የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአራት ክልሎችና በአንድ ከተማ አስተዳደር በሚገኙ የሕፃናት ማሳደጊያ ማእከላት ውስጥ ያሉ ሕፃናትን ሁኔታ ከሕፃናት መብቶች፣ መርሖች እና መስፈርቶች አንጻር ለመገምገም ባከናወነው ክትትል የተለዩ ግኝቶች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ጥቅምት 29 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱ ክትትል ከተደረገባቸው ከሐረሪ፣ ከኦሮሚያና ከሲዳማ ክልሎች እና ከወላይታ ዞን እንዲሁም ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የተውጣጡ አስራ አራት የሕፃናት ማሳደጊያ ማእከላት ተወካዮች እንዲሁም ከክልሎቹ እና ከከተማ አስተዳደሩ ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮዎች የተወከሉ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል። የውይይቱም ዋና ዓላማ የክትትል ግኝቶችን ለሚመለከታቸው አካላት ማሳወቅ እና በክትትሉ የተለዩ የመብት ጥሰቶች እንዲሻሻሉ እንዲሁም በምክረ ሐሳቦቹ መሠረት ባለድርሻ አካላት ተገቢውን እርምጃ እንዲወስዱ ውትወታ ማድረግ ነው፡፡
በክትትሉ በሕፃናት ማሳደጊያ ማእከላት ውስጥ ያሉ ሕፃናት ሁኔታን ከሕፃናት መብቶች መሠረታዊ መርሖች አንጻር በመቃኘ የቅበላ ሥርዓት፤ የሕፃናቱ በቂ የኑሮ ደረጃ ማግኘት፣ የጥበቃ፣ የተሳትፎና የግላዊ ሕይወት ሁኔታ እንዲሁም የመረጃና የማኅበራዊ መብቶች ተፈትሸዋል፡፡ በክትትሉ የተለዩ መልካም ተሞክሮዎች፤ ተግዳሮቶች እና መወሰድ ያለባቸው የማሻሻያ እርምጃዎች ለተሳታፊዎች በዝርዝር ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች የክትትሉ ግኝቶች በማሳደጊያ ተቋማት ውስጥ እና በተቆጣጣሪ አካላት በኩል ያለውን ሁኔታ የሚያሳዩ መሆኑን ገልጸው፤ ይህ የምክክር መድረክ መዘጋጀቱ በክትትል ለተለዩ ችግሮች አፋጣኛ መፍትሔ ለመስጠት እንዲሁም እርስ በእርስ ለመማማር በር እንደከፈተላቸው ተናግረዋል። በመጨረሻም የሕፃናት ማሳደጊያ ማእከላት የሕፃናት መብቶችን ለማሻሻል የቀረቡትን ምክረ ሐሳቦች መተግበር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ተወያይተዋል። ተጨማሪ ትኩረት የሚሹ ዋና ዋና ጉዳዮችን በመለየትም ተግባራዊ ለማድረግ ስምምነት ላይ ተደርሷል።
የኢሰመኮ የሴቶች እና የሕፃናት መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር የምስራች ለገሰ ከቤተሰብ እንክብካቤ ውጪ የሚያድጉ ሕፃናት ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሠራበት የሚገባ መሆኑን አስረድተዋል። አክለውም የሕፃናት ማሳደጊያ ተቋማት በሕፃናት መብቶች የተቃኘ እንክብካቤ፤ የአገልግሎቶች እና የጥበቃ ሥርዓቶች በመዘርጋትና መልካም ተሞክሮዎችን በመለዋወጥ ብቁ ዜጋን በማፍራት ረገድ ያላቸውን ሚና እንዲያጎለብቱ በአጽንዖት ገልጸዋል፡፡