የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሰኔ 16 ቀን 2016 ዓ.ም. በ 4 ክልሎች ለሚደረገው የ6ኛው ዙር ቀሪ እና ድጋሚ ምርጫ የሰብአዊ መብቶች ክትትል ለሚያከናውኑ ባለሙያዎች ሰኔ 6 እና 7 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ስልጠና ሰጥቷል። ስልጠናው በምርጫ ወቅት የሚከናወን የሰብአዊ መብቶች ክትትል ምንነትና ሥነ ዘዴዎችን እንዲሁም የምርጫ ክትትል ባለሙያዎች ሊከተሏቸው የሚገቡ ደንቦችና መርሖችን ለማስታወስ ያለመ ነው።
የስልጠናው ተሳታፊዎች የምርጫ ቅሰቀሳ የማይደረግበት የጥሞና ጊዜን ጨምሮ፣ የድምፅ መስጫ ዕለት እና ሌሎች የቅድመ እና የድኅረ ምርጫ ሂደቶችን ክትትል የሚያደርጉ ናቸው። በስልጠናው 9 ሴቶች እና 23 ወንዶች በአጠቃላይ 32 የክትትል ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን፣ ከኢሰመኮ የተለያዩ የዘርፍ ሥራ ክፍሎች ከተውጣጡ የክትትል ባለሙያዎች በተጨማሪ ኮሚሽኑ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር ያለውን አጋርነት ለማጠናከር በማሰብ ምርጫው በሚከናወንባቸው አካባቢዎች ከሚገኙ 4 ዩኒቨርሲቲዎች የተወከሉ መምህራንም ይገኙበታል። የስልጠናው መጠናቀቅን ተከትሎ የክትትል ባለሙያዎቹ ምርጫው በሚደረግባቸው በተመረጡ የአፋር፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ የማእከላዊ ኢትዮጵያ እና የሶማሊ ክልሎች አካባቢዎች ተሰማርተዋል።
ስልጠናው ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና ከናሽናል ዴሞክራቲክ ኢንስቲትዩት (National Democratic Institute) በተገኙ ባለሙያዎች ተሰጥቷል። በዚህም በምርጫ ወቅት የሚከናወን የሰብአዊ መብቶች ክትትል ምንነትና ሥነ ዘዴዎችን እንዲሁም የምርጫ ክትትል ባለሙያዎች ሊከተሏቸው የሚገቡ ደንቦችና መርሖች ላይ በተሰጠ ማብራሪያ ውይይት ተደርጓል። በተጨማሪም ለሰብአዊ መብቶች ክትትሉ የተዘጋጁ የክትትል ቅጾችን አስመልክቶ ለባለሙያዎች ገለጻ ተሰጥቷል።
የኢሰመኮ የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል በስልጠናው መክፈቻ ላይ ባስተላለፉት መልእክት፣ ምርጫ በዋናነት የሰዎች በሕዝባዊ ጉዳዮች ላይ የመሳተፍ መብት አንደኛው መተግበሪያ ሂደት መሆኑን አስታውሰው ‘‘በሂደቱ የአመለካከት እና ሐሳብን በነጻ የመያዝና የመግለጽ መብት፣ የመደራጀት መብት፣ የመዘዋወር ነጻነት እና የመሳሰሉ ሰብአዊ መብቶች ተግባራዊ አፈጻጸማቸውን ክትትል ማድረግ አስፈላጊ ነው’’ ብልዋል። አክለውም ከምርጫው ጋር በተገናኘ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ጥቆማና አቤቱታ ያለው ማንኛውም አካል በአካባቢው ለሚያገኛቸው የሰብአዊ መብቶች ክትትል ባለሙያዎች፣ በአቅራቢያ በሚገኙ የኢሰመኮ የከተማ ጽሕፈት ቤቶች በአካል በመገኘት ወይም በኮሚሽኑ ነጻ የስልክ መስመር 7307 ላይ በመደወል ማቅረብ እንደሚቻል ገልጸዋል።