የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከጥር 1 እስከ መጋቢት 30 ቀን 2017 ዓ.ም. ባለው ጊዜ በሰብአዊ መብቶች እና በሽግግር ፍትሕ፣ በሕፃናት፣ በታራሚዎች፣ በአረጋውያን እና በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መብቶች ላይ ያተኮሩ ስልጠናዎችን በተለያዩ ከተሞች ሰጥቷል።

በሰብአዊ መብቶች እና በሽግግር ፍትሕ ዙሪያ የወጣቶችን ሚና ለማሳደግ ያለሙ ስልጠናዎች ከተለያዩ ወጣት ማኅበራት ለተውጣጡ 63 አመራሮች እና አባላት ከየካቲት 10 እስከ 14 ቀን 2017 ዓ.ም. በአርባምንጭ ከተማ እና ከመጋቢት 15 እስከ 19 ቀን 2017 ዓ.ም. በሶዶ ከተማ ተሰጥቷል። በተመሳሳይ የማሕበረሰብ እና የሃይማኖት መሪዎችን ትኩረት ያደረጉ በድምሩ 64 ተሳታፊዎች የተሳተፉባቸው ስልጠናዎች ከየካቲት 4 እስከ 6 ቀን 2017 በጅማ እና ቢሾፍቱ ከተሞች ተከናውነዋል። በስልጠናዎቹ ስለ ሽግግር ፍትሕ ጽንሰ ሐሳብ፣ የሌሎች ሀገራት የሽግግር ፍትሕ ተሞክሮዎች እና በሂደቱ ታሳቢ ሊደረጉ የሚገቡ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች የቀረቡ ሲሆን ክህሎትን የሚያሳድጉ ተግባራዊ ልምምዶች ተካተዋል።

በሰብአዊ መብቶች እና በሽግግር ፍትሕ ዙሪያ ከአዲስ አበባ ከተማ እና ከኦሮሚያ ክልል ለተውጣጡ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሠራተኞች እና የሥራ ኃላፊዎች በአዳማ ከተማ ከመጋቢት 1 እስከ 5 ቀን 2017 ዓ.ም. የአሰልጣኞች ስልጠና ተሰጥቷል። የተሰጡት ስልጠናዎች በኢትዮጵያ ሊተገበር በታቀደው የሽግግር ፍትሕ ሂደት ሰልጣኞች ሊኖራቸው የሚችለውን ሚና ለማስገንዘብ፤ እንዲሁም የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ለመከታተል፣ ለመሰነድ እና ውትወታ ለማድረግ ክህሎት እንዲያዳብሩ ዕድል ፈጥሯል።

በሌላ በኩል ኢሰመኮ ከአሶሳ፣ ከመተከ እና ከካማሽ ዞን ማረሚያ ቤቶች ለተውጣጡ 31 የማረሚያ ቤት የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በታራሚዎች መብቶች እና አያያዝ ዙርያ ከመጋቢት 8 እስከ 12 ቀን 2017 ዓ.ም. በአሶሳ ከተማ እንዲሁም በትግራይ ክልል ከሚገኙ ማረሚያ ቤቶች ለተውጣጡ 34 የሥራ ኃላፊዎች ከመጋቢት 1 እስከ 5 ቀን 2017 ዓ.ም. በመቀሌ ከተማ ስልጠናዎቸን ሰጥቷል። ስልጠናዎቹ የታራሚዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝን በተመለከተ የማረሚያ ቤት አመራሮችና ባለሙያዎች ዕውቀታቸውን፣ አመለካከታቸውን እና ክህሎታቸውን ለመገንባት የሚያግዝ ነው። በተለይም ተሳታፊዎቹ ተግባራዊ ሊያደርጓቸው በሚገቡ መሠረታዊ የሰብአዊ መብቶች መመዘኛዎች ላይ የተሻለ ግንዛቤ እንዲያዳብሩም ስልጠናው ዕድል ፈጥሮላቸዋል።

በሩብ ዓመቱ ከተሰጡ ስልጠናዎች መካከል ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በተለያዩ ግጭቶች ምክንያት ተፈናቅለው በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለሚገኙ እና ወደ ቀዬአቸው ለተመለሱ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች አገልግሎት ለሚሰጡ 30 ባለሙያዎች እና የሥራ ኃላፊዎች በቦንጋ ከተማ ከመጋቢት 1 እስከ 5 ቀን 2017 ዓ.ም. የተሰጠው ስልጠና አንዱ ነው። በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ውስጥ የሚገኙና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የተለያዩ መሥሪያ ቤቶች በቅድመ መፈናቀል፣ በመፈናቀል እና በድኅረ መፈናቀል ወቅት በዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊ እና ሀገራዊ የሕግ ማዕቀፎች የተደነገጉ መብቶች፣ ከሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጋር በተያያዘ የመንግሥት ግዴታዎች እና መንግሥታዊ ያልሆኑ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ኃላፊነትን የተመለከቱ ጉዳዮች በስልጠናው ቀርበዋል።

ኢሰመኮ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አረጋውያን እና ጡረተኞች ማኅበር ለተውጣጡ 28 የሥራ ኃላፊዎች ከመጋቢት 16 እስከ 19 ቀን 2017 ዓ.ም. በአሶሳ ከተማ ስልጠና ሰጥቷል። በዚህ ስልጠና በአረጋውያን ላይ የሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን ለመከላከል፣ ሪፖርትና ውትወታ ለማድረግ በተግባር የታገዘ የክህሎት ልምምዶች ተካተውበታል።

እንዲሁም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በሕፃናት ጥበቃ ላይ ለሚሠሩ 35 ባለሙያዎች እና የሥራ ኃላፊዎች በሕፃናት መብቶች ዙሪያ ከመጋቢት 24 እስከ 28 ቀን 2017 ዓ.ም. በቦንጋ ከተማ ስልጠና ተሰጥቷል። ስልጠናው በክልሉ የሚታዩትን በሕፃናት ላይ የሚፈጸሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እና የመብት ጥሰቶችን መነሻ በማድረግ የተሰጠ ነው። ስልጠናው በሕፃናት ላይ የሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን የመለየት እና መወሰድ ስላለባቸው የእርምት እርምጃዎች ተሳታፊዎች በቡድን ውይይት ሐሳብ እና ልምድ እንዲለዋወጡ የማድረግ አጋጣሚን ፈጥሯል።