Skip to content
Facebook XYouTube Linkedin Flicker TikTok Instagram WhatsApp Telegram
Ethiopian Human Rights Commission – EHRC
  • About
    • Who We Are
    • Our Team
    • Careers
    • Contact Us
  • Regions
        • Regions

          EHRC is an independent federal institution tasked with the promotion and protection of human rights in Ethiopia.

        • Addis Ababa
        • Afar
        • Amhara
        • Benishangul Gumuz
        • Gambella
        • Oromia
        • Somali
        • Tigray
        • Central Ethiopia
        • Dire Dawa
        • Harari
        • Sidama
        • South Ethiopia
        • South West Ethiopia Peoples'
  • Areas of Work
        • Areas of Work

          We are an independent national human rights institution tasked with the promotion & protection of human rights in Ethiopia.

        • Economic, Social & Cultural Rights
        • Civil & Political Rights
        • IDPs, Refugees & Migrants’ Rights
        • Rights of Persons with Disabilities & the Rights of Older Persons
        • Women’s & Children’s Rights
        • Human Rights Education
        • Human Rights Monitoring & Investigation
        • Human Rights Film Festival
        • Human Rights Moot Court Competition
  • Press Releases
  • Reports
  • Media
    • EHRC on the News
    • EHRC Newsletters
    • EHRC Videos
    • EHRC Visuals
  • Latest
    • Expert Views
    • Explainers
    • Event Updates
    • Annual Ethiopia Human Rights Situation Reports
  • Resources
 
Ethiopian Human Rights Commission – EHRCEthiopian Human Rights Commission – EHRC

ሶማሌ ክልል፡ በቦምባስ ከተማ በአኪሾ ጎሳ አባላት ባሕላዊ ሥነ ሥርዓት ላይ በክልሉ መንግሥት የፀጥታ አካላት የተወሰደ መጠን ያለፈ የኃይል አጠቃቀም ለሞትና የአካል ጉዳት ምክንያት ሆኗል

May 12, 2022October 5, 2022 Press Release, Report

የክልሉ መንግሥት ለሟች ቤተሰቦች እና የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ካሳ የከፈለ ቢሆንም ለተሟላ ፍትሕ የወንጀል ተጠያቂነት ሊረጋገጥ ይገባል

Twitter Facebook Telegram Email Whatsapp Print

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በሶማሌ ክልል ፋፈን ዞን ጉርሱም ወረዳ ቦምባስ ከተማ መጋቢት 11 እና 12 ቀን 2014 ዓ.ም. በባሕላዊ ሥነ ሥርዓት የጎሳ መሪ (ሱልጣን) ለመምረጥ በተሰበሰቡ ሰዎች ላይ ግድያ እና የአካል ጉዳት ስለመፈጸሙ በደረሰው ጥቆማ መነሻነት ከሚያዝያ 7 እስከ 12 ቀን 2014 ዓ.ም. በቦታው በመገኘት ምርመራ አድርጓል። በዚህም መሰረት በአጠቃላይ በሁለቱ ቀናት በክልሉ ፀጥታ ኃይሎች እና በታጠቁ ግለሰቦች በተፈጸሙ ጥቃቶች 11 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ ይኸውም በታጠቁ ሰዎች የተፈጸመ ግድያ እና በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ከመጠን ያለፈ የኃይል አጠቃቀም (excessive use of lethal force) የደረሰ የሕይወት መጥፋት መሆኑን፤ በተጨማሪም ቢያንስ በ33 ሰዎች ላይ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን ኮሚሽኑ በምክንያታዊ ሁኔታ አሳማኝ (reasonable ground to believe) ሆኖ አግኝቶታል፡፡

ኮሚሽኑ ምርመራውን ለማከናወን የአይን ምስክሮችን፣ ተጎጂዎችን፣ የተጎጂ ቤተሰቦችን እና የሀገር ሽማግሌዎችን በግል እና በቡድን በማነጋገር፣ ከሆስፒታል ምንጮች መረጃ በማሰባሰብ እንዲሁም ስለጉዳዩ ማብራሪያና ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ የሆኑ የክልሉ ኃላፊዎችን በማነጋገር ምርመራውን አካሂዷል። የአካል ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎች መካከል በቡሽማን ቀበሌ 7 ተጎጂዎችን በቤታቸው፣ እንዲሁም በጅግጅጋ አጠቃላይ ሆስፒታል በመገኘት በመታከም ላይ የነበሩ 5 ተጎጂዎችን በማነጋገር እና ምልከታ በማድረግም ማስረጃ አሰባስቧል፡፡ 

በተጨማሪም ቦምባስ ከተማ የሚገኝ የጥቃቱ ሰለባዎች የተቀበሩበትን የመቃብር ስፍራ የጎበኘ ሲሆን፣ በዚህም በመጀመሪያ ቀን ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች የተቀበሩበት አንድ የጅምላ መቃብር እና በሁለተኛው ቀን የተገደለች ሴት የተቀበረችበት መሆኑ የተገለጸ ለብቻው ያለ አንድ ሌላ የመቃብር ቦታ ተመልክቷል፡፡

ከክልሉ የመንግሥት አካላት የክልሉ ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት እና የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኢሰመኮን ያነጋገሩ ሲሆን፣ የክልሉ ልዩ ኃይል፣ የክልሉ የፀጥታ ቢሮ እና የጉርሱም ወረዳ አስተዳደርን ለማግኘት የተደረገው ተደጋጋሚ ጥረት ባለመሳካቱ ምላሻቸውን ማካተት አልተቻለም። 

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ የክልሉ መንገግሥት በፀጥታ ኃይሎች የተፈጸመው ግድያ ፈጽሞ ተገቢ እንዳልነበር በመገንዘብ ለተጎጂዎችና ቤተሰቦች ካሳ እንዲከፈል ማድረጉ ጥሩ እርምጃ መሆኑን አስታወስው፤ “ከዚህ በተጨማሪ የተሟላ ፍትሕ ለማረጋገጥና ለወደፊትም ተመሳሳይ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እንዳይከሰቱ ለመከላከል የወንጀል ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ይገባል፤ ስለሆነም በአፋጣኝ የወንጀል ምርመራ ሊጀመር ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡


ስለ ጉዳዩ ዝርዝር መረጃዎች፣ የምርመራው ሂደት እና ግኝቶች ከዚህ በታች ይመለከቱ፡፡

ስለአካባቢው ባሕላዊ ልማድ አጭር መግቢያ 

በሶማሌ ክልል ከሚገኙ የተለያዩ የሶማሌ ጎሳዎች መካከል አንዱ የአኪሾ ጎሳ ነው፡፡ የአኪሾ ጎሳ ማኅበረሰብ አባላት በተለያዩ የክልሉ አከባቢዎች ይኖራሉ፡፡ ከእነዚህ አከባቢዎች መካከል አንዱ የፋፈን ዞን ጉርሱም ወረዳ ነው፡፡ የጉርሱም ወረዳ ዋና ከተማ ቦምባስ ሲሆን፣ ከክልሉ ዋና ከተማ 50 ኪ.ሜ. ያህል ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ በጉርሱም ወረዳ ቡሽማን ቀበሌ ውስጥ የሚኖሩ የአኪሾ ጎሳ አባላት ከዚህ ቀደም በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሀረርጌ ዞን፣ ጉርሱም ወረዳ ስር ይተዳደሩ የነበሩ ቢሆንም፣ በ2011 ዓ.ም. በሁለቱ ክልሎች መካከል በተደረገ ስምምነት በሶማሌ ክልል ስር ወደሚገኘው ጉርሱም ወረዳ ተጠቃለዋል፡፡ 

በተለምዶ በሶማሌ ክልል የሚገኙ አብዛኛዎቹ ጎሳዎች የየራሳቸው ሱልጣን (የጎሳ መሪ) አላቸው።በጉርሱም ወረዳ የሚገኙት የአኪሾ ጎሳ ማኅበረሰብ አባላት በ2013 ዓ.ም. የራሳቸውን የጎሳ መሪ ለመምረጥ ፈልገው በመከልከሉ ምክንያት በተፈጠረ አለመግባባት በሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ደርሶ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ በዚህም ምክንያት በወረዳው የሚኖሩ የጎሳው አባላት በወረ ሁሜ ሱልጣን ሥርዓት ስር ተጠቃለው የቆዩ መሆኑን፣ ሆኖም አሁንም ከወረ ሁሜ ሱልጣን ስር በመውጣት የራሳቸውን ሱልጣን ለመምረጥ የሚፈልጉ መሆኑን ኮሚሽኑ ያነጋገራቸው የማኅበረሰቡ የሀገር ሽማግሌዎች ይገልጻሉ። 

የአሁኑ ግጭት መነሻ 

በጉርሱም ወረዳ የሚገኙ የአኪሾ ጎሳ አባላት የራሳቸውን የጎሳ መሪ ለመምረጥ የምርጫ ሥነ-ሥርዓት ማዘጋጀት እንደሚፈልጉ ለጉርሱም ወረዳ አስተዳዳር ማሳወቃቸውን ገልጸዋል። የወረዳ አስተዳደሩም የአኪሾ ጎሳ በወረ ሁሜ ሥርዓት ስር የሚተዳደር በመሆኑ አዲስ መሪ መምረጥ አያስፈልግም በሚል ምክንያት ዝግጅቱ እንዳይደረግ በመከልከሉ፤ የጎሳ አባላቱ ጉዳዩን ለፋፈን ዞን፣ እንዲሁም ለክልሉ መንግሥት ፕሬዝዳንት ቢሮ እና ለፀጥታ ቢሮ እንዳሳወቁ ተገልጿል። ኢሰመኮ ያነጋገራቸው የጎሳው ሽማግሌዎች የክልሉ የፀጥታ ቢሮ ኃላፊ “ይህን ማከናወን መብታችሁ በመሆኑ እዚህ መምጣትም አይጠበቅባችሁም ነበር” የሚል ምላሽ እንደሰጣቸውና በ20 ቀናት ውስጥ ምርጫውን ማካሄድ የሚችሉ መሆኑን እንደነገራቸው አብራርተዋል፡፡

በሌላ በኩል የወረ ሁሜ ሱልጣን የተወሰኑ የአኪሾ ጎሳ አባላት አቤቱታቸውን ለወረዳው አስተዳዳሪ፤ ለፋፈን ዞን አስተዳደር ፣ ለክልል መስተዳደር ጽሕፈት ቤት እና ለክልሉ ፀጥታ ቢሮ አቅርበው እነዚህ የአስተዳደር አካላት “ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርባችሁ በወረ ሁሜ ሕግ አልተፈቀደላችሁም፣ ስለዚህ የጎሳው መሪ ጋር ሂዱ” የሚል ምላሽ ተሰጥተዋቸዋል ብለዋል፡፡ አክለውም የአኪሾ ጎሳ አባላት ወደ እርሳቸው መጥተው እንደነበርና “በወረ ሁሜ ባሕላዊ ሕግ መሰረት ሌላ ሱልጣን መምረጥ እንደማይችሉ በመግለጽ” እንደመለሷቸው ገልጸዋል፡፡ ሆኖም የጎሳው አባላት የራሳቸውን ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅታቸውን መቀጠላቸውና ለባሕላዊ ሥነ ሥርዓቱ ድግስ ግመሎችን እና ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ የምግብ ግብዓቶችን በማዘጋጀት ጭምር ለምርጫ የተያዘውን ቀን ሲጠባበቁ እንደነበር ለመረዳት ተችሏል፡፡

በሌላ በኩል የአኪሾ ጎሳ አባላት ቀደም ሲል ምርጫውን እንዲያከናወኑ የፈቀደላቸው የፀጥታ ቢሮ ኃላፊ በሥራ ቦታ ባልነበሩበት ወቅት ወክሎት የሄደው የቢሮው ምክትል ኃላፊ መሆኑ የተጠቀሰ ግለሰብ፣ ከዋናው የቢሮው ኃላፊ በተቃራኒ ምርጫውን ማድረግ እንደማይችሉ እንደነገራቸውና ጉዳዩን በወረሁሜ ሥርዓት መሰረት ብቻ መፍታት እንዳለባቸው የገለጸላቸው መሆኑን ገልጸው፣ ሆኖም ግን የጎሳ አባላቱ ዝግጅቱን መሰረዝ ወይም ማስተላለፍ እንደማይችሉ ለመንግሥት ኃላፊዎች መናገራቸውን ለኢሰመኮ አስረድተዋል። 

ስለሆነም የአኪሾ ጎሳ አባላት ባሕላዊ ሥነ ሥርዓት ባለመግባባትና በተቃርኖ አስተያየት እልባት ሳያገኝ ቀኑ እየተቃረበ መምጣቱና ለግጭት መነሻ ምክንያት መሆኑን ኮሚሽኑ ተገንዝቧል፡፡

የምርጫው ቀን ከመድረሱ 4 ቀናት ቀደም ብሎ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አባላት ቦምባስ ከተማ በመግባት ጥበቃ ሲያደርጉ እንደነበረ እና ከልዩ ኃይሉ ውጪ ሌላ የፀጥታ ኃይል በከተማው ውስጥ ያልነበረ መሆኑን ኢሰመኮ ያነጋገራቸው የአይን እማኞች ተናግረዋል፡፡

የአኪሾ ጎሳ መሪ ምርጫ ዕለት

መጋቢት 11 ቀን 2014 ዓ.ም. በግምት ከጠዋቱ 1፡00 ሰዓት አካባቢ ቦምባስ ከተማ ቀበሌ 02 ዋና መንገድ ላይ ቀደም ሲል በተያዘው ቀጠሮ መሰረት የጎሳውን ሱልጣን ለመምረጥ ቁጥራቸው በግምት እስከ 4ሺህ የሚደርሱ የአኪሾ ጎሳ ተወላጆች ተሰበሰቡ፡፡ የጎሳ መሪውን ለመምረጥ ከተሰበሰቡት ሰዎች መካከል የጎሳው ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች እና ሕፃናት እንደሚገኙበት በዕለቱ በቦታው የነበሩ የአይን እማኞች ጨምረው አስረድተዋል፡፡

ዝግጅቱ ከተጀመረ ከጥቂት ቆይታ በኋላ በግምት ከጠዋቱ 2፡00 ሰዓት አካባቢ ሲሆን፣ የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት ወደ ስብሰባው ቦታ መጥተው “የጎሳ አባላቱ ስብሰባውን አቋርጠው ይበተኑ” በማለታቸው አለመግባባት እንደተፈጠረ ለመረዳት ተችሏል፡፡ በስፍራው የነበሩ ምስክር ስለሁኔታው ሲያስረዱ “በቦታው የተገኘ የልዩ ኃይል አዛዥ እኛ የተሰበሰብንበት ቦታ በመምጣት ከዚህ ቦታ ትነሳላችሁ ወይስ አትነሱም?” ብሎ ሲጠይቅ ‘የመጣነው የጎሳ መሪያችንን ለመምረጥ ስለሆነ አንነሳም’ በማለት ምላሽ ሰጥተናል” ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ሌሎች በአካባቢው የነበሩ የአይን እማኞች እና ተጎጂዎችም ይህንኑ ያረጋገጡ ሲሆን፤ አለመግባባት እንደተፈጠረና የልዩ ኃይል አዛዡ በአካባቢው ለነበሩ የልዩ ኃይል ፖሊስ አባላት ትዕዛዝ በመስጠቱ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል የደንብ ልብስ የለበሱና መሳሪያ የታጠቁ ወታደሮች “በግምት እስከ 5 ሜትር ርቀት ላይ በመሆን በቀጥታ ወደ ሕዝቡ ጥይት መተኮስ ጀመሩ” በማለት አስረድተዋል፡፡ አንድ ምስክር የነበረውን ሁኔታ ሲገልጽ “በቀጥታ ወደ ሕዝቡ ነው የተኮሱት፤ ጦርነት ውስጥ የገባን ነበር የሚመስለው” ብሏል፡፡ 

በሌላ በኩል የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ለኢሰመኮ ሲያስረዱ፤ “ተሰብሳቢዎቹ መንገድ ዘግተውና በብዛት መሳሪያም ታጥቀው ነበር፣ መንገድ ለምን ትዘጋላችሁ በሚል በፖሊስና በተሰብሳቢዎቹ መካከል ግብግብ ተፈጠረ፣ በዚህ መካከል ከተሰብሳቢዎቹ ጥይት መተኮሱንና ኮሎኔል ውሊዮ የተባለ የልዩ ፖሊስ አባል በጥይት ተመታ፣ በዚህም ምክንያት ፖሊሶች ስሜታዊ በመሆን ተመጣጣኝ ሊባል የማይችል እርምጃ ሊወስዱ ችለዋል” በማለት መልስ ሰጥተዋል፡፡ በተጨማሪም ግጭቱ የአድማ በታኝ ፖሊሶችን ወደ ከተማው ለማስገባት በመንቀሳቀስ ላይ እያሉ የተፈጠረ መሆኑን ገልጿል፡፡

በዚህ ሁኔታ በተፈጠረው ሁከትና በልዩ ኃይሉ አባሎች በተተኮሰ ጥይት የዝግጅቱ ታዳሚ ከነበሩት ሰዎች መካከል (1) አብዲረሳቅ ዩሱፍ ኡመር (2) መሐመድ የሬ ሙሀመድ ኡመር (3) አብዲ ኢብራሂም ዩሱፍ (4) ሀሰን አብዲ አው በደል (5) ሙሴ ሙሀመድ ኡመር (6) ኢብራሂም አብዲ ፋራህ (7) አደን አብዲ አብዲላሂ (8) ሀሰን መሐሙድ ሮብሌ የተባሉ በአጠቃላይ 8 ሰዎች ግንባራቸውን እና ሆዳቸውን ላይ በጥይት ተመትተው ወዲያውኑ ለምርጫው በተሰበሰቡበት ቦታ ላይ መሞታቸውን ኢሰመኮ ካነጋገራቸው የሟች ቤተሰቦች እና የአይን እማኞች አረጋግጧል፡፡

በተጨማሪም አብዲአዚዝ መሐመድ እና ኤሊያስ አብዲረዛቅ የተባሉ ሁለት ተጎጂዎች የልዩ ኃይል ፖሊሶች ውስጥ ቁስለኞችን “ደማቸው ፈሶ ይለቅ” በማለት ሕክምና በመከልከላቸው ምክንያት፣ ከወደቁበት ቦታ ሳይነሱ ከቆዩ በኋላ ወደ ጅግጅጋ ከተማ እና ወደ ድሬደዋ ከተማ ለሕክምና የተወሰዱ ቢሆንም፣ በደረሰባቸው ጉዳት ምክንያት ሕይወታቸው ማለፉን የአይን እማኞች ለኮሚሽኑ አስረድተዋል።

ከሞቱት ሰዎች በተጨማሪ 22 ሰዎች በልዩ ኃይል ፖሊስ አባሎች በተተኮሱ ጥይቶች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ተጎጂዎች የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ጠዋት ቢሆንም በፀጥታ ኃይሎች ሕክምና እንዳያገኙ ተከልክለው ሕክምና ያገኙት ከሰዓት በኋላ በግምት ከቀኑ ወደ 10፡00 ሰዓት አካባቢ መሆኑን ከአይን እማኞች፣ ከተጎጂዎች እና ከተጎጂ ቤተሰቦች የተሰበሰቡ ማስረጃዎች ያሳያሉ። 

ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎች መካከል በጥይት ሆዳቸው፣ እጃቸው እና እግራቸው ላይ የተመቱ፣ አጥንታቸው የተሰበሩ ተጎጂዎችን ኮሚሽኑ የተመለከተ ሲሆን፤ ከተጎጂዎች መካከል ሴቶች፣ ሕፃናት እና አረጋውያን ይገኙበታል፡፡ 

የልዩ ኃይል ፖሊሶች ሌሎች ሰዎች አስክሬኖቹን እንዳያነሱ በመከልከልና አንድ ቦታ በመሰብሰብ ከተወሰነ ሰዓት በኋላ በአንድ ላይ በመኪና በመጫን በረካሌ ተብሎ ወደሚጠራ ቀበሌ ወስደው ማስቀመጣቸውን ምስክሮች ገልጸዋል፡፡ ፖሊሶች የሟቾች ቤተሰቦች አስክሬኖቹን በየቀበሌያቸው ወስደው እንዲቀብሩዋቸው ቢያዙም በአኪሾ የጎሳ መሪ አማካኝነት ከፖሊሶቹ ጋር በተደረገው ንግግር አማካኝነት በዛው ዕለት አመሻሽ ላይ አስከሬኖቹን ወደ ቦምባስ ከተማ በመመለስ ሁሉንም በአንድ መቃብር መቅበራቸውን የሟቾች ቤተሰቦች እና የአይን ምስክሮች አስረድተዋል፡፡

የሟቾች ቀብር ሥነ ሥርዓት ዕለት 

የቀብር ሥነ ሥርዓቱ በተከናወነበት መጋቢት 12 ቀን 2014 ዓ.ም. ዕለት የተከሰተውን ሁኔታ የአይን እማኞች ሲያስረዱ የሞቱት የጎሳው አባላትን ለመቅበር ቦምባስ መሄዳቸውንና፤ “ከቀብር በፊት ግን የጎሳ መሪ ምርጫ እየተካሄደ እያለ የታጠቁ ግለሰቦች ተኩስ ከፍተው፤ በጥቃቱም ለተሰብሳቢዎች ምግብ እያዘጋጁ ከነበሩ ሴቶች መካከል ሰአዲያ ኢብራሂም የተባሉ ሴት አረጋዊ ወዲያውኑ ሕይወታቸው ሲያልፍ፣ ሃሊሞ ኑሪዬ የተባለች ሌላ እርጉዝ ሴት የአካል ጉዳት ደርሶባታል” ብለዋል። በተጨማሪም 11 የአኪሾ ጎሳ አባላት በታጠቁት ግለሰቦች በዱላ ተመትተው የተለያየ መጠን ያለው የአካል ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን ምስክሮቹ ጨምረው አስረድተዋል፡፡

አክለውም ድብደባና ግድያ በታጠቁ ግለሰቦች ሲፈጸም የክልሉ ልዩ ፖሊስ እና አድማ በታኝ ኃይል በአካባቢው የነበሩ ቢሆንም፣ ድርጊቱን ለመከላከልም ሆነ ድርጊቱ ከተፈጸመ በኋላ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ ያደረጉት ጥረት የለም ብለዋል። ከላይ ከተጠቀሱ የፀጥታ አካላት በተጨማሪ ጥቃቱ ሲፈጸም የክልሉ የፀጥታ ቢሮ ኃላፊ በቦታው የነበሩና የጎሳ መሪ ምርጫን አስመልክቶ ንግግር ያደረጉ መሆኑን፤ በንግግራቸውም “ምርጫው መብታችሁ ነው እንኳን መረጣችሁ” ማለታቸውን፤ ነገር ግን ስለተገደሉት ሰዎች ምንም የተነገረ ጉዳይ አለመኖሩን ኮሚሽኑ ያነጋገራቸው የአይን ምስክሮች አስረድተዋል፡፡ 

የክልሉ መንግሥት ምላሽ

ከዚህ በላይ እንደተገለጸው የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ስለ ጉዳዩ በሰጠው ምላሽ ተሰብሳቢዎቹ መንገድ ዘግተው፣ መሳሪያም ታጥቀው እንደነበር፣ “መንገድ ለምን ትዘጋላችሁ?” በሚል በፖሊስና በተሰብሳቢዎቹ መካከል በተፈጠረ ግብግብ ከተሰብሳቢዎቹ መካከል ጥይት መተኮሱንና አንድ የልዩ ፖሊስ አባል በጥይት መመታቱን፣ በዚህም ፖሊሶች ስሜታዊ በመሆን ተመጣጣኝ ሊባል የማይችል እርምጃ መውሰዳቸውን ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪም ግጭቱ የተከሰተውና ጉዳቱ የደረሰው የአድማ በታኝ ፖሊሶችን ወደ ከተማው ለማስገባት በመንቀሳቀስ ላይ እያሉ፤ የአድማ በታኝ ፖሊሶች በስፍራው ከመድረሳቸው በፊት መሆኑን ገልጿል፡፡ 

በሌላ በኩል ኮሚሽኑ ያነጋገራቸው የአኪሾ ጎሳ አባላት ውስጥ “ድርጊቱ ሆነ ተብሎ የተፈጸመ ነው፣ እኛ የጦር መሳሪያ አልያዝንም፤ ከጥቃቱ በኋላም የብዙ ሰው ቤት ተፈትሿል፤ ነገር ግን የተገኘ የጦር መሳሪያ የለም” በማለት ለኢሰመኮ ገልጸዋል፡፡ ስለሆነም በልዩ ኃይል ፖሊሶች የተወሰደው የኃይል እርምጃ ተመጣጣኝ አለመሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ድርጊቱ እና የተጠያቂነት መጠኑ በተሟላ የወንጀል ምርመራ ሊጣራ የሚገባው ነው፡፡

የክልሉ ልዩ ኃይል፣ የክልሉ የፀጥታ ቢሮ እና የጉርሱም ወረዳ አስተዳደርን ለማግኘት የተደረገው ተደጋጋሚ ጥረት ባለመሳካቱ ምላሻቸውን ለማካተት አልተቻለም፡፡ ኢሰመኮ መጋቢት 27 ቀን 2014 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ ቁጥር HRCJB/08/339/2014 ለክልሉ መንግሥት ደብዳቤ የጻፈ ቢሆንም ይህ ሪፖርት ይፋ እስከተደረገበት እለት ድረስ ከክልሉ መንግሥት ቢሮዎች የጽሑፍ ምላሽ አልተሰጠም። በተጨማሪም ከተሰብሳቢዎች በተተኮሰ ጥይት ጉዳት የደረሰበትን የልዩ ፖሊስ አባል ለማግኘት እና ለማነጋገር የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ 

በሌላ በኩል የኢሰመኮ ምርመራ መጀመርን ተከትሎ፤ የክልሉ መንግሥት ለሟች ቤተሰቦች እና የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ካሳ የከፈለ መሆኑን አዲሱ የጉርሱም ወረዳ የአኪሾ ጎሳ መሪ በሚያዚያ 18 ቀን 2014 ዓ.ም. ለኮሚሽኑ አረጋግጠዋል፡፡

ምክረ ሃሳብ

በአኪሾ ጎሳ አባላት ላይ ድብደባ፣ የአካል ጉዳት እና የሕይወት መጥፋት ያስከተሉ ሰዎች በሙሉ የአስተዳደርና የፀጥታ አካላትን ጨምሮ ግልጽ የሆነ የወንጀል ምርመራ ተደርጎ የወንጀል ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ እና ለወደፊት ተመሳሳይ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንዳይከሰት ለመከላከል፤ አስፈላጊ የሆኑ አስተዳደራዊ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ኢሰመኮ ያሳስባል፡፡

Related posts

February 2, 2022August 28, 2023 Press Release
ኦሮሚያ ክልል፡ በከረዩ የሚችሌ ገዳ የጅላ አባላት ላይ ግድያ የፈጸሙና ያስፈጸሙ የፀጥታና የአስተዳደር አባላት ላይ ተገቢው የወንጀል ምርመራ ተደርጎ ለፍትሕ ሊቀርቡ ይገባል
August 26, 2021February 12, 2023 Press Release
ምስራቅ ወለጋ፡ የነዋሪዎችን ደኅንነት ለማረጋገጥ የአካባቢው የፀጥታ ኃይል ሊጠናከር ይገባል
January 1, 2021August 28, 2023 Report
ኦሮሚያ ክልል፡ የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ተከስቷል
November 15, 2020February 11, 2023 Press Release
ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፀጥታና ደኅንነትን ለማጠናከር ፈጣንና የተቀናጀ እርምጃ አስፈላጊ ነው

Signup for the Latest Update from EHRC

Submit your email to singup
Facebook Like us on FacebookXFollow us on XYouTube Follow us on YouTubeLinkedin Follow us on LinkedinWhatsApp WhatsAppTikTok TikTokTelegram TelegramInstagram InstagramFlicker Flickr

Useful Links

  • NANHRI
  • GANHRI
  • OHCHR
  • ACHPR
  • TRANSITIONAL JUSTICE

Get Involved

  • Jobs
  • Events
  • Contact Us
  • Telegram Bot
  • Subscribe to our newsletter

Connect with Us

  • Facebook
  • Twitter
  • LinkedIn
  • YouTube
  • Flickr
  • Instagram
Descriptive Text

We are an independent
national human rights
institution tasked with
the promotion and protection of human
rights in Ethiopia.

Submit your email to get the latest update from EHRC

Address: Sunshine Tower No. 5, Meskel Square, on Bole Road next to Hyatt Regency Hotel, Addis Ababa, Ethiopia
Tel: +251115504031 | Fax: +251 11 550 4125 | PO Box 1165 Addis Ababa | Email: info@ehrc.org


The contents of this website, excepting third party content for which the Commission bears no responsibility,
may be freely used and copied for educational and other non-commercial purposes, provided that any such reproduction is accompanied by an acknowledgement of the Ethiopian Human Rights Commission (EHRC). Source of images used in the content of this website: EHRC Media and Communications Department Archive and Creative Common License.

This website is managed by the Media and Communications team of the Ethiopian Human Rights Commission (EHRC).

We are using cookies to give you the best experience on our website.

You can find out more about which cookies we are using or switch them off in .

Scroll to top
  • About
    • Who We Are
    • Our Team
    • Careers
    • Contact Us
  • Regions
    • Addis Ababa
    • Afar
    • Amhara
    • Benishangul Gumuz
    • Central Ethiopia
    • Dire Dawa
    • Gambella
    • Harari
    • Oromia
    • Sidama
    • Somali
    • South Ethiopia
    • South West Ethiopia Peoples’
    • Tigray
  • Areas of Work
    • Economic, Social & Cultural Rights
    • Civil & Political Rights
    • IDPs, Refugees & Migrants’ Rights
    • Rights of Persons with Disabilities & the Rights of Older Persons
    • Human Rights Monitoring & Investigation
    • Women’s & Children’s Rights
    • Human Rights Education
    • Human Rights Film Festival
    • Human Rights Moot Court Competition
  • Press Releases
  • Reports
  • Media
    • EHRC on the News
    • EHRC Newsletters
    • EHRC Videos
    • EHRC Visuals
  • Latest
    • Expert Views
    • Explainers
    • Event Updates
    • Annual Ethiopia Human Rights Situation Reports
  • Resources
Facebook XYouTube Linkedin Flicker TikTok Instagram WhatsApp Telegram
Search
Ethiopian Human Rights Commission - EHRC
Powered by  GDPR Cookie Compliance
Privacy Overview

This website uses cookies so that we can provide you with the best user experience possible. Cookie information is stored in your browser and performs functions such as recognising you when you return to our website and helping our team to understand which sections of the website you find most interesting and useful.

Strictly Necessary Cookies

Strictly Necessary Cookie should be enabled at all times so that we can save your preferences for cookie settings.

If you disable this cookie, we will not be able to save your preferences. This means that every time you visit this website you will need to enable or disable cookies again.