የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በሴቶች መብቶች ላይ የሚሠሩ መደበኛ ያልሆኑ አደረጃጀቶች የሚያከናውኗቸው ተግባራት ሰብአዊ መብቶች ተኮር እንዲሆኑ ለማስቻል የግንዛቤ ማሳደጊያ ውይይት ነሐሴ 2 እና 3 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ አካሂዷል። ውይይቱ ግንዛቤ ከማሳደግ በተጨማሪ በውይይቱ በሚለዩ የሥራ ጉዳዮች መሠረት ከአደረጃጀቶቹ ጋር ቀጣይነት ያለው ትብብርና ግንኙነት ለመፍጠር ያለመ ነው።
በውይይቱ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ካቋቋማቸው በጎ ፈቃደኛ ኮሚቴ ማእከሎች እና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ ከተመሠረተው ‘ይታወቅ የራስ አገዝ ቡድን ጥምረት’ ከአዲስ አበባ፣ ከአርባ ምንጭ፣ ከአሶሳ፣ ከድሬዳዋ፤ ከጋምቤላ፣ ከሃዋሳ፣ ከጅማ፣ ከመቀሌ እና ከሰመራ ከተሞች የተውጣጡ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።
በግንዛቤ ማሳደጊያ ውይይቱ ኢሰመኮ ባለፉት ሁለት ዓመታት በሴቶች ሰብአዊ መብቶች ላይ ባካሄዳቸው ክትትሎች የለያቸው በተፈጥሮአዊ እና በሰው ሰራሽ አደጋዎች ሳቢያ በሴቶች ላይ የደረሱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች፣ የሴቶች ጤናማ የሥራ ሁኔታ የማግኘት መብት፣ ከጥቃት የመጠበቅ መብት፣ የጥቃት ተጎጂ የሆኑ ሴቶች በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ጉዳያቸው የሚታይበት ሁኔታ እንዲሁም ሴቶች በፖለቲካ መስክ ያላቸውን ተሳትፎ የተመለከቱ ግኝቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ በተጨማሪም ኢሰመኮ በ2017 ዓ.ም. ትኩረት በሚያደርግባቸው የሴቶች እና የሕፃናት መብቶች ጉዳዮች እንዲሁም በሽግግር ፍትሕ እና ሀገራዊ ምክክር ላይ ማብራሪያ ተሰጥቷል።
ተሳታፊዎች በበኩላቸው በሥራ እንቅስቃሴአቸው ከእናቶቻቸው ጋር በማረሚያ ቤት የሚቆዩ ሕፃናት ሁኔታን፣ በሥራ ቦታ የሚፈጸም ጾታዊ ትንኮሳን እና በሴቶችና በሕፃናት መነገድን በተመለከተ ያስተዋሏቸውን አሳሳቢ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች እና በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ምላሽ አሰጣጥ ዙሪያ ያሉ ወስንነቶችን አጋርተዋል። በመጨረሻም በውይይት የተነሱ የሴቶችና የሕፃናት መብቶችን ለመጠበቅ እና ጥሰቶችን ለመከላከል በሰብአዊ መብቶች ተሟጋች አደረጃጀቶች ሊሠሩ የሚገቡ የውትወታ ሥራዎች እና ዘላቂ ትብብር ለመፍጠር የሚያስችል የድርጊት መርኃ ግብር የተዘጋጀ ሲሆን ለአፈጻጸሙም የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል።
የኢሰመኮ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአረጋውያን እና የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ ለተሟላ የሴቶች እና የሕፃናት ሰብአዊ መብቶች ጥበቃ እና መከበር የሚመለከታቸው አካላት ትብብርና ጥረት እንደሚያስፈልግ ገልጸው “የውትወታ ሥራዎች ስልታዊ እና ሰብአዊ መብቶች ተኮር ሊሆኑ ይገባል” ብለዋል።