የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በሶማሊ ክልል ያለውን አጠቃላይ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ በተመለከተ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጋር ጥቅምት 10 ቀን 2018 ዓ.ም. በጅግጅጋ ከተማ ውይይት ማካሄዱ ይታወሳል። በውይይቱ ኢሰመኮ በክልሉ ያለውን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ በተመለከተ በተለያየ ጊዜ ባካሄዳቸው ክትትሎች የደረሰባቸውን ግኝቶች በማቅረብ መልካም እመርታዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እና አሳሳቢ ጉዳዮች የእርምት እርምጃ እንዲወሰድባቸው አሳስቧል። በተለይም በማረሚያ ቤቶች እና በፖሊስ ጣቢያዎች በሕግ ጥበቃ ሥር ያሉ ሰዎች የሰብአዊ መብቶች አያያዝ እና የፍትሕ ተደራሽነት እንዲሻሻል ለማድረግ የሚያስችሉ እርምጃዎች እንዲወሰዱ እንዲሁም የተራዘመ የቅድመ ክስ እስራት ሁኔታ እንዲታረም ለተፋጠነና የተሟላ ፍትሕ አሰጣጥ በቂ ትኩረት እንዲሰጥ ኢሰመኮ ምክረ ሐሳብ አቅርቧል።

የሶማሊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር ክቡር ሙስጠፋ መሀመድ በውይይቱ ላይ ኢሰመኮ በዝርዝር ያነሳቸው አሳሳቢ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮችን እልባት ለመስጠት በተለይም የተራዘመ የቅድመ ክስ እስራትን በማስቀረት የተፋጠነ ፍትሕ ሥርዓትን ለመተግበር የክልሉ መንግሥት በልዩ ትኩረት አንደሚሠራ እና ክትትል እንደሚያደርግ በገቡት ቃል መሠረት ክልሉ አበረታች ተግባራዊ እርምጃዎችን መውሰድ መጀመሩን ኢሰመኮ ለማረጋገጥ ችሏል። በዚሁ መሠረት በክልሉ በተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች ከሕግ አግባብ ውጪ ታስረው የነበሩ በአጠቃላይ 121 ሰዎች ከእስር መለቀቃቸውን እንዲሁም ሌሎች ትኩረት የሚፈልጉ አሳሳቢ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮችን ለማስተካከል ክልሉ ጥረቶችን በማድረግ ላይ መሆኑን ለመገንዘብ ችሏል። በተጨማሪም ክልሉ ተፈርዶባቸው በማረሚያ ቤቶች የነበሩ 2 ጋዜጠኞችን በይቅርታ መልቀቁን ኢሰመኮ አረጋግጧል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ የሶማሊ ክልል በአጭር ጊዜ ውስጥ ለወሰዳቸው አበረታች የምክረ ሐሳቦች አፈጻጸም እርምጃዎች ዕውቅና ሰጥተው፣ ተግባሩ በሌሎች ክልሎችም በአርዓያነት ሊወሰድ የሚገባው መሆኑን ገልጸዋል። ክልሉ ሌሎች አሳሳቢ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮችን መፍትሔ ለመስጠት የጀመራቸውን ጥረቶች እንዲያጠናክር አሳስበው፣ ኢሰመኮ በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታን ለማሻሻል በክልሎች ደረጃ የሚያደርጋቸውን የውትወታና የምክረ ሐሳቦች አፈጻጸም ክትትል ሥራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።