የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሕገወጥ የሕፃናት ዝውውርን እና ፍልሰትን በሚመለከት ሰኔ 9 እና 10 ቀን 2015 ዓ.ም. በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው ውይይት ላይ የሕፃናት ፍልሰትን በሚመለከት ያከናወነውን የሰብአዊ መብቶች ክትትል ግኝቶችን እና ምክረ ሐሳቦችን አቅርቧል። የኮሚሽኑ ክትትል በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ከምባታ ጠምባሮ ዞን፣ ሃዲያ ዞን፣ ጋሞ ዞን እንዲሁም ወላይታ ዞን በሚገኙ 12 ወረዳዎች ውስጥ ያለውን የሕፃናት ፍልሰተኞች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ ሸፍኗል።

መድረኩ የተዘጋጀው በኢሰመኮ፣ ኮንራድ አደናወር ሽቲፍቱ (Konrad Adenauer Stiftung)፣ የተ.መ.ድ. የፍልሰተኞች ድርጅት (አይ.ኦ.ኤም./IOM) እና ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ትብብር ሲሆን በመድረኩ የክልሉ ምክትል ፕሬዚደንት እና የከተማ ልማት ኀላፊ፣ የወላይታ ሶዶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ እንዲሁም ከዞን እስከ ፌዴራል  ደረጃ ጉዳዩ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት የተወጣጡ ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡

ኢሰመኮ ያከናወነውን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል ኢ-መደበኛ ፍልሰትን ከመከላከል፣ ለፍልሰተኛ፣ ለተጎጂ እንዲሁም ለተመላሽ ሕፃናት ከሚሰጠው ጥበቃ፣ ከቅንጅታዊ አሠራር እና የፍትሕ አሰጣጥ እንዲሁም ከሰብአዊ መብቶች አያያዝ አኳያ የተለዩ ግኝቶች እና የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች በዝርዝር ለተሳታፊዎች ለውይይት ቀርበዋል፡፡ በዝግጅቱ ላይ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት፣ የዘርፉ ተመራማሪዎች እና ምሁራን የተለዩትን የሰብአዊ መብት ጉዳዮች መሠረት በማድረግ የሕፃናት ፍልሰትን አስቀድሞ ለመከላከል፣ ተገቢውንና ለሕፃናት ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጥ ጥበቃና ድጋፍ ለመስጠት፣ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም ትብብርና ቅንጅታዊ አሠራርን ለማጠናከር የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን በስፋት ተወያይተዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ክትትል በተደረገባቸው አካባቢዎች የሕፃናት ፍልሰት በስፋት እንደሚካሄድ የተመላከተ ሲሆን ሕፃናቱ በብዛት ሀገር ውስጥ ወደሚገኙ የተለያዩ ከተሞች ቢፈልሱም ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ግን በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች አማካኝነት ድንበር ተሻግረው ከሀገር እንደሚወጡ እና ለከፋ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተጋላጭ እንደሚሆኑ ተጠቅሷል፡፡

የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ
የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ

የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ በመክፈቻ ንግግራቸው መከላከልን መሠረት ያደረገ ለሕፃናት ከፍተኛ ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጥ የመብቶች ጥበቃ ተግባራዊ እንዲደረግ እና ተጠያቂነትን በማስፈን ለሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች አጥጋቢ ምላሽ ለመስጠት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተው በቅንጅት በመሥራት የሀገር ውስጥ እንዲሁም ድንበር ተሻጋሪ የሕፃናትን ፍልሰት መቆጣጠር አስፈላጊ መሆኑን አሳስበዋል፡፡ አክለውም መንግሥት ማስረጃ ላይ በተመሠረተ እና ሁሉንም የመንግሥት አካላት ባሳተፈ መልኩ የሕፃናት ፍልሰተኞችን መብቶች ለማስጠበቅ እንዲሁም ከፍልሰት ጋር ለተያያዙ ችግሮች መፍትሔ ማመቻቸት ይቻል ዘንድ ረቂቅ የፍልሰት ፖሊሲውን በአስቸኳይ አጽድቆ ወደ ሥራ ማስገባት ይኖርበታል ብለዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል የተከበሩ ወ/ሮ አቡኔ ዓለም ተመስገን የሕፃናት ፍልሰት ለሚበዙባቸው አካባቢዎች ትኩረት ተሰጥቶ የቅድመ መከላከል ሥራ መሠራት እንዳለበት በመግለጽ የሕፃናት ፍልሰት በቂ ትኩረት ያልተሰጠው በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት እንዲረባረቡ ጥሪ አቅርበዋል።