የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከGIZ-PILUP II ፕሮጀክት ጋር በመተባበር የመሬት መብቶች እና ሰብአዊ መብቶች በሚል ርእስ ከባለድርሻ አካላት ጋር በአዳማ ከተማ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አካሄደ። ከየካቲት 9 እስከ 10 ቀን 2015 ዓ.ም. በተካሄደው መድረክ የፌደራል ፕላን እና ልማት ሚንስቴር፣ የአማራ እና የኦሮሚያ ክልል መሬት ቢሮ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኢንቨስትመንት እና መሬት ቢሮ እና የጋምቤላ ክልል የግብርና ቢሮ እንዲሁም የተለያዩ ሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች ተሳትፈዋል።
የኢሰመኮ የሲቪል፣ ፖለቲካዊ፣ የኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጂብሪል የመሬት መብት ከምግብ፣ ከጤና፣ የራስን መብት በራስ የመወሠን፣ የመጠለያ፣ የውሃ፣ የባህላዊ መብቶች ጋር ጥብቅ ግንኙነት እንዳለው አስታውሰዋል፡፡ በተጨማሪም መሬትን በመጠቀም ረገድ በሴቶች እና ከይዞታቸው አላግባብ በሚነጠቁና በሚነቀሉ ላይ የሚደረሰውን ጫና መንግሥት መከላከል እንዳለበት የተናገሩ ሲሆን አክለውም መንግሥት ባለመብቶችን እና የባለደርሻ አካላትን ስለጉዳዩ ማስገንዘብ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
በግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ ስለመሬት መብቶች እና ሰብአዊ መብቶች አጠቃላይ ትስስር የተዳሰሰ ሲሆን፤ የመሬት እና የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ እንዲሁም በመሬት ይዞታ ዋስትና ከመሬት መብቶች ጋር ያለው ተያያዥነትን እና ሰብአዊ መብቶች መሠረት ያደረገ አቀራረብ ለመሬት አጠቃቀም እቅድ ያለውን ሚና የተመለከቱ ሦስት ጽሑፎች ቀርበዋል። በውይይቱ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት ከኮሚሽኑ ጋር የሥራ ትስስር መፈጠር እንዳለበትም አስገንዝበዋል።