የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአፋር፣ አማራ እና ትግራይ ክልሎች ከተከሰተው ጦርነት ጋር በተያያዘ በርካታ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል እና ምርመራ ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ ኮሚሽኑ ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም. በደቡብ አፍሪካ፣ ፕሪቶሪያ ከተፈረመው የዘላቂ ሰላም እና ግጭት ማቆም ስምምነት ወዲህም ሆነ ከዛ ቀደም ላሉት ጊዜያት ክትትል እያደረገባቸው ከሚገኝባቸው ጉዳዮች መካከል በጦርነቱ ወቅት የተቀበሩና በመሬት ላይ ያላግባብ ተበታትነው የሚገኙ ፀረ-ሰው ፈንጂዎች (anti-personnel mine) በሲቪል ሰዎች በተለይም በሕፃናት ላይ እያደረሱት ያለውን ጉዳት የተመለከተው ይገኝበታል። 

እ.ኤ.አ. በ1997 የፀረ-ሰው ፈንጂዎች ጥቅም፣ ምርት፣ ግብይት እና ክምችትን ለማገድ በተደረገው ስምምነት (የኦታዋ ስምምነት) መሠረት ‘‘ፀረ-ሰው ፈንጂ’’ ማለት ሰው በአካባቢው ሲገኝ፣ ሲቀርበው ወይም ሲነካው እንዲፈነዳ ተደርጎ በመሬት ላይ፣ ተቀብሮ ወይም ከመሬት በላይ ከቁስ ጋር ተጣብቆ ሊገኝ የሚችል እና አንድ ወይም ከዚያ በላይ ሰዎችን ለመግደል፣ ለማቁሰል ወይም አቅም ለማሳጣት የተሠራ ፈንጂ/የጦር መሣሪያ ነው። ስምምነቱ በዋናነት ፀረ-ሰው ፈንጂዎች መጠቀምን ጨምሮ የማልማት፣ የማምረት፣ የማከማቸት ወይም ለሌሎች የማስተላለፍ ድርጊቶችን ይከለክላል።

ኢትዮጵያም ይህን ስምምነት እ.ኤ.አ. በ1997 ፈርማ በ2004 ያጸደቀች እንደመሆኑ፤ ሌሎች ዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊና ብሔራዊ ሕግጋትን ጨምሮ ስምምነቱ በሚጥላቸው ግዴታዎች መሠረት መንግሥት በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሉ ፀረ-ሰው ፈንጂዎችን የማስወገድ ወይም መወገዳቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ እርምጃዎችን የመውሰድ ግዴታ አለበት። 

ባለፉት ዓመታት በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ ሲቪል ሰዎች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች፣ በእርሻ፣ በውሃ መቅጃ እና በገበያ ቦታዎች እንዲሁም የትምህርት ወይም የጤና ተቋማትን የመሳሰሉ የዕለት ተዕለት መሠረታዊ ሕይወት ወደሚከወኑባቸው ሥፍራዎች በሚወስዱ መንገዶች አካባቢ የተቀበሩ ፈንጂዎች፣ የተጣሉ ቦምቦች፣ የከባድ መሣሪያ ቅሪቶች እና በቀላል ንክኪ የሚፈነዱ ሌሎች መሣሪያዎች በሰዎች ሕይወት፣ አካልና ንብረት ላይ ጉዳት እያደረሱ ይገኛል።

ኮሚሽኑ ይህን በተመለከተ ባደረገው ክትትል በአፋር ክልል፣ ካሳጊታ ከተማ በአንድ መኖሪያ አካባቢ በድንገት በፈነዳው የሞርታር ጥይት ምክንያት 4 ሰዎች ወዲያው ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን በከፍተኛ ደረጃ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው 5 ሰዎች ወደ ዱብቲ ሆስፒታል ተወስደዋል፡፡ ሆስፒታል ከደረሱ በኋላም አንድ ሕፃን ሕይወቱ ማለፉን ኮሚሽኑ አረጋግጧል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከአፋር ክልል አድዓር ወረዳ ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት በተገኘ መረጃ መሠረት 23 ሕፃናት በፈንጂ ጉዳት እንደሞቱ፣ እንዲሁም ወደ 20 የሚገመቱ ተጨማሪ ሕፃናት ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ለመረዳት ተችሏል፡፡

በተጨማሪም ኢሰመኮ ከጥር 12 እስከ ጥር 17 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ ባደረገው የሰብአዊ መብቶች ክትትል እንደተገነዘበው በጦርነቱ ወቅት በአዲአርቃይ ወረዳ ሥር ከሚገኙ 22 ቀበሌዎች ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያ እና በደባርቅ ከተማ ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው ሲኖሩ የቆዩ ተፈናቃዮች፣ ከጥቅምት 25 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ቀድሞ ቀያቸው እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡ ተፈናቃዮቹ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ከመደረጉ በፊት አካባቢውን ወዳድቀው ከሚገኙ የጦር መሣሪያዎች እና ፈንጂዎች ሙሉ በሙሉ የማጽዳት ሥራ ባለመከናወኑ ክትትሉ ከመካሄዱ ከሦስት ወራቶች በፊት ሕይወታቸው ያለፈ እና አካል ጉዳት የደረሰባቸው ሕፃናት መኖራቸውን ተገንዝቧል።

በወቅቱ በተለያዩ አካባቢዎች የነበረውን ሥጋት ለመቀነስ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አካባቢውን ከፈንጂ እና ከወዳደቁ የጦር መሣሪያዎች ለማጽዳት ጥረት ማድረጉን ኮሚሽኑ የክትትል ሥራውን ባከናወነበት ወቅት ለመረዳት ችሏል። 

የኦታዋ ስምምነት አንቀጽ 6(3) የፈንጂ ተጎጂዎች (landmine victims) ተገቢውን የእንክብካቤ እና የተሐድሶ ድጋፍ ማግኘትን ጨምሮ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ውስጥ ተመልሶ የመካተት (social and economic reintegration of the mine victims) መብቶች እንዳላቸው ይደነግጋል። የፈንጂ ተጎጂዎች ከአደጋው በኋላ የሚከሰቱ ጭንቀቶችን (post-traumatic stress disorder) እና ማንኛውንም ዓይነት ጉዳቶች ለመቋቋም፣ አምኖ ለመቀበልም ሆነ ከማኅበረሰቡ ጋር ተመልሶ ለመቀላቀል ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ የሚያግዝ የማኅበረ ሥነ-ልቦና ድጋፍ (psychosocial support) ሊደረግላቸው ይገባል። በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ውስጥ ተመልሰው እንዲካተቱ የሚያስችሉ በኢኮኖሚ የማብቃት (economic empowerment)፣ አካታች ስልጠናና ትምህርት እንዲሁም የሥራ ዕድል ማመቻቸት ያስፈልጋል።

በተመሳሳይ ዓለም አቀፉ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነትም በተቀበሩና በተጣሉ ፈንጂዎች እንዲሁም መሰል ተቀጣጣይ ነገሮች ምክንያት የአካል፣ የሥነ-ልቦና እና የአእምሮ ጉዳት ለደረሰባቸው ተጎጂዎች ሊደረጉ ስለሚገባቸው ድጋፎች ተጨማሪ ጥበቃ ይሰጣል። በስምምነቱ አንቀጽ 26 መሠረት አካል ጉዳተኞች የተሟላ አካላዊ፣ አእምሯዊ፣ ማኅበራዊና ሞያዊ ብቃት እንዲሁም በሁሉም የሕይወት መስኮች የተሟላ ተካታችነትና ተሳትፎ እንዲኖራቸው የሚያስችል የማቋቋም እና ተሐድሶ (habilitation and rehabilitation) አገልግሎቶች የማግኘት መብት እንዳላቸው ይደነግጋል። ይህም ሲባል የፈንጂ ተጎጂዎች ጉዳቱ ሊያስከትልባቸው ከሚችለው የአካል፣ የተግባቦትና ግንዛቤ፣ የንግግር ቋንቋ ውስንነቶች በመነሳት አዳዲስ ክህሎቶችን፣ ችሎታዎችን እና ዕውቀቶችን እንዲያገኙ ማመቻቸትን እንዲሁም የተጎዳውን አካል የሚተካ፣ የሰውነት ማጠንከሪያ፣ ድጋፍ ወይም የእንቅስቃሴ አጋዥ መሣሪያዎች አቅርቦትን ይመለከታል። 

ስለሆነም፦ 

  • ጦርነት በተካሄደባቸው አካባቢዎች ያሉ የተቀበሩ ፈንጂዎች፣ የተጣሉ ቦምቦች፣ የከባድ መሣሪያ ቅሪቶች እና በቀላል ንክኪ የሚፈነዱ ሌሎች መሣሪያዎችን የማጽዳት እና ሙሉ በሙሉ የማስወገድ ተግባር እንዲፋጠን፣
  • ከማጽዳት ተግባሩ ጎን ለጎን መንግሥት ለፈንጂ ተጎጂዎች ሊደረጉ የሚገባቸውን የማቋቋም እና ተሐድሶ አገልግሎት ድጋፎች እንዲያስፋፋ ኮሚሽኑ ጥሪውን ያቀርባል።