የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የብሔራዊ ምርመራ ዘዴን በመጠቀም በሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ጥበቃ ላይ ያተኮረ ግልጽ የአቤቱታ መቀበያ መድረክ እና በሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ሕግ አስፈላጊነት ላይ ማእከል ያደረገ የውይይት መድረክ ታኅሣሥ 10 እና 11 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ አካሂዷል። በመድረኮቹ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የሕግ አስከባሪና የአስተዳደር አካላት እንዲሁም የፍርድ ቤት ተወካዮች እና ጋዜጠኞች ተገኝተዋል።
በግልጽ የአቤቱታ መቀበያ መድረኩ ኢሰመኮ ከአፍሪካ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ትስስር (Network of African National Human Rights Institutions) ጋር በመተባበር በሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ጥበቃ ዙሪያ የዳሰሳ ጥናት ማዘጋጀቱን እንዲሁም ይህ መድረክ የመብቶች ተሟጋቾች የሚደርስባቸውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እና ችግሮች ለይቶ በማቅረብ ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመወያየት እና ውትወታ ለማካሄድ ታልሞ የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል።
የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች፣ የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋች እና ጋዜጠኛ በአቤቱታ መቀበያ መድረኩ በግልጽ በመቅረብ እንዲሁም አንድ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች በምስጢር በመቅረብ መደበኛ ሥራቸውን ሲያከናውኑ ስለደረሰባቸው የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እና ችግሮች በዝርዝር አስረድተዋል። ከተጠቀሱ የመብት ጥሰቶች እና ተግዳሮቶች መካከል ሥራቸውን እንዲያቆሙ ማስጠንቀቅ፣ ዛቻ እና ማስፈራሪያ፣ የዘፈቀደ እስር፣ ድብደባ፣ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ሴት የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ላይ የሚደርስ ስም ማጥፋት፣ ትንኮሳ፣ የአስገድዶ መድፈር እና የግድያ ዛቻ ይገኙበታል። የሕግ አስከባሪ አካላት ተወካዮችም በመድረኩ ላይ ለቀረቡ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እና ተግዳሮቶች ምላሽ የሰጡ ሲሆን ስለተወሰዱ የእርምት እና የማስተካከያ እርምጃዎችም ገለጻ አድርገዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ላይ የሚደርሱ የመብቶች ጥሰቶች እና ሌሎች ተግዳሮቶችን ለመከላከል እና ለመቀነስ መከናወን በሚገባቸው ተግባራት ላይ የተወያዩ ሲሆን የመብቶች ጥሰቶች የሚፈጽሙ አካላት ላይ የሚመለከተው አካል ተገቢውን ምርመራ በማከናወን የሕግ ተጠያቂነትን ማስፈን እንደሚገባው አጽንዖት ሰጥተዋል። በተጨማሪም የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ለሰብአዊ መብቶች ጥበቃ እና መከበር በመወትወት እና ድምጽ በመሆን በሚያበረክቱት በጎ አስተዋጽዖ ለተለያዩ የመብቶች ጥሰቶች እና ችግሮች ተጋላጭ በመሆናቸው ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ተጠቅሷል።
የኢሰመኮ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር እና የግልጽ የአቤቱታ መቀበያ መድረኩ የመርማሪ ኮሚሽነሮች ሰብሳቢ ርግበ ገብረሐዋሪያ ሐሳብን በነጻነት የመያዝና የመግለጽ መብት በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 29 እና በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሕግ ዕውቅና ያለውና አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል የማይስማማበትን ሐሳብ ጭምር የመያዝና የመግለጽ መብትን የሚያካትት መሆኑን ጠቅሰዋል። አያይዘውም “ሴት የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች በሚያነሷቸው ሐሳቦች ምክንያት ጾታን መሠረት ላደረጉ ጥቃቶች የተጋለጡ በመሆኑ ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል” ብለዋል። አክለውም በቴክኖሎጂ የታገዘ ጾታዊ ጥቃትን (Technology Facilitated Gender-based Violence) ለመከላከልና የጥቃት ፈጻሚዎችን ተጠያቂነት ለማረጋገጥ ምርመራውን በቴክኖሎጂ ማዘመን የመንግሥት ኃላፊነት መሆኑን ገልጸዋል።
የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ሕግ አስፈላጊነትን አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር በተካሄደ የውይይት መድረክ ኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ጥበቃን አስመልክቶ ያከናወነው የዳሰሳ ጥናት ቅድመ ግኝቶች ቀርበው ተጨማሪ ግብአት ተሰብስቧል። እንዲሁም ኢሰመኮ ያዘጋጀው የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ሞዴል ረቂቅ ሕግ በዝርዝር ቀርቦ ውይይት ተካካሂዷል። የውይይቱ ተሳታፊዎች የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ሕግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው በቀረበው ሞዴል ረቂቅ ሕግ ላይ የማዳበሪያ አስተያየቶቻቸውን ሰጥተዋል።
የኢሰመኮ የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ የማህበራዊ እና የኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል “የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች በየትኛውም ሙያ ውስጥ የሚገኙ እና ለሴቶች፣ ለሕፃናት፣ ለአካል ጉዳተኞች፣ ለአረጋውያን ወይም ለየትኛውም የማኅበረሰብ ክፍል መብቶች መከበር እና መጠበቅ የሚሠሩ መሆናቸውን ጠቅሰው በዓለም አቀፍ፣ በአህጉራዊ እና በብሔራዊ ሕጎች የተደገፈ በቂ ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል” ብለዋል። አክለውም ኢሰመኮ በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ሕግ እንዲወጣ ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚሠራ ገልጸዋል።