የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በሐረሪ ክልል የተጠርጣሪዎችና የታራሚዎች የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ ላይ ከሰኔ 16 እና 17 ቀን 2015 ዓ.ም. ከባለድርሻ አካላት ጋር በድሬዳዋ ከተማ የውይይት መድረኮች አካሄደ፡፡
በመድረኮቹ የሐረሪ ክልል ማረሚያ ቤት እና የፖሊስ ኮሚሽን ከፍተኛ ኀላፊዎች፣ የፖሊስ ጣቢያ አዛዦች፣ መርማሪ ፖሊሶች፣ እንዲሁም የክልሉ ፕሬዝደንት ጽ/ቤት፣ የክልሉ ምክር ቤት፣ የፍትሕ ቢሮ፣ ጠቅላይ ፍ/ቤት፣ ጸጥታ ቢሮ፣ የጤና ቢሮ እና የትምህርት ቢሮ ተወካዮች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
በውይይት መድረኩ ክትትል በተደረገባቸው ፖሊስ ጣቢያዎች እና ማረሚያ ቤት ላይ የታዩ እምርታዎችን፣ አሳሳቢ ጉዳዮችን፣ እንዲሁም ለወደፊት ሊወሰዱ የሚገቡ የማስተካከያ እርምጃዎችን የተመለከቱ ምክረ ሐሳቦች የቀረቡ ሲሆን በአጠቃላይ ግኝቶች ላይ መግባባት የተፈጠረበት እና በትብብር ለመሥራት ቃል የተገባበት ነበር።
በክልሉ የተጠርጣሪዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝን በተመለከተ ስርዓታዊ አካላዊ ድብደባ አለመኖሩ፣ የተጠርጣሪ ቤተሰቦች (ጠያቂዎች) ከተጠርጣሪዎች ጋር የመገናኘት መብቶቻቸው መከበሩ እና ለተጠርጣሪዎች ቁርስ እንዲቀርብ መደረጉ ከሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ አንጻር በመልካም አፈጻጸም ተነስተዋል፡፡
በሌላ በኩል በጣቢያዎች አሳሳቢ የመቆያ ክፍሎች፣ የመፀዳጃ ቤቶች እና የግቢ የንጽሕና ጉድለቶች ያሉ መሆናቸው፣ በሚሊሻ፣ በአስተዳደር አካላት እና በመደበኛ ፖሊስ የሚፈጸም የዘፈቀደ እስር መኖሩ፣ በማቆያ ክፍሎቹ በቂ የተፈጥሮም ሆነ ሰው ሰራሽ ብርሃን አለመኖር፣ የማቆያ ክፍሎቹ ጠባብና የተጨናነቁ መሆን፣ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ሲውሉ ለቤተሰቦቻቸው አለማሳወቅ፣ ከተለዩ አሳሳቢ ጉዳዮች ውስጥ ይገኙበታል፡፡ በተጨማሪም በሁሉም ክትትል በተደረገባቸው የፖሊስ ጣቢያዎች ለሴት ተጠርጣሪዎች የተዘጋጁ የማቆያ ክፍሎች አለመኖራቸው፣ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ተጠርጣሪዎች ለአካለ መጠን ከደረሱ ተጠርጣሪዎች ጋር ተቀላቅለው እንዲያዙ ማድረግ፣ ጤነኛ እና የታመሙ ተጠርጣሪዎችን አንድ ክፍል ውስጥ እንዲሆኑ ማድረግ፣ ተጠርጣሪዎች ሲገቡና ሲለቀቁ መመዝገብ (documentation) ላይ ክፍተቶች መስተዋላቸው እና የመሠረታዊ አቅርቦት እጥረት የሚሉት እንደ ክፍተት የቀረቡ ግኝቶች ናቸው።
ኢሰመኮ በሐረሪ ክልል የተጠርጣሪዎችን ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ለማሻሻል በቀጣይ ጊዜያት በክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን መተግበር ያለባቸው የድርጊት መርሃግብሮችን በማዘጋጀት ያቀረበ ሲሆን ከእነዚህም መካከል በክልሉ የዘፈቀደ እስር እና ድብደባ እንዲቆም ለፖሊስ፣ ለአስተዳደር አካላት እና ለሚሊሻ አባላት ግልጽ የሆነ መመሪያ እንዲተላለፍ እና እንዲተገበር፣ ለሴቶች እና ዕድሜአቸው ከ18 አመት በታች ለሆኑ ተጠርጣሪዎች ተለይተው የሚያዙበት ክፍሎች እንዲዘጋጁ፣ የተጠርጣሪዎች ማቆያ ክፍሎች መጣበብ ለመቀነስ ተጨማሪ ክፍሎች እንዲገነቡ፣ አሁን ያሉ የማቆያ ክፍሎች በቂ የሆነ ብርሀን እንዲኖራቸው እንዲደረግ፣ የፖሊስ ጣቢያዎች የተስፋፋ የንጽህና ችግር እንዲቀረፍ፣ ማንኛውም ተጠርጣሪ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሲገባ እና ሲለቀቅ በአግባቡ እንዲመዘገብ ፣ የተጠርጣሪዎች የሰብአዊ መብቶችን በተመለከተ ለጸጥታ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እንዲሰጥ የሚሉ እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡ በተመሳሳይ በሐረሪ ክልል ማረሚያ ቤት ላይ የተደረገ ክትትል ግኝቶችን መነሻ በማድረግ በክልሉ የታራሚዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ ሰኔ 17 ቀን 2015 ዓ.ም. በድሬዳዋ ከተማ ከክልሉ ማረሚያ ቤት ኮሚሽን እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡ በውይይቱ ለሴት ታራሚዎች እና ለልጆቻቸው የሚውል የማገገሚያ ተቋም ለብቻ መገንባቱ፣ ከዚህ ቀደም ይስተዋል የነበረው የታራሚዎች ኢ-ሰብአዊ አያያዝ መሻሻሉ፣ ለታካሚ ታራሚዎች የሚውሉ መድኃኒቶችን አቅርቦት መጠን ማሳደግ መቻሉ እንዲሁም በማረሚያ ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ የጉድጓድ ውሃ ቁፋሮ በማካሄድ ከውሃ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመቅረፍ ጥረቶች መጀመራቸው እንደ መልካም እምርታዎች ተነስተዋል፡፡
በክትትል ግኝቱ በታራሚዎች አያያዝ ላይ እንደ ክፍተት ከተለዩና ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መካከል የአእምሮ ሕመም ያለባቸው ታራሚዎችን ከሌሎች ታራሚዎች ጋር አንድ ላይ እንዲሆኑ ማድረግ፣ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ታራሚዎች ለአካለ መጠን ከደረሱ ታራሚዎች ጋር ተቀላቅለው መገኘታቸው፣ ታራሚዎች ለሲጋራ እና ጫት ተጠቃሚነት መጋለጣቸው፣ የሙያና ክህሎት ትምህርቶች እና ስልጠናዎች ለረጅም ዓመት ፍርደኞች ተደራሽ አለመሆናቸው፣ ለታራሚዎች የሚቀርበው ምግብ ጥራትና ንጽሕና የጎደለው መሆን እና የመጸዳጃ ቤቶች ላይ የንጽሕና ጉድለት መኖሩ የሚሉት ይገኙበታል።
በውይይቱም ኢሰመኮ የክትትል ግኝቶችን መሠረት በማድረግ ምክረ ሀሳብ ያቀረበ ሲሆን መሠረታዊ አገልግሎቶችን በተለይም ምግብ፣ መጠለያ፣ ጤና እና ውሃ ለሟሟላትየክልሉ መንግሥት እየጨመረ የሚሄድ በጀት እንዲመድብ፣ የማረሚያ ቤት ክፍል እና ግቢ ጥበትን ለመቅረፍ መፍትሔ እንዲፈለግ፣ ሕፃናት ታራሚዎችን ከአካለ መጠን ከደረሱ ታራሚዎች ተለይተው እንዲታረሙ፣ የሚስተዋለውን የውሃ አቅርቦት መቆራረጥ ለመቅረፍ ዘላቂ መፍትሔ እንዲፈለግለት፣ ታራሚዎችን ለሱስ የሚያጋልጡ ድርጊቶች ላይ ተገቢ የሆነ ቁጥጥር እንዲደረግ እና በክትትሉ የተለዩ ክፍተቶችን ለመቅረፍ በሚደረግ ጥረት ውስጥ ደግሞ የባለድርሻ አካላት በቅንጅት እንዲሠሩ የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን እንዲሁም የማረሚያ ቤቱ ከፍተኛ ኀላፊዎች በክትትሉ የተለዩ ክፍተቶችን በሂደት ለማስተካከል ቁርጠኝነታቸውን የገለጹ ሲሆን አያይዘውም የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን የበጀትና የቴክኒክ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።