የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ይፋዊ መግለጫ
ሰኔ 9 ቀን 2014 ዓ.ም.
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በየዓመቱ ሰኔ 9 የሚታሰበውን የአፍሪካ ሕፃናትን ቀን በማስመልከት በሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ሕፃናት ላይ የሚፈጸሙ ጎጂ ድርጊቶችን ለማስወገድ የክልልና የፌዴራል መንግሥታት፥ እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ኢትዮጵያ ፈርማ ባጸደቀቻቸው የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች መሰረት ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቀረበ። የአፍሪካ ሕፃናት ቀን በ2014 ዓ.ም. “ሕፃናትን የሚጎዱ ጎጂ ድርጊቶችን ማስወገድ፡ ባለፉት አስርት ዓመታት በፖሊሲ እና በአሠራር የታዩ እምርታዎች” (“Eliminating Harmful Practices Affecting Children: Progress on Policy and Practice since 2013”) በሚል መሪ ቃል ይታሰባል፡፡
ጎጂ ድርጊቶች በአፍሪካ የሕፃናት መብቶች ቻርተር እና በአፍሪካ የሴቶች መብቶች ፕሮቶኮል (Maputo Protocol) አንቀጽ 1 (ተ) መሰረት ያለ ዕድሜ ጋብቻን፥ ጾታዊና ወሲባዊ ጥቃቶችን፤ የጉልበትና ወሲባዊ ብዝበዛን፥ ግርዛትን የሚጨምሩ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በ2012 ዓ.ም. ያጸደቀችው በሀገር ውስጥ የተፈናቀሉ ሰዎችን ለመጠበቅና ድጋፍ ለማድረግ የአፍሪካ ኅብረት ስምምነት (የካምፓላ ስምምነት)፣ ተዋዋይ ሀገራት ተፈናቃዮችን ከማንኛውም ዓይነት የወሲባዊ እና ጾታዊ ጥቃት በተለይም አስገድዶ መደፈር፣ የወሲብ ብዝበዛ እና ጎጂ ድርጊቶች፣ ባርነት፣ ሕፃናትን ለውትድርና መመልመል እና በግጭቶች ውስጥ ማሳተፍ፣ የግዳጅ ጉልበት ሥራ፣ በሰዎች መነገድ እና ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርና ድንበር ማሻገር የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው ይገልጻል፡፡ እንዲሁም ስምምነቱ ልዩ ድጋፍ ለሚያሻቸው የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በተለይም ከቤተሰባቸው ለተለዩ እና ብቻቸውን ላሉ ሕፃናት፣ ለአካል ጉዳተኞች ወይም ተላላፊ በሽታ ላለባቸው ሰዎች ልዩ ጥበቃ እና ድጋፍ እንዲደረግላቸው ይጠይቃል፡፡
እ.ኤ.አ. በሚያዝያ ወር 2022 ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት (International Organization for Migration/IOM) ባወጣው ዘገባ መሰረት በኢትዮጵያ ወደ 4.5 ሚሊዮን የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እንደሚኖሩ እና ከእነዚህ መካከል 54 በመቶ ሕፃናት እንደሆኑ ይገመታል፡፡ ዘገባው 80 በመቶ በላይ የሆኑት የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ከግጭት ጋር በተገናኘ ከመኖሪያ አካባቢያቸው የተፈናቀሉ መሆኑን ያስረዳል፡፡ እ.ኤ.አ. መስከረም ወር 2021 ባወጣው ዘገባ ደግሞ የተ.መ.ድ. የሕፃናትና የትምህርት ፈንድ (UNICEF) የትግራይ ጦርነት ወደ አፋር እና አማራ ክልሎች በመስፋፋቱ 14 ሚሊዮን ሕፃናት አስቸኳይ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው መግለጹ ይታወሳል፡፡
ኢሰመኮ ባለፉት አስር ወራት ወደ 1.5 ሚሊዮን የሚጠጉ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በሚገኙባቸው አምስት ክልሎች ባሉ 47 መጠለያ ጣቢያዎችና አካባቢዎች ላይ ባደረገው የሰብአዊ መብቶች ክትትል መሰረት የሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ሕፃናት ለከፍተኛ የምግብ እጥረት መጋለጥና ትምህርት ማቋረጥን ጨምሮ፣ ለጾታዊ ጥቃት፥ ለጉልበት እና ለወሲባዊ፥ ብዝበዛ፣ ለልመና እና ሌሎች ጎጂ ድርጊቶች ተጋላጭ እንደሆኑ መረዳት ተችሏል።
የኢሰመኮ የሴቶች እና ሕፃናት መብቶች ኮሚሽነር መስከረም ገስጥ “ከሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ሕፃናት መካከል ሴት ሕፃናት፥ ከወላጆቻቸው የተነጠሉ ወይም ጠባቂ የሌላቸው ሕፃናት እንዲሁም የአካል ጉዳተኛ ሕፃናት ለበለጠ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ስለሚጋለጡ ባለድርሻ አካላት ልዩ ትኩረት ሊሰጧቸው ይገባል” በማለት ለጉዳዩ አጽንዖት ሰጥተዋል።
የተፈናቃይ ሕፃናት ለተደራራቢ ጎጂ ድርጊቶች የመጋለጥ ዋነኛ መንሥኤዎች በመፈናቀል ሁኔታ እና ሂደት ሕፃናት በቤተሰብ፣ በማኅበረሰብ እና በመንግሥት የሚደረግላቸው ጥበቃና እንክብካቤ መላላት፥ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እንዲሁም፣ የፍትሕ አካላት ውጤታማነት መቀነስ ናቸው። በመሆኑም በየዓመቱ ሰኔ 9 የሚታሰበውን የአፍሪካ ሕፃናት ቀን አስመልከቶ ኢሰመኮ መንግሥት በተፈናቃይ ካምፖች እና በተለያዩ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የሚኖሩ የሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ሕፃናት ከማንኛውም ዓይነት ጎጂ ድርጊቶች እንዲጠበቁ ለማረጋገጥ አስፈላጊው እርምጃዎች እንዲወሰዱ ጥሪ እያቀረበ፣ በተለይም፦
- የፌደራል እና የክልል መንግሥታት በካምፖች እና ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች የሚኖሩ ተፈናቃይ ሕፃናት ጥቅምና ፍላጎትን መሰረት ያደረጉ ማቆያዎችን (Safe Space) እንዲያዘጋጁ፥ ጥቃት ሲፈጸም አቤቱታ የሚያቀርቡበት፥ ማኅበራዊና ሥነ ልቦናዊ ድጋፎች የሚያገኙበት እንዲሁም ተጠያቂነት የሚረጋገጥበት
ሥርዓት እንዲዘረጉ፥ መንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ማኅበረሰብ አቀፍ የሕፃናት ጥበቃ ሥርዓት (Community-based child protection system) የሕፃናቱን ሁኔታ እና ፍላጎት መሰረት በማድረግ ተግባራዊ ለማድረግ በጋራ እንዲሰሩ፥ - የሕፃናትን የተሻለ ጥቅም (Best Interest of the Child) ማስጠበቅን ባገናዘበ መልኩ ለመፈናቀል ዘላቂ መፍትሔዎች ለማግኘት በሚደረጉ ማንኛውም ጥረቶች መንግሥት የተፈናቃይ ሕፃናትን ልዩ ፍላጎት እና ጥቅምን መጠበቁን እንዲያረጋግጥ፥ ኮሚሽኑ ጥሪ ያቀርባል።