የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በሶማሊ ክልል ያለውን አጠቃላይ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ በተመለከተ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጋር ጥቅምት 10 ቀን 2018 ዓ.ም. በጅግጅጋ ከተማ ውይይት አካሂዷል። ውይይቱ ኢሰመኮ በክልሉ ያለውን የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ በተመለከተ በተለያየ ጊዜ ባካሄዳቸው ክትትሎች የደረሰባቸውን ግኝቶች በማቅረብ መልካም እመርታዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እና አሳሳቢ ጉዳዮች የእርምት እርምጃ እንዲወሰድባቸው ለማሳሰብ ያለመ የኢሰመኮ የውትወታ ተግባር አካል ነው። በውይይቱ ኢሰመኮ የሶማሊ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር ሙስጠፋ መሀመድን እና የክልሉ ማረሚያ ቤት ኮሚሽነር በሽር አህመድ ሐሺን ጨምሮ ሌሎች የሥራ ኃላፊዎችን አነጋግሯል።




የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ በሶማሊ ክልል ከሀገራዊ ለውጡ በፊት በማረሚያ ቤቶች እና በፖሊስ ጣቢያዎች ሲፈጸሙ የነበሩ ድብደባ እና ሌሎች የማሰቃየት ተግባራት እንዲሁም ስልታዊ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መቅረታቸው፣ ለታራሚዎች ከሌሎች ክልሎች የተሻለ የቀን ፍጆታ በጀት መመደቡ፣ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው በመመለስ እና በማቋቋም ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ጥረቶች መደረጋቸው እና የሽግግር ፍትሕን ተግባራዊ ለማድረግ እርምጃዎች መወሰዳቸው አበረታች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።




በሌላ በኩል ዋና ኮሚሽነሩ በክልሉ ፋፈን እና ጀረር ዞንን በሚያዋስነው ደወአሌይ አካባቢ ተፈጥሮ የነበረው ግጭት ተገቢው ትኩረት እንዲሰጠው እና የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ፈጻሚዎችን በመለየት ተጠያቂነትን የማረጋገጥ እና ተጎጂዎችን የማቋቋም ቀሪ ሥራዎች እንዲከናወኑ፤ በዚህ ረገድ ክልሉ እያደረገ ያለው ጥረት በሚመለከታቸው የፌዴራል መንግሥት አካላት እንዲደገፍ፤ በማረሚያ ቤቶች እና በፖሊስ ጣቢያዎች በሕግ ጥበቃ ሥር ያሉ ሰዎች የሰብአዊ መብቶች አያያዝ እና የፍትሕ ተደራሽነት እንዲሻሻል ለማድረግ የሚያስችሉ እርምጃዎች እንዲወሰዱ እንዲሁም የተራዘመ የቅድመ ክስ እስራት ሁኔታ እንዲታረም ለተፋጠነና የተሟላ ፍትሕ አሰጣጥ በቂ ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል።



የሶማሊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር ክቡር ሙስጠፋ መሀመድ ኢሰመኮ በዝርዝር ያነሳቸው የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮችን በበጎ የሚመለከቷቸው መሆናቸውን ገልጸው፣ የተራዘመ ቅድመ ክስ እስራትን በማስቀረት የተፋጠነ ፍትሕ ሥርዓትን ለመተግበር የክልሉ መንግሥት በልዩ ትኩረት አንደሚሠራ እና ክትትል እንደሚያደርግ ጠቁመዋል። በሽግግር ፍትሕ ላይ የተጀመረውን ሥራ እንዲሁም በሰብአዊ መብቶች ጽንሰ ሐሳቦችና ጥበቃ ዙሪያ ያሉ የግንዛቤና የአሠራር ክፍተቶችን ለመሙላት ከኢሰመኮ ጋር የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል። አክለውም በክልሉ ውስጥ እና በአጎራባች ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ለሚፈጠሩ ችግሮች ሰላማዊ መፍትሔ በማፈላለግ ተጨማሪ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ለመከላከል የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን በማንሳት፤ ችግሮቹ ዘላቂ መፍትሔ እስከሚያገኙ ድረስ የክልሉ መንግሥት በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል።


የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታውን ለማሻሻል ኢሰመኮ ከክልሎች ጋር የሚያደርገውን የውትወታ ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተው፤ “በክልሉ ከታራሚዎቸ አያያዝ፣ ከሽግግር ፍትሕ ቅድመ ትግበራ እና የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ሰለባዎችን ከመካስ አንጻር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት የሚበረታቱ እና በምሳሌነት የሚጠቀሱ ናቸው” ብለዋል።