የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሸን (ኢሰመኮ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በጋሞ ዞን፣ አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ በተለይም ከአካባቢ አስተዳደር መዋቅር ጥያቄ ጋር በተያያዘ ከነዋሪዎች ጥያቄ መነሳት ከጀመረበት ወቅት አንስቶ ነዋሪዎችን፣ የመንግሥት አስተዳደር እና ጸጥታ ኃላፊዎችን እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በማነጋገር የሰብአዊ መብቶች ክትትል እና ውትወታ ሲያደርግ ቆይቷል። በተጨማሪም ኮሚሽኑ በአካባቢው እየተፈጸሙ ያሉ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ወደ ከፋ ደረጃ እንዳይሸጋገሩ፤ የተፈጠሩ አለመግባባቶች ሕጋዊና ሰላማዊ መንገድን ተከትለው እንዲፈቱ ለአካባቢው የመንግሥት አስተዳደር፣ ለአስተዳደር መዋቅር ጥያቄ አቅራቢዎች እና ለፖለቲካ ፓርቲዎች ምክረ ሐሳብ በማቅረብ ሁኔታው ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኝ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

በጋሞ ዞን፣ አርባ ምንጭ ዙርያ ወረዳ ሥር የሚገኙ ኤልጎ፣ ወዘቃ፣ ደምብሌ እና ጫሞ 01 የተባሉ አራት ቀበሌዎች ከጋሞ ዞን በመውጣት ልዩ ወረዳ ሆነው ለመደራጀት በተለያየ ጊዜ ጥያቄ ሲያነሱ ቆይተው የነበረ ሲሆን በተለይ ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ ውዝግቡ እየተባባሰ እንደመጣ ያስረዳሉ፡፡ ኢሰመኮ ያነጋገራቸው የአስተዳደር መዋቅር ጥያቄ አቅራቢዎች በተለያዩ መድረኮች እና ወቅቶች በሚያነሱት በዚህ የአስተዳደር መዋቅር ጥያቄ ምክንያት እና በስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ፣ ለሁለቱም ምክር ቤቶች የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲን በመምረጣቸው ምክንያት የጋሞ ዞን አስተዳደር በተለያየ መንገድ ስልታዊ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እየተፈጸመብን ነው በማለት ቅሬታ ያቀርባሉ። የዞኑ አስተዳደር በበኩሉ የአስተዳደር መዋቅር ጥያቄ አቅራቢዎች የአካባቢ ምርጫ ተካሂዶ አካባቢውን ለማስተዳደር ሕግን በተከተለ መንገድ ምርጫውን በማሸነፍ ሥልጣን ሳይረከቡ መንግሥት ቀበሌዎቹን ማስተዳደር የለበትም በሚል ምክንያት በአካባቢው የመንግሥት መዋቅር እንዲፈርስና አካባቢው እንዳይረጋጋ እያደረጉ ነው በማለት ምላሽ ይሰጣል፡፡

ከጥቅምት ወር 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በአስተዳደር መዋቅር ጥያቄ አቅራቢዎች እና በጋሞ ዞን አስተዳደር መካከል ያለው አለመግባባት ውጥረት እየጨመረ ቆይቶ፣ ጥቅምት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. አንድ በወንጀል የተጠረጠረ ግለሰብ በኤልጎ ቀበሌ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር በዋለበት ሂደት እና በቁጥጥር ሥር በነበረበት ወቅት በተፈጸመበት ድብደባ መሞቱን ተከትሎ ሁኔታው እጅግ ተባብሶ ወደ ግጭት አምርቷል። የጋሞ ዞን ፖሊስ አስተዳደር ከግለሰቡ ግድያ ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ የፖሊስ አባላትን በቁጥጥር ሥር በማዋል ምርመራ እያደረገ መሆኑን ለኢሰመኮ አስረድቷል፡፡ ሆኖም ከጥቅምት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ክስተት ጀምሮ በተለያዩ ሰዎችና ቡድኖች በተፈጸሙ ጥቃቶች የነዋሪዎች የሙዝ እርሻዎች እና በመንግሥት የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ከፍተኛ ንብረት ማውደም ጉዳት ደርሷል፣ በተለይም ከኅዳር 16 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ ጊዜዎች በተፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት በግለሰቦች እና በጸጥታ አካላት በተወሰዱ የኃይል እርምጃዎች ለጊዜው ቁጥራቸው በትክክል ያልታወቀ ነዋሪዎች እና የጸጥታ አባላት ላይ የሞት እና የአካል ጉዳት ደርሷል፡፡ እንዲሁም በርካታ ነዋሪዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ፡፡

የአስተዳደር መዋቅር ጥያቄ አቅራቢዎች እና በዞኑ አስተዳደር መካከል በሚፈጠሩ ተደጋጋሚ አለመግባባቶች በአካባቢው ነዋሪዎችና በጸጥታ ኃይል አባላት ላይ የሞት እና የአካል ጉዳት፣ እንዲሁም የዘፈቀደ እስር እና የንብረት ውድመት እያደረሰ መሆኑን ኢሰመኮ ክትትል እና ምርመራ ሲያደርግ የቆየ ሲሆን፤ ምርመራው ሲጠናቀቅ ሙሉ ሪፖርቱ ይፋ የሚደረግ ይሆናል፡፡ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በሁለቱ ወገኖች መካከል አሁንም ይህ ሪፖርት እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ የቀጠለው ውጥረት፣ ግጭት እና እየተወሰዱ ያሉ የኃይል እርምጃዎች በነዋሪዎች ላይ ተጨማሪ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እንዳያስከትል ኮሚሽኑ ያለውን ሥጋት ገልጸው፣ “የፌዴራል እና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት ከአካባቢው ነዋሪዎች እና ከዞኑ አስተዳደር እንዲሁም ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በአፋጣኝ ውጥረቱን የሚያረግብ ሰላማዊ እርምጃዎች መውሰድ እና ዘላቂ መፍትሔ ተግባራዊ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው፣ እንዲሁም ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ነዋሪዎች በቂ የሆነ አስቸኳይ የሰብአዊ ድጋፍ እንዲቀርብና ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ተመልሰው በዘላቂነት የሚቋቋሙበት ሁኔታ እንዲመቻች ያስፈልጋል” ብለዋል። ዋና ኮሚሸነሩ አክለውም የአስተዳደር መዋቅር ጥያቄ አቅራቢዎችም በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ጥያቄያቸውን በሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ ብቻ ማቅረብ እንዳለባቸው አስታውሰዋል፡፡