የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በ2017 ዓ.ም. በሲዳማ ክልል በ15 ፖሊስ ጣቢያዎች እና በይርጋለም ማረሚያ ቤት በሕግ ጥበቃ ሥር የሚገኙ ሰዎች ሰብአዊ መብቶች ሁኔታን አስመልክቶ ባከናወነው ክትትል በተለዩ ግኝቶች እና የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች ላይ ሐምሌ 11 ቀን 2017 ዓ.ም. ከባለድርሻ አካላት ጋር በሻሸመኔ ከተማ ውይይት አካሂዷል። በውይይቱ የሲዳማ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ፣ የክልሉ የጤና፣ ትምህርት እና ፍትሕ ቢሮዎች፣ የማረሚያ ቤቶች እና ፖሊስ ኮሚሽን እንዲሁም የዞኖች እና የሃዋሳ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

በውይይት መድረኩ በኢሰመኮ ክትትል የተለዩ እመርታዎች፣ አሳሳቢ ጉዳዮች እና የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። ክትትል በተደረገባቸው ፖሊስ ጣቢያዎች ከታዩ መሻሻሎች መካከል ተጠርጣሪዎች በሚያዙበት ጊዜ የተጠረጠሩበት ወንጀል እና የተያዙበት ምክንያት የሚገለጽላቸው መሆኑ፣ የተጠርጣሪዎች መረጃ አያያዝ መሻሻሉ፣ በተጠርጣሪዎች ላይ አካላዊ ጥቃት/ድብደባ እንዲሁም ሌላ ጭካኔ የተሞላበት፣ ኢ-ሰብአዊ ወይም አዋራጅ አያያዝ አለመፈጸሙ፣ ተጠርጣሪዎች ያለምንም ጫናና ማስገደድ ቃላቸውን መስጠታቸው፣ ከቤተሰቦቻቸው እና ከሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር እንዲገናኙ መደረጉ፣ በራሳቸው ወጪ የሕክምና አገልግሎት ማግኘት መቻላቸው እንዲሁም በፍርድ ቤት የሚሰጡ ትእዛዞች ተፈጻሚ መሆናቸው በውይይቱ ተጠቅሷል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች

በሌላ በኩል በአንዳንድ ፖሊስ ጣቢያዎች በሕግ ከተቀመጠው አግባብ ውጭ የታሰሩ ሰዎች መኖራቸው፣ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ተጠርጣሪዎች በሕግ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸው፣ የተጠርጣሪዎች ማደሪያ ክፍሎች የተጨናነቁ እና የንጽሕና ጉድለት ያለባቸው መሆኑ፣ ልዩ ድጋፍ ለሚሹ ተጠርጣሪዎች ፍላጎታቸውን መሠረት ያደረገ አያያዝ አለመኖሩ፣ በአብዛኛዎቹ ፖሊስ ጣቢያዎች 18 ዓመት ያልሞላቸው ተጠርጣሪዎች (በወንጀል ነክ ነገር ውስጥ በመግባት የተጠረጠሩ ሕፃናት) ለአካለ መጠን ከደረሱ ተጠርጣሪዎች ተለይተው አለመያዛቸው፣ ከቤተሰብ ምግብ ለማይቀርብላቸው ወይም በራሳቸው ዐቅም ምግብ ገዝተው መመገብ ለማይችሉ ተጠርጣሪዎች የሚቀርብ ምግብ አለመኖሩ እንዲሁም ክትትል በተደረገባቸው ሁሉም ፖሊስ ጣቢያዎች ለተጠርጣሪዎች በመንግሥት የሕክምና አገልግሎት የሚቀርብ አለመሆኑ በአሳሳቢነት የቀጠሉ ጉዳዮች መሆናቸው ተመላክቷል።

ኢሰመኮ በይርጋለም ማረሚያ ቤት ባደረገው ክትትል ከለያቸው ጠንካራ ጎኖች መካከል በታራሚዎች ላይ አካላዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ጥቃት፣ የማሰቃየት እና ሌሎች ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች አለመፈጸማቸው፣ ያለ በቂ ምክንያት ታራሚዎች በካቴና አለመታሰራቸው፣ የእምነት ነጻነት እና የመጎበኘት መብታቸው መከበሩ፣ ለታራሚዎች የቀለምና የሙያ ትምህርትና ስልጠና መሰጠቱ፣ ለሴት ታራሚዎች የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁስ መቅረቡ ዋና ዋናዎቹ ናቸው። በሌላ በኩል ታራሚዎች ከጾታ ባሻገር በሌሎች በሕግ የተቀመጡ መስፈርቶች መሠረት ተለይተውቶ አለመያዛቸው፣ ለታራሚዎች የሚቀርበው ምግብ የተመጣጠነ፣ በቂ እና ጥራቱን የጠበቀ አለመሆኑ፣ በማረሚያ ቤቱ ያለው የመጠጥና የንጽሕና መጠበቂያ ውሃ አቅርቦት በቂ አለመሆኑ እና ልዩ ትኩረት ለሚያስፈልጋቸው ታራሚዎች የሚደረግ ድጋፍ ውስን መሆኑ በክፍተትነት ተገልጸዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች ኢሰመኮ ላቀረባቸው ምክረ ሐሳቦች ትግበራ የድርጊት መርኃ ግብር ያዘጋጁ ሲሆን በፖሊስ ጣቢያዎች እና በማረሚያ ቤት የታዩ የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ክፍተቶች እንዲሻሻሉ ተግባራዊ እርምጃዎችን እንደሚወስዱ ገልጸዋል።

በዳሳ ለሜሳ፣ የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ የሪጅን ዳይሬክተር

የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ የሪጅን ዳይሬክተር በዳሳ ለሜሳ በክትትሉ የተለዩ መልካም አፈጻጸሞችን በማስቀጠል እና ክፍተቶች በታዩባቸው ጉዳዮች ላይ በኢሰመኮ ምክረ ሐሳቦች መሠረት እርምጃዎችን በመውሰድ በክልሉ ሁሉም ፖሊስ ጣቢያዎችና ማረሚያ ቤቶች የተሻለ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታን ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፤ “ለዚህም የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሠራር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት” ብለዋል።