባይ ያለባቸው መሆናቸው እና ተጠርጣሪዎች ቅሬታ የሚያቀርቡበት ይፋዊ የአሠራር ሥርዓት አለመኖሩ በፖሊስ ጣቢያዎቹ ከተለዩ ችግሮች መካከል ይገኙበታል፡፡

በማረሚያ ቤቶች ለአንድ ታራሚ የሚመደበው የምግብ በጀት የወቅቱ የገበያ ሁኔታን ያላገናዘበ መሆኑና በቂ ምግብ ለማቅረብ አለማስቻሉ፤ በማረሚያ ቤቶች ከፍተኛ የታራሚ ክፍሎች ጥበትና የንጽሕና ጉድለቶች መስተዋሉ፤ የመኝታ አልጋ እና የፍራሽ አቅርቦቶች ላይ ከፍተኛ እጥረት መኖሩ ተገልጿል፡፡ ታራሚዎችን በፈርጁ ለይቶ ለማቆየት የሚያስችል የማረሚያ ተቋማት አደረጃጃት ያለመኖሩ፤ በማረሚያ ቤቶች የሚገኙ የሕክምና መስጫ ተቋማት የላቦራቶሪ መሣሪያዎች እና የመድኃኒቶች እጥረት መኖሩ፤ የተደራጀ እና ወጥ የሆነ የቅሬታ ማቅረቢያ ሥርዓት አለመዘርጋት፤ ወጥ የሆነ የይቅርታ አሰጣጥ የሕግ ማዕቀፍ በሀገሪቷ ያለመኖሩ ክፍተት የፈጠረ መሆኑ እና ልዩ ድጋፍ ለሚሹ ታራሚዎች በቂ ድጋፍ አለመኖሩ ተነግሯል፡፡  እንዲሁም በይርጋለም ማረሚያ ተቋም ከማደሪያ ክፍል ጥበት፤ ከንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እና ንጽህና ጉድለት ከ2014 ዓ.ም. ጀምሮ በተከሰቱ በሽታዎች ታራሚዎች ለከፍተኛ ህመም እና ሞት መዳረጋቸው ተጠቁሟል፡፡

ተሳታፊዎች የክትትል ግኝቶቹ የፖሊስ ጣቢያዎቹንና የማረሚያ ቤቶቹን ነባራዊ ሁኔታ የሚያሳዩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የተጠርጣሪዎች እና የታራሚዎች ማደሪያ ክፍሎች ደረጃቸውን ያልጠበቁ መሆናቸው እና የምግብ፣ የፍራሽ እና የአልባሳት አቅርቦት ያለመኖሩ በቀጥታ ከበጀት ጋር የሚገናኝ መሆኑን እና  እነዚህን  ችግሮች ለመቅረፍ የሚመለከታቸው የክልል መንግሥታት ተገቢ ድጋፍ እንዲያደርጉ እና የተጀመሩት ጥረቶች አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራ ሥራ ክፍል ከፍተኛ ዳይሬክተር ዶ/ር ሚዛኔ አባተ በፖሊስ ጣቢያዎች እና ማረሚያ ቤቶች ያሉ ክፍተቶችን ማረም ዋነኛ ኃላፊነት የመንግሥት መሆኑን ገልጸው በማረሚያ ቤቶች የሚስተዋሉ ችግሮች መነሻዎቻቸው ለማረሚያ ተቋማት የሚመደብ በጀት በቂ አለመሆን፤ በባለድርሻ ተቋማት መካከል ደካማ የቅንጅት ሥራዎች መኖራቸው፤ ወጥ የሆነ የታራሚዎች አያያዝ እና አጠባበቅ ሕግ ያለመኖሩ እና ከጊዜው ጋር ያልዘመኑ የሕግ ማዕቀፎች መሆናቸውን ጠቅሰው በማረሚያ ቤቶች የሚስተዋሉ የታራሚዎች መጨናነቅን ለመቀነስ ፍርድ ቤቶች አማራጭ ቅጣቶችን ሊተገብሩ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ የኢሰመኮ የሃዋሳ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ በጋሻው እሸቱ በበኩላቸው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል አዲስ የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር አዋጅ በቅርቡ ማጽደቁ የታራሚዎችን መብቶችን አያያዝ ከማሻሻል አኳያ በአወንታዊነት የሚታይ እርምጃ እንደሆነ በመጥቀስ በክልሉ በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመቅረፍ አዋጁን በፍጥነት ተግባራዊ ከማድረግ በተጨማሪ ለአዋጁ የማስፈጸሚያ ደንብ ሊዘጋጅለት እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡