የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ያለውን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ አስመልክቶ ከክልል፣ ከዞኖች እና ከልዩ ወረዳዎች ከተውጣጡ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ታኅሣሥ 21 ቀን 2018 ዓ.ም. በሆሳዕና ከተማ ውይይት አካሂዷል። ውይይቱ ኢሰመኮ በክልሉ ባከናወናቸው የሰብአዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራ ሥራዎች የለያቸው መልካም ተሞክሮዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እና እንዲስፋፉ እንዲሁም ለሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችና ሥጋቶች ምክንያት የሚሆኑ የሕግ፣ የተቋምና የአሠራር ክፍተቶች ተገቢው ትኩረት ተሰጥቷቸው የሚታረሙበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ያለመ ነው።

በውይይቱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር እንዳሻው ጣሰውን ጨምሮ የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት፣ የፍትሕ ቢሮ፣ የሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ፣ የፖሊስ ኮሚሽን እንዲሁም የዞኖች እና የልዩ ወረዳዎች የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

ዶ/ር እንዳሻው ጣሰው፣የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፕሬዝዳንት (በቀኝ)
በውይይቱ ኢሰመኮ ከዚህ ቀደም ባደረጋቸው የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ሥራዎች የለያቸው ግኝቶች ቀርበዋል። ክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ለሚነሱ ግጭቶች የኅብረተሰቡን ዕሴቶችና ባህላዊ የዕርቅ ሥርዓቶች በመጠቀም ለመፍታት ጥረት እያደረገ መሆኑ፣ ከኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ተፈናቅለው በክልሉ የሚገኙ ሰዎችን በመለየት መሠረታዊ አገልሎቶችን ማግኘት እንዲችሉ ጥረት እየተደረገ መሆኑ፣ የታራሚዎች የዕለት የምግብ በጀት ከ33 ብር ወደ 65 ብር ከፍ እንዲል መደረጉ እንዲሁም ፖሊስ ጣቢያዎችና ማረሚያ ቤቶች ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ለማድረግ የሚሠሩ ሥራዎች ሊበረታቱ የሚገባቸው መሆናቸው ተመላክቷል፡፡


በሌላ በኩል አልፎ አልፎ የሚነሱ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት ጥናትን መሠረት ያደረጉና ኅብረተሰብ አሳታፊ የሆኑ መንገዶችን በመጠቀም መሥራት እንደሚገባ እንዲሁም ግጭቶችን አስቀድሞ ለመከላከል እና በሚከሰቱበትም ወቅት ምላሽ ለመስጠት የሚወሰዱ እርምጃዎች ሰብአዊ መብቶችን ያከበሩ መሆናቸውን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ተገልጿል። በተጨማሪም ማረሚያ ቤቶች ራሳቸውን በበጀት ለመደጎም እና ዐቅማቸውን ለማጠናከር የታራሚዎችን ጥበቃና ደኅንነት ማእከል ባደረገ መልኩ የልማት ተግባራትን ማጠናከር እንደሚገባ ምክረ ሐሳብ ተሰጥቷል።


የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፕሬዝዳንት ዶ/ር እንዳሻው ጣሰው ኢሰመኮ በክልሉ የሆሳዕና ከተማ ጽሕፈት ቤትን መክፈቱን በአዎንታዊነት እንደሚመለከቱት ገልጸው፣ ኢሰመኮ የሚያከናውናቸውን የሰብአዊ መብቶች ተግባራት ተደራሽ ለማድረግ እና ችግሮችን ለመፍታት በየደረጃው ከሚገኙ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በቅርበት ለመሥራት የሚረዳ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በክልሉ መፍትሔ ሳያገኙ ለረጅም ጊዜ የቆዩ ችግሮች መኖራቸውን ገልጸው፣ የኢሰመኮን ምክረ ሐሳቦች መሠረት በማድረግ በርካታ ሥራዎች እንደተሠሩ እና ይሄው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል፣ በውይይቱ የተነሱ አሳሳቢ ጉዳዩችን መፍትሔ ለመስጠትም የሚመለከታቸው የክልልና የዞን ተቋማት ተገቢውን ትኩረት ሰጥተው እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ከኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ በሆኑ አካባቢዎች በዜጎች ሕይወትና ንብረት ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለማስቆም እንዲሁም የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀድሞ አካባቢያቸው ለመመለስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ሁለቱ ክልሎች በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡