የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እና የሲቪል ማኅበራት የትብብር መድረክ በሀገራዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታዎች በተለይም በሲቪክ ምኅዳሩ እና በሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ጥበቃ ላይ ያተኮረ ብሔራዊ ኮንፈረንስ ሰኔ 24 ቀን 2017 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ አካሂደዋል። ብሔራዊ ኮንፈረንሱ በ2017 በጀት ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ የነበሩ አሳሳቢ እና ወቅታዊ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች ላይ ከተለያዩ ክልሎች ከተውጣጡና በሰብአዊ መብቶች ላይ አተኩረው ከሚሠሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር በጋራ ለመምከር ያለመ ነው።

በብሔራዊ ኮንፈረንሱ በሰብአዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራ፣ በሽግግር ፍትሕ፣ በሴቶች እና ሕፃናት፣ በአካል ጉዳተኞችና አረጋውያን መብቶች እና መሰል ዘርፎች ላይ ሀገራዊ መሻሻል ለማምጣት ኢሰመኮ፣ ሲቪል ማኅበራትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በትብብርና በቅንጅት መሠራት ባለባቸው ሥራዎች ላይ ውይይት አድርገዋል። ኢሰመኮ በሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ጥበቃ እና ከሲቪክ ምኅዳሩ ጋር በተያያዘ በ2017 ዓ.ም. የነበሩ ክስተቶች ላይ ያከናወነው ጥናት፣ በግልጽ የአቤቱታ መቀበያ መድረክ እንዲሁም በክትትልና ምርመራ የተለዩ ግኝቶች በዝርዝር ለኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች ቀርበዋል። በተጨማሪም በሰብአዊ መብቶች ላይ የሚሠሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በሥራቸው ወቅት ስለሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች እና ወቅታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን አስተያየቶች በግልጽ አቅርበዋል።

የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ የሰብአዊ መብቶችን ለማስጠበቅና ለማስከበር እንዲሁም በሲቪክ ምኅዳሩም ሆነ በሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ዙሪያ የሚታዩ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ከሕግና ፖሊሲ ውትወታ በተጨማሪ ሌሎች አማራጭ የመፍትሔ ሐሳቦች ላይ አተኩሮ መሥራት እንደሚገባ በሰጡት አስተያየት ጠቁመዋል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ባስተላለፉት መልእክት በሰብአዊ መብቶች፣ በሲቪክ ምኅዳሩም ሆነ በሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ጥበቃ ዙሪያ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚታዩ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ የሚመለከታቸው አካላት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ግልጽ የሆነ ውይይት ማድረግና በአጋርነት መሥራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል። የኢሰመኮ እና የሲቪል ማኅበራት የትብብር መድረክን ይበልጥ በማጠናከር ቀጣይነት ያለው ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግ፤ ለዚህም ኢሰመኮ የሚሰጠውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።