የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከታኀሣሥ 8 እስከ 14 ቀን 2016 ዓ.ም. በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በ3 ዞኖች፣ በ1 ልዩ ወረዳ፣ በ15 ወረዳዎች እና በ7 ከተሞች በሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎች የተጠርጣሪዎች የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ ባደረገው ክትትል እንዲሁም በመስቃን ወረዳ የሚገኙ የማረቆ ብሔረሰብ ተወላጆች ባቀረቡት የሰብአዊ መብቶች ጥሰት አቤቱታ መሠረት ከግንቦት 14 እስከ 20 ቀን 2016 ዓ.ም. ባከናወነው ምርመራ የለያቸውን ግኝቶች እና ያቀረባቸውን ምክረ ሐሳቦች አስመልክቶ ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም. በሆሳዕና ከተማ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።

በውይይቱ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር፣ የወንጀል ምርመራ ዘርፍ ተወካይ፣ የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ እንዲሁም የዞኖች፣ የልዩ ወረዳዎች፣ የወረዳዎች እና የከተሞች ፖሊስ ጣቢያዎች አዛዦች፣ የፍርድ ቤትና የፍትሕ ጽሕፈት ቤቶች ኃላፊዎች እና ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡ ኢሰመኮ የተጠርጣሪዎችን ሰብአዊ መብቶች ሁኔታ አስመልክቶ ባከናወነው ክትትል እንዲሁም በምሥራቅ ጉራጌ ዞን በመስቃን ወረዳ 9 ቀበሌዎች ውስጥ የሚገኙ የማረቆ ብሔረሰብ ተወላጆች ባቀረቡት አቤቱታ መሠረት ባደረገው ምርመራ የተለዩ ግኝቶችና የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች

በክትትሉ ተጠርጣሪዎች ወደ ፖሊስ ጣቢያዎች ሲገቡ መረጃዎቻቸው በባሕር መዝገብ ላይ መያዙ፣ በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረባቸው፣ የቤተሰብ ጥየቃ በሁሉም ቀናት መፈቀዱ፣ ቃላቸውን  ያለምንም ጫና እና ማስገደድ መስጠታቸው፣ በሴት ተጠርጣሪዎች ማደሪያ ክፍሎች ውስጥ መጨናነቅ አለመኖሩ፣ ማደሪያ ክፍሎች የኤሌክትሪክ መብራት ያላቸው መሆኑ በአበረታችነት ከተገለጹት መካከል ይገኛሉ። በሌላ በኩል እጅ ከፍንጅ ከተፈጸመ ወንጀል ውጪ በርካታ ተጠርጣሪዎች ያለፍርድ ቤት ማዘዣ እና ፖሊስ መጥሪያ የተያዙ መሆናቸው፣ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር በሚውሉበት ጊዜ የተያዙበት ምክንያት የማይገለጽላቸው መሆኑ፣ ቃል ከመስጠታቸው በፊት የሕግ ባለሙያ የማማከር እና በቃል መስጠት ሂደት እንዲገኙ የማድረግ መብት እንዳላቸው የማይነገራቸው መሆኑ እንዲሁም በግል ጠበቃ ለማቆም ለማይችሉ ተጠርጣሪዎች የሕግ ባለሙያ ድጋፍ እንዲያገኙ የሚያስችል አሠራር አለመኖር በክትትሉ ከተለዩ ክፍተቶች መካከል መሆናቸው በውይይቱ ተገልጿል።

የኢሰመኮ የሰብአዊ መበቶች ክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል የሪጅን ዳይሬክተር የሆኑት ሰላማዊት ግርማይ ንግግር እያደረጉ

የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ሽመልስ ካሳ በኢሰመኮ የቀረበው ሪፖርት ያለውን ነባራዊ ሁኔታ የሚያሳይ መሆኑን ገልጸው፣ በክትትሉ የተለዩ ጠንካራ ጎኖችን በማስቀጠል የታዩ ክፍተቶችን ለማሻሻል በትኩረት እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡ በተመሳሳይ የክልሉ ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ የፍትሕ ጥምር ኮሚቴ በየጣቢያዎቹ ክትትል እንደሚያደርግ፣ የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች ተፈጻሚነትንም ለማረጋገጥ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡ ተሳታፊዎች ባካሄዱት የቡድን ውይይት ከሥራ ኃላፊነታቸው አንጻር በአጭር፣ በመካከለኛ እና በረጅም ጊዜ ሊከናወኑ የሚገባቸውን ተግባራትና ምክረ ሐሳቦችን በመለየት የአንድ ዓመት የድርጊት መርኃ ግብር አዘጋጅተዋል።

በተመሳሳይ የውይይት መድረክ ኢሰመኮ በምሥራቅ ጉራጌ ዞን በመስቃን ወረዳ የማረቆ ብሔረሰብ ተወላጆች ባቀረቡት የሰብአዊ መብቶች ጥሰት አቤቱታ መነሻነት ያከናወነው ምርመራ፣ በአካባቢው ዕርቀ ሰላም የማጽናት ሥነ ሥርዓት ከተካሄደበት የካቲት 5 ቀን 2016 ዓ.ም. በኋላ በተፈጠሩ ግጭቶች የጉራጌና ማረቆ ብሔረሰብ ተወላጆች ሕይወት ማለፉን፣ የአካል ጉዳት መድረሱን፣ መኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውን እንዲሁም የነዋሪዎች በመረጡት ቦታ የመኖር እና ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት መገደቡን አመልክቷል፡፡ የሰላምና ጸጥታ እንዲሁም የፖሊስ አመራሮች የቀረበው ሪፖርት መሬት ላይ ያለውን እውነታ በግልጽ ያሳየ መሆኑን በመግለጽ በአካባቢው ሰላም ለማስፈን እየሠሩ መሆኑን፣ በድርጊቱ ተሳታፊ ናቸው የተባሉ የወረዳ አመራሮችን በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን እንዲሁም ለተፈጸሙ ግድያዎች የምሥራቅ ጉራጌ ዞን ፖሊስ መምሪያ የወንጀል ምርመራ መጀመሩን አስረድተዋል፡፡

የኢሰመኮ የሰብአዊ መበቶች ክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል የሪጅን ዳይሬክተር የሆኑት ሰላማዊት ግርማይ፣ የክልሉን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ለማሻሻል በጎ ጅምሮችን ማጠናከር እንዲሁም በክትትል እና ምርመራ ግኝቶች መሠረት የቀረቡ ምክረ ሐሳቦችን መተግበር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። በተለይም በክልሉ ያለውን የተጠርጣሪዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ለማሻሻል በግንዛቤ ማሳደጊያ ፕሮግራሞች፣ በምግብ በጀት እና በተጠርጣሪዎች የነጻ ሕክምና አገልግሎት ዙሪያ ኢሰመኮ ውትወታውን እንደሚቀጥል ገልጸዋል። አክለውም በማረቆ ልዩ ወረዳ እና በምሥራቅ መስቃን ወረዳ መካከል በወሰን ይገባኛል ጥያቄ መነሻነት የሚፈጠሩ አለመግባባቶች በዘላቂነት እንዲፈቱ የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሁለቱን አካላት በቅርበት በማነጋገር መፍትሔ እንዲሰጥ፣ የተጀመረውን የወንጀል ምርመራ በተገቢው ጊዜ በማጠናቀቅ የአጥፊዎች ተጠያቂነት እና የተጎጂዎች ተገቢ ካሳ የማግኘት መብት እንዲረጋገጥ ጥሪ አቅርበዋል።