ማብራርያ
ሴሬብራል ፓልዚ እና ሰብአዊ መብቶች
ጥቅምት 6 ዓለም አቀፍ የሴሬብራል ፓልዚ ቀን ሆኖ ይታወሳል፡፡ የዚህ ዓመት የሴሬብራል ፓልዚ ቀን መሪ ቃል “በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ምክንያቶች” ሲሆን በዓለማችን ላይ የሚገኙት 17 ሚሊዮን ከሴሬብራል ፓልዚ ጋር የሚኖሩ ሰዎችን በማሰብ ተከብሮ ውሏል፡፡ ይህ የኢሰመኮ ገላጭ ጽሑፍ ሴሬብራል ፓልዚ ላይ ግንዛቤን ለመፍጠር ይረዳል፡፡
ሴሬብራል ፓልዚ ምንድን ነው?
ሴሬብራል ፓልዚ በልጆች ላይ ከሚደርሱ የተለመዱ የአካል ጉዳቶች አንዱ እና እስካሁን ድረስ ዘላቂ ፈውስ ያልተገኘለት በመሆኑ በአንድ ሰው ሙሉ የሕይወት ዘመን የሚኖር የአካል ጉዳት ነው። ሴሬብራል ፓልዚ ባልተለመደ የአንጎል እድገት ወይም በእድገት ላይ ባለው አንጎል ላይ በሚደርስ ጉዳት ጡንቻን የመቆጣጠር ችሎታን የሚጎዳ የአካል ጉዳት አይነት ነው። ሴሬብራል ማለት ከአንጎል ጋር ግንኙነት ያለው ማለት ሲሆን ፓልዚ ማለት በጡንቻዎች አጠቃቀም ላይ የሚኖር ድክመት ወይም ችግር ማለት ነው፡፡ ሴሬብራል ፓልዚ ጡንቻን የማዘዝ አቅም ላይ ተጽዕኖ የሚያደርስ ሲሆን በጡንቻ እንቅስቃሴ፣ ሚዛን በመጠበቅ፣ ቅንጅት እና አቀማመጥ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። እነዚህ የሴሬብራል ፓልዚ ዋና ዋና መገለጫዎች ናቸው። ከሴሬብራል ፓልዚ ጋር የሚኖሩ ሰዎች ላይ እንደ መናድ (የሚጥል ሕመም) እና የአእምሮ እድገት ውስንነት ያሉ ተጓዳኝ ሁኔታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ። በተጨማሪም ከሴሬብራል ፓልዚ ጋር አብረው ሊከሰቱ የሚችሉ፤ ከክስተቱ ጋር የማይገናኙ የማየት፣ የመስማት፣ የንግግር እና ሌሎች እክሎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ሴሬብራል ፓልዚ በልጅነት ጊዜ የሚከሰት የእንቅስቃሴ ጉዳት ነው። የአንጎል ጉዳቱ አንጎል በእድገት ላይ ባለበት ወቅት፣ ልጅ ከመወለዱ በፊት (በእርግዝና ወቅት)፣ በሚወለድበት ወቅት እንዲሁም ወድያው ከተወለደ በኋላ በሚከሰት የአንጎል መጎዳት ወይም የተዛባ የአንጎል እድገት ይከሰታል፡፡ ምንም እንኳን መከሰቱ የሚታወቀው ከወራት ወይም ከዓመታት በኋላ ቢሆንም አብዛኞቹ ሕፃናት ከጉዳቱ ጋር የተወለዱ ናቸው፡፡
የሴሬብራል ፓልዚ መንስዔዎች እና ተጋላጭነትን የሚጨምሩ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
የሴሬብራል ፓልዚ የተለመዱ ምክንያቶች የሚከተሉትን ያካትታሉ፡-
- የዘረመል መዛባት እና ያልተለመደ የአንጎል እድገት
- እንደ ማጅራት ገትር ያሉ በእርግዝና ወቅት የሚከሰቱ የባክቴሪያ እና የቫይረስ ኢንፌክሽኖች
- በአንጎል ውስጥ የደም መፍሰስ
- በወሊድ ጊዜ ወይም ሕፃናት ከተወለዱ በጥቂት ዓመታት ውስጥ የተከሰተ የጭንቅላት ጉዳት
- በእርግዝና፣ በወሊድ እንዲሁም ከወሊድ በኋላ የተከሰተ የአንጎል ውስጥ የኦክስጅን እጥረት
- በወሊድ ጊዜ በሚከሰት የሕክምና ስሕተት ወይም ቸልተኝነት ሊሆን ይችላል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ የሴሬብራል ፓልዚ ሁኔታ ምን ይመስላል?
ምንም እንኳን የተጠናቀረ ሀገራዊ መረጃ ባይኖርም በርካታ ቁጥር ያላቸው ከሴሬብራል ፓልዚ ጋር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በገጠርና በከተማ መኖራቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ፡፡ በማኅበረሰባችን በአጠቃላይ በአካል ጉዳት ዙሪያ ያለው አሉታዊ አመለካከት እንዲሁም በተለየ ሁኔታ በሴሬብራል ፓልዚ ዙሪያ ያሉ ሥር የሰደዱና የተሳሳቱ አመለካከቶች የዚህን የማኅበረሰብ ክፍል እንደ እኩል ዜጋ መቆጠር ጥያቄ ውስጥ በመክተት የሚያስፈልጋቸውን ልዩ ድጋፍ እንዳያገኙ እና በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ እንዲገደብ አድርጓል፡፡ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በሴሬብራል ፓልዚ ዙሪያ በተደረገ ጥናት መሠረት ሴሬብራል ፓልዚ በልጆች ላይ በከፍተኛ ደረጃ የሚስተዋል መሆኑን እና አብዛኞቹ ታካሚዎች በሪፈራል ከገጠር ወደ ከተማ እንደሚመጡ የሚያመለክት ሲሆን፤ በሴሬብራል ፓልዚ ዙሪያ የግንዛቤ እጥረት በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ይስተዋላል፡፡
በሴሬብራል ፓልዚ እና በሰብአዊ መብቶች መካከል ያለው ግንኙነት ምንድነው?
ከሴሬብራል ፓልዚ ጋር የሚኖሩ ሕፃናት እና አካለ መጠን የደረሱ ሰዎች ካለባቸው የጉዳት ሁኔታ አንጻር ከፍተኛ የሆነ መድልዎ እና መገለል የሚገጥማቸውና የሚያስፈልጋቸውን እንክብካቤና ድጋፍም የማያገኙ ናቸው፡፡ ከሴሬብራል ፓልዚ ጋር የሚኖሩ ሰዎች እና ወላጆቻቸው ወይም አሳዳጊዎቻቸው እንዲሁም ቤተሰቦቻቸው መድልዎ እና ማኅበራዊ መገለል ይደርስባቸዋል። በአብዛኛው ከሴሬብራል ፓልዚ ጋር የሚኖሩ ሰዎች የትምህርትና የጤና አገልግሎቶችን ጨምሮ እጅጉን ከሚያስፈልጉ ሕዝባዊ አገልግሎቶች የተገለሉ ናቸው፡፡
አጋዥ መሣሪያዎች/ቴክኖሎጂዎች ከሴሬብራል ፓልዚ ጋር የሚኖሩ ሰዎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቻቸውን ለማከናወን እና በማኅበረሰብ ውስጥ በንቃት እና በብቃት ለመሳተፍ የሚረዷቸው መሣሪያዎች ናቸው፡፡ አጋዥ መሣሪያ/ቴክኖሎጂ የሚለው ቃል አካል ጉዳተኛ የሆነን ግለሰብ ተግባር ለመደገፍ ወይም ለማሳለጥ የሚያገለግልን ማንኛውንም ዕቃ ወይም ሥርዓት ይገልጻል፡፡ ሴሬብራል ፓልዚ የሚያስከትለውን የአካል ጉዳት ከግምት ውስጥ በማስገባት የተለያዩ አጋዥ መሣሪያዎች/የቴክኖሎጂ ዓይነቶች ጥቅም ላይ የሚውሉ ሲሆን የመንቀሳቀስ፣ የመግባባት፣ የእይታ፣ የመስማት እና የአካባቢ ቴክኖሎጂዎችን ያካትታሉ፡፡
የአጋዥ ቴክኖሎጂ ተደራሽነት የጤና፣ የትምህርትና የሥራ ተደራሽነትን እንዲሁም በማኅበረሰብ ውስጥ መሳተፍን ጨምሮ ውጤታማ የሆነ ማኅበራዊ ሕይወት ለመምራት የሚያስችል የአካል ጉዳተኞች መሠረታዊ የሰብአዊ መብት ነው። አጋዥ ቴክኖሎጂዎች የአካል ጉዳተኞችን ተካታችነት በማረጋገጥ እና የማኅበረሰብን ውህደት በማፋጠን ከፍተኛ ሚና አላቸው። ስለሆነም ሴሬብራል ፓልዚ ላለባቸው ሰዎች አጋዥ መሣሪያዎች፣ ሕክምናዎች እና መድሃኒቶች እኩል ዕድሎችን ለመስጠት እና ከሌሎች ጋር ምሉዕ እና እኩል የሆነ የሰብአዊ መብቶች ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ቅድመ ሁኔታዎች ናቸው (ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት፣ አንቀጽ 41/ሰ)፡፡
ከሴሬብራል ፓልዚ ጋር የሚኖሩ ሰዎች ሰብአዊ መብቶቻቸውን ሙሉ ለሙሉ እንዲጠቀሙ ከባቢያዊ፣ የአመለካከት፣ የተግባቦት እና ተቋማዊ ዕንቅፋቶችን ማስወገድ የግድ ነው፡፡ በዚህም መሠረት መንግሥት የዓለም አቀፉ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነትን የተቀበለ እንደመሆኑ መጠን ከሴሬብራል ፓልዚ ጋር የሚኖሩ ሰዎች ነጻነትን በከፍተኛ መጠን እንዲጎናፀፉ፣ ምሉዕ የሆነ አካላዊ፣ አእምሯዊ፣ ማኅበራዊ እና ሞያዊ ችሎታን እንዲያዳብሩ፣ እንዲሁም በሁሉም የሕይወት ገጽታ ምሉዕ ተሳትፎና ተካታችነታቸው እንዲረጋገጥ የመሪነት ሚና መጫወት አለበት (ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት፣ አንቀጽ 26)፡፡
በተጨማሪም ባለድርሻ አካላት የሆኑ ሁሉም መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በሴሬብራል ፓልዚ ዙሪያ በማኅበረሰቡ ውስጥ ሠርጾ ያለውን የተሳሳተ አመለካከት ለማስተካከል የሚያስችል ተገቢውን የግንዛቤ ማስጨበጫ እንቅስቃሴን ማድረግ የሚጠበቅባቸው ሲሆን ማኅበረሰቡን በስፋት ከመድረስ አንጻር የመገናኛ ብዙኃን ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ ይገባል፡፡