የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በሰባት ክልሎች በሰፋፊ እርሻ ልማት ጣቢያዎች ውስጥ የሚሠሩ ሴት እና ወጣት ሠራተኞች የሰብአዊ መብቶች ሁኔታን አስመልክቶ ባከናወነው ክትትል በተለዩ ግኝቶች እና በተሰጡ ምክረ ሐሳቦች ላይ ከአራት ክልሎች ከተወጣጡ ባለድርሻ አካላት ጋር ጥቅምት 28 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ዙር ውይይት ማካሄዱ ይታወሳል። በተያያዘም የሁለተኛ ዙር ውይይት ከሦስት ክልሎች ከተወጣጡ ባለድርሻ አካላት ጋር ታኅሣሥ 2 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ አካሂዷል፡፡
በውይይቱ የሶማሊ፣ ኦሮሚያ (ጅማ ዞን) እና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ክትትል የተደረገባቸው የእርሻ ጣቢያዎች እንዲሁም የፌዴራል፣ የክልል እና ዞን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ፣ የሥራና ክህሎት፣ የጤና እና የኢንቨስትመንት ቢሮዎች ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡
በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል ከትምህርት ቤቶች ጋር የተያያዘ የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ላይ የተካሄደ የምክረ ሐሳብ አፈጻጸም ክትትል እና በክትትሉ የተለዩ የተሻሻሉ ጉዳዮች እንዲሁም በቀጣይ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እና ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ መወሰድ ያለባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡