የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) ጦርነት በተካሄደባቸው የትግራይ ክልል እና አዋሳኝ አካባቢዎች ያለውን አጠቃላይ ሁኔታ፣ በተለይም በቦታው ያሉ የሲቪል ሰዎችን ደኅንነት እንዲሁም በጦርነቱ ምክንያት የደረሰውን ሰብአዊ ቀውስና ከመኖሪያ ቦታቸው የተፈናቀሉ ሰዎችን ሁኔታ በመከታተል ላይ ይገኛል። ከታኅሣሥ 6 እስከ ታኅሣሥ 11 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ፣ እንዲሁም ከታኅሣሥ 22 እስከ ታኅሣሥ 27 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ በትግራይ ክልል እና በአዋሳኝ አካባቢዎች ያለውን የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ሁኔታ በተመለከተ ያዘጋጀውን ሪፖርት ከዚህ ቀደም ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

በዚሁ ሪፖርት የኮሚሽኑ ክትትል ባለሞያዎች ከጥር 2 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ለተጨማሪ ክትትል መቀሌ ከተማ እና በሌሎች የትግራይ ክልል አካባቢዎች እንደሚገኙና ኮሚሽኑ በግጭቱ ምክንያት የተፈጠረውን የሰብአዊ ቀውስ በመመርመር ላይ መሆኑን ጠቅሶ፣ ስራው ሲጠናቀቅ ሪፖርቱን ይፋ እንደሚያደርግ ገልጾ ነበር። በዚህም መሰረት፣ ኢሰመኮ ከጥር 2 ቀን እስከ ጥር 15 ቀን 2013 ዓ.ም. በመቀሌ ከተማ ከፍተኛ ወታደራዊ እና ሲቪል አመራሮችን፣ የጤና ዘርፍ ሰራተኞችን፣ ነዋሪዎችን፣ ተጎጂዎችን እና እንደጊዚያዊ መጠለያ በሚያገለግሉ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችን አነጋግሯል። እንዲሁም ኮሚሽኑ በደቡባዊው የትግራይ ዞን አላማጣ፣ መሆኒ እና ኩኩፍቶ ከተሞች ተመሳሳይ ክትትል አድርጓል።

በክልሉ ያለው የፀጥታ ሁኔታ እንዲሁም የመሰረተ ልማትና የማኅበራዊ አገልግሎቶች ገና በተሟላ ሁኔታ ወደ መደበኛ ስራቸው አለመመለስ፣ በሚፈለገው መጠንና ፍጥነት አስፈላጊ ወደሆኑ ቦታዎች ሁሉ ተንቀሳቅሶ ምርመራ እና ክትትል ለማድረግ አዳጋች አድርጎታል። ሆኖም ኮሚሽኑ ከቅርብና ከርቀት፣ እንዲሁም ልዩ ልዩ ተአማኒ የመረጃ ምንጮችን በመጠቀም እና ማስረጃዎችን በማሰባሰብ የሚያደርገውን ክትትል በመቀጠል፣ የሚደርስበትን ግኝቶች ወደፊት ይፋ ያደርጋል። በተጨማሪም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸምና ከሰአት እላፊ ገደብ ጋር በተያያዘ ሰለተፈጸሙ ግድያዎች ጨምሮ በልዩ ልዩ ቦታዎች ተፈጽመዋል ስለተባሉ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች የማጣራት ሂደቱ የቀጠለ ሲሆን ወደፊት የሚገለጽ ይሆናል፡፡ ይህ ሪፖርት በቅርቡ በተካሄደው የክትትል ስራ ዋነኛ ግኝቶች ላይ ያተኩራል።