የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሐምሌ 2017 ዓ.ም. እስከ መስከረም 2018 ዓ.ም. ባሉት ሦስት ወራት በተለያዩ ከተሞች ለሚገኙ የወጣቶች ማኅበራት፣ ለሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እንዲሁም ለማረሚያ ቤት ፖሊሶች እና አመራሮች በሰብአዊ መብቶች እና በሽግግር ፍትሕ፣ በወንጀል የተጠረጠሩ እና ተፈርዶባቸው በመታረም ላይ የሚገኙ ሰዎች ሰብአዊ መብቶች ላይ ያተኮሩ ስልጠናዎችን ሰጥቷል።

ኢሰመኮ በሰብአዊ መብቶች እና በሽግግር ፍትሕ ዙሪያ በአርባ ምንጭ፣ በበደሌ፣ በዲላ፣በመቱ እና በሮቤ ከተሞች ከሐምሌ 14 እስከ ነሐሴ 23 ቀን 2017 ዓ.ም. ድረስ የአምስት የአምስት ቀናት የስልጠና መድረኮችን በማዘጋጀት ለ166 ወጣቶች የአሰልጣኞች ስልጠና ሰጥቷል። ስልጠናው ወጣቶች በሰብአዊ መብቶች ፅንሰ ሐሳብ እና እሴቶች ላይ ያላቸውን ዕውቀት እና ክህሎት በማሳደግ የሰብአዊ መብቶች መከበር ለሰላም እና አብሮ መኖር ያላቸውን ዋጋ ተረድተው የበኩላቸውን እንዲወጡ ለማድረግ ያለመ ነው።

በስልጠናዎቹ የሌሎች ሀገራት የሽግግር ፍትሕ ተሞክሮዎች የቀረቡ ሲሆን የወጣቶችን ጉልህ ሚና ለማሳደግ የሚረዱ ተግባራዊ ልምምዶች የተካተቱበት ነው። በዚህ የአሰልጣኞች ስልጠና ላይ የተሳተፉ ወጣቶች በየከተማቸው ለሚገኙ 113 ወጣቶች እና የማኅበር አባላት የመልሶ ስልጠና ሰጥተዋል።

በተጨማሪም ኢሰመኮ ከፕሮጀክት ኤክስፒዳይት ጀስቲስ (Project Expedite Justice) ጋር በመተባበር የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጀቶች በሽግግር ፍትሕ ሂደቱ ላይ በሚኖራቸው ሚና ዙሪያ በአራት ዙር የአሰልጣኞች ስልጠናዎችን ሰጥቷል። ስልጠናዎቹ ከሲዳማ እና ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች ለተውጣጡ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች በአርባ ምንጭ ከተማ፤ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ከትግራይ ክልሎች ለተውጣጡ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በአዳማ ከተማ እንዲሁም ከአፋር ክልል ለተውጣጡ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በኮምቦልቻ ከተማ ከሐምሌ 5 2017 እስከ መስከረም 30 ቀን 2018 ዓ.ም. ድረስ ለ76 ተሳታፊዎች የአምስት ቀናት ስልጠናዎችን መስጠት ተችሏል። ስልጠናው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በሽግግር ፍትሕ ዙሪያ ያላቸው መረዳት በማሳደግ እንዲሁም ሂደቱ ሁሉንም ማኅበረሰብ የሚያሳተፍ፣ ተጎጂዎችን ማዕከል ያደረገ፣ አካታች እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶችን ያከበረ እንዲሆን የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲወጡ የሚያስችል ነው።

በሌላ በኩል ኢሰመኮ በታራሚዎችና በተጠርጣሪዎች የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ዙሪያ ለማረሚያ ቤት አመራሮችና ፖሊሶች ስልጠና ሰጥቷል። ከመስከረም 19 እስከ 24 ቀን 2018 ዓ.ም. በነቀምት ከተማ የተሰጠው ይህ ስልጠና የማረሚያ ቤት አመራሮችና ፖሊሶች ከሥራቸው ጋር ተዛማጅ ስለሆኑ የሰብአዊ መብቶች ዕሴቶች ምንነት እና የታራሚዎችና የተጠርጣሪዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝን በተመለከተ ዕውቀታቸውን፣ አመለካከታቸውን እና ክህሎታቸውን ለመገንባት የሚያግዝ ነው። በስልጠናው ከኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ፣ ምዕራብ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋ፣ ቡኖ በደሌ፣ ምዕራብ ሸዋ ዞኖች እና ከጅማ አርጆ ማረሚያ ቤቶች ለተወጣጡ 36 የማረሚያ ቤት ፖሊስ አመራሮችና ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል። ለማረሚያ ቤቶች መካከለኛ አመራሮች እና ፖሊሶች የተሰጠው ስልጠና የስልጠናው ተሳታፊች በሥራቸው ተግባራዊ ሊያደርጓቸው በሚገቡ መሠረታዊ የሰብአዊ መብቶች መመዘኛዎች ላይ የተሻለ ግንዛቤ ሊያዳብሩ የሚችሉበትን ዕድል የፈጠረ ነው።