ዓለም አቀፍ የስደተኞች ቀን ከታኅሣሥ ወር 1993 ዓ.ም. ጀምሮ በዓለም እና ሀገር አቀፍ ደረጃ የስደተኞችን ሰብአዊ መብቶችና ፍላጎቶች ለማሳካት የሚያስችል የፖለቲካ ቁርጠኝነትን እና የሃብት ምደባ ለማጠናከርና ለማነቃቃት በየዓመቱ ሰኔ 13 ቀን ታስቦ ይውላላል። የዘንድሮ የስደተኞች ቀን የሚከበረው ‘ደኅንነትን መሻት ሰብአዊ መብት ነው’ በሚል መሪ ቃል ሲሆን፣ ‘የደኅንነትን መብት’ ማክበር እና መከበሩን ማረጋገጥ ስደተኞች ጥገኝነት በሚጠይቁበት ሂደትም ሆነ የስደተኝነት እውቅና አግኝተው በሚኖሩበት ወቅት በእኩልነት መስተናገዳቸውን፣ ሰብአዊ ክብራቸው እና ደኅንነታቸውን መጠበቁን ማረጋገጥ ያጠቃልላል። ይህንን ቀን መታሰቢያ በማድረግ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ኢትዮጵያ ለስደተኞች እና ለጥገኝነት ጠያቂዎች በሮቿን ክፍት በማድረጓና ከ850 ሺህ በላይ ስደተኞችን ማስተናገዷ በአወንታዊ ጎኑ የሚታይ መሆኑን አስታውሶ፣ በመንግሥት የስደተኝነት እውቅና የመስጠት ሂደትን ጨምሮ፣ ለስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች የሚሰጡ አገልግሎቶች ልዩ ፍላጎትን መሰረት ያደረገ እንዲሆን ጥሪ ያቀርባል።
በኢትዮጵያ ከሚኖሩት ስደተኞች ውስጥ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች ናቸው፡፡ ከ50% በላይ የሚሆኑት ሴቶች፣ ሕፃናት፣ አካል ጉዳተኞች እና አረጋዊያን ናቸው፡፡ ምንም እንኳን በ2011 ዓ.ም. በወጣው የስደተኞች ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1110/2011 አንቀጽ 38 ለእነዚህ የሕብረተሰብ ክፍሎች መንግሥት ልዩ ፍላጎታቸውን መሰረት ያደረገ እገዛ እንደሚያደርግ የተገለጸ ቢሆንም፣ አተገባበሩ በርካታ ውስንነቶች አሉበት።
ኢሰመኮ በጋምቤላ እና በሶማሌ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ 10 የስደተኛ መጠለያ ካምፖች እና መቀበያ ጣቢያ ላይ ባከናወነው የሰብአዊ መብቶች ክትትል መሰረት የትምህርትና የጤና አገልግሎት አቅርቦትን ጨምሮ በርካታ ጠንካራ ጎኖችን የተመለከተ ሲሆን፤ በአንጻሩ ክፍተቶችንም ለይቷል፡፡ በሁሉም የስደተኛ መጠለያ ጣብያዎች ውስጥ ሴቶች በወሊድ ወቅት እና በድኅረ ወሊድ በቂ የሕክምና አገልግሎት እንደማያገኙ፣ በመጠለያዎች ውስጥ በሴቶች ላይ የሚደርስ የጾታ ጥቃት መኖሩ፣ በአካባቢው ባለው የሥርዓተ-ጾታ ልማድ ምክንያት ማንኛውም ስራ ሴቶች ያለወንዶች ድጋፍ የሚያከናውኑ መሆኑን እና በቂ የንጽሕና መጠበቂያ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች በቂ ድጋፍ እንደማይደረግላቸው ተመልክቷል። ሴት ሕፃናት አብዛኛው ጊዜ በቤት ውስጥ ሥራ ስለሚጠመዱ ለትምህርታቸው ትኩረት እንደማይሰጡ፣ እድሜያቸው ከ6 ዓመት በላይ የሆኑ ሕፃናት አልሚ ምግብ ስለማያገኙ ለተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንደሚጋለጡ ታይቷል፡፡
በተጨማሪም በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ያሉ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ለአካል ጉዳተኛ እና አረጋዊያን ስደተኞች ተደራሽ አለመሆናቸው፣ በተለያዩ የተራድኦ ተቋማት የሚደረገው የአካል ጉዳተኞች መርጃ መሳሪያዎች ከስደተኞቹ ቁጥር ጋር አለመመጣጠን እና ልዩ ልዩ የአካል ጉዳት ላለባቸው የአካል ጉዳተኛ ስደተኛ ተማሪዎች የትምህርት መርጃ ቁሳቁሶች (hearing aid and braille) አለመኖር ከተለዩት ክፍተቶች መካከል ናቸው። እንዲሁም በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚገኙ መምህራን ስለአካል ጉዳተኝነት ያላቸው ግንዛቤ አናሳ መሆን፣ የተለያየ የአካል ጉዳት ላለባቸው ስደተኞች እንደየ አካል ጉዳታቸው የሚያስፈልጋቸው የትምህርት አሰጣጥ/ሥነ-ዘዴ አለመኖር፣ ለአካል ጉዳተኞች የመሰብሰቢያ እና የመዋያ ስፍራ (persons with disabilities friendly spaces) አለመኖር፣ ለአረጋዊያን የምገባ አገልግሎት አለመኖር፣ ለአረጋዊያን ድጋፍ የሚያደርጉ በቂ ድርጅቶች ባለመኖራቸው ምክንያት ለችግር መዳረጋቸውን መረዳት ተችሏል፡፡
ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ ስደተኞች ፍላጎቶቻቸውን መሰረት ያደረገ እገዛ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ እነዚህ የማኅበረሰብ ክፍሎች በመደበኛ ሁኔታም ቢሆን ለአድሎ እና ጥቃት የተጋለጡ ሲሆን የስደተኝነት ሁኔታ ደግሞ ይበልጥ ለጥቃት ያጋልጣቸዋል፡፡ ስደተኝነት ከፍ ላለ ብዝበዛ፣ መጎሳቆል እና መገለልን ጨምሮ ለጥበቃ ስጋቶች የሚያጋልጥ ከመሆኑ ባሻገር ለመብት ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ ስደተኞች ሰብአዊ እርዳታን፣ ትምህርትን፣ ጤናን እና ሌሎች አገልግሎቶችን በእኩልነት ለማግኘት ይቸገራሉ። በተጨማሪም ለምሳሌ አረጋውያን ወይም አካል ጉዳት ያለባቸው በመሆናቸው ብቻ ለአድልዎ ይጋለጣሉ፡፡ እንዲሁም አብዛኛውን ጊዜ ከውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶች እና የአመራር እድሎች ይገለላሉ።
ስለሆነም፡
- ኢትዮጵያ በተቀበለቻቸው የዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ የሰብአዊ መብቶች ሰነዶች እውቅና የተሰጣቸውን ‘የእኩልነት/equality’ እና የ‘ምክንያታዊ ማመቻቸት/reasonable accommodation’ መርሆችን ባገናዘበ መልኩ፣ መንግሥት በመንግሥት እና በተራድኦ ተቋማት ለስደተኞች የሚቀርቡ የሰብአዊ ድጋፎችም ሆኑ ሌሎች አገልግሎቶች ለመብት ጥሰት ተጋላጭ ለሆኑ ስደተኞች አካታች፣ ተደራሽ እና ሰብአዊ ክብራቸውን እና ደኅንነታቸውን በጠበቀ መልኩ መሆናቸውን ሊያረጋግጥ ይገባል፤
- በተጨማሪም በውሳኔ አሰጣጥ ላይ እንዲሳተፉና ለመብቶቻቸው መከበር ሁኔታው ሊመቻችላቸው ይገባል፡፡