‘‘የሽግግር ፍትሕ’’ ሲባል ማህበረሰቦች የተለያዩ የፖሊሲ እርምጃዎችን በመውሰድ እና ተቋማዊ አሠራሮችን በመጠቀም ያለፉ መጠነ-ሰፊ ጥሰቶችን፣ ክፍፍሎችን እና አለመመጣጠኖችን ለማስወገድ፣ ፍትሕን ለማስፈን እና እርቅን ለማውረድ፣ ለደኅንነትም ሆነ ለዴሞክራሲያዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ሥርዓት ግንባታ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የሚያደርጉትን ጥረት የሚመለከት ፅንሰ ሐሳብ ነው፡፡[1]

በቅርቡ ይፋ በተደረገው ‘‘የኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ አቅጣጫ አማራጮች’’ ሰነድ ዙሪያ በሚደረጉ ምክክሮችም ሆነ በሌሎች የሽግግር ፍትሕ ሂደቶች የአረጋውያን እና አካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ እና ተካታችነት ለማረጋገጥ አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎችን መውሰድ ይገባል።

ከተሳትፎ እና ተካታችነት አንጻር የመንግሥት ግዴታ ምንድን ነው?

የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን በሕዝባዊ ጉዳዮች ውስጥ የመሳተፍና መካተት መብት በብሔራዊ ሕጎች እና ኢትዮጵያ ፈርማ ባጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍና አህጉራዊ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች ዕውቅና የተሰጠው መብት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 38 ንዑስ አንቀጽ 1(ሀ) መሠረት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በቀለም፣ በዘር፣ በብሔር፣ በብሔረሰብ፣ በጾታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ ወይም በሌላ አመለካከት ወይም በሌላ ሁኔታ [አካል ጉዳት፣ ዕድሜ…] ላይ የተመሠረተ ልዩነት ሳይደረግበት በቀጥታ እና በመረጣቸው ተወካዮች አማካኝነት በሕዝብ ጉዳይ የመሳተፍ መብት ያለው መሆኑን ይደነግጋል፡፡

በተመሳሳይ የአረጋውያን እና የአካል ጉዳተኞች በሕዝባዊ ጉዳዮች የመሳተፍ መብት በዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች መግለጫ አንቀጽ 21፣ በዓለም አቀፉ የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን አንቀጽ 25 (ሀ)፣ በዓለም አቀፉ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት አንቀጽ 3 (ሐ) እና 29 (ለ)፣ በአፍሪካ የሰዎች እና ሕዝቦች መብቶች ቻርተር አንቀጽ 13 ንዑስ አንቀጽ 1 እንዲሁም በአፍሪካ የአረጋውያን መብቶች ፕሮቶኮል አንቀጽ 17 ድንጋጌዎች ውስጥ ተደንግጎ የሚገኝ ሰብአዊ መብት ነው፡፡ ከእነዚህ የሕግ ሰነዶች ባሻገር እንደ የተ.መ.ድ. በሕዝባዊ ጉዳዮች የመሳተፍ መብት ውጤታማ አተገባበር መመሪያ (UN OHCHR Guidelines for States on the effective implementation of the right to participate in public affairs)፣ የተ.መ.ድ. የአረጋውያን መርሆች (United Nations Principles for Older Persons)፣ ዓለም አቀፉ የአረጋውያን የድርጊት መርኃ ግብር (International Plan of Action on Ageing) ያሉ ዓለም አቀፍ የፖሊሲ ማዕቀፎች ሀገራት ፖሊሲዎችን በሚያወጡበትና በሚፈጽሙበት ጊዜ የአረጋውያን ንቁ ተሳትፎ መኖር እንዳለበት ይገልጻሉ፡፡

በሕዝባዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ የማድረግ መብት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት፣ የሕግ የበላይነት እና ማኅበራዊ አካታችነትና እድገት እውን እንዲሆን እንዲሁም ሰብአዊ መብቶች እንዲስፋፉ የጎላ አስተዋጽዖ የሚያድርግ እንደመሆኑ፤ መንግሥት አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያንን ጨምሮ ማንኛውም ሰው በሕዝባዊ ጉዳዮች ላይ ያለአድሎና ከሌሎች ጋር በእኩልነት ውጤታማ እና ትርጉም ያለው ተሳትፎ ማድረጋቸውን የማረጋገጥ ግዴታ አለበት፡፡

አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች በሽግግር ፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ እንዴት ይሳተፉ?

በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ በአፋር፣ አማራ እና ትግራይ ክልሎች የሚኖሩ አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ለጅምላ ጥቃት፣ ለሞት፣ ለአካል እና ለሥነልቦና ጉዳቶች፣ ወሲባዊ እና ጾታዊ ጥቃቶች እንዲሁም ለንብረት ውድመት፣ ዘረፋ እና ገፈፋ መዳረጋቸውን፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ቀደም ሲል ይፋ ያደረጋቸው የምርመራ እና ክትትል ሪፖርቶች ያሳያሉ፡፡ በተለይም መስማት የተሳናቸው ሰዎች እና የአእምሮ ሕሙማን በመንገድ ላይ በመገኘታቸው፣ መንቀሳቀስ በተከለከለባቸው ሰዓታት ሲንቀሳቀሱ በመገኘታቸው፣ የሚሰጣቸውን ትእዛዝ ለመፈጸም ባለመቻላቸው፣ ለሚጠየቁት ጥያቄ ትክክለኛ መልስ ለመስጠት ባለመቻላቸው፣ ወይም ‘‘ሰላዮች ናቸው’’ በሚል ጥርጣሬ መገደላቸውን እና ከሌሎች ሲቪል ሰዎች በተለየ የጥቃት ኢላማ መደረጋቸውን ኮሚሽኑ አረጋግጧል፡፡

በጦርነት ዐውድ የተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ለመለየት ከተከናወኑት ምርመራዎች በተጨማሪ በአፋር እና አማራ ክልሎች በተለያዩ ጊዜያት በተከሰተው ጦርነት  በተለይ በአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ ለመገምገም የተደረገው የሰብአዊ መብቶች ክትትልም በአረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች ላይ ዓይነተ-ብዙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መፈጸማቸውን፣ ለተጎጂዎች የሚደረጉ ሰብአዊ ድጋፎች በበቂ መጠን ተደራሽ አለመሆናቸውን እንዲሁም የመልሶ ማቋቋምና ተሐድሶ አገልግሎቶችን በበቂ መጠን ተጠቃሚ እንዳልሆኑ ለይቷል፡፡

ስለሆነም ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች በአካል ጉዳተኞችና አረጋውያን ላይ የደረሰውን መጠነ ሰፊ ጉዳትና እንግልት ከግምት ውስጥ በማስገባት፡-

  • በሁሉም የሽግግር ፍትሕ ሂደቱን በተመለከቱ ምክክሮች ላይ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች ተሳትፎ እንዳይኖራቸው ዕንቅፋት የሚፈጥሩ የአመለካከት ተግዳሮቶችን ጨምሮ ከተቋማዊ አሠራር፣ ምክክሮች ከሚደረጉባቸው መሰብሰቢያዎች ጋር በተገናኘ የሚስተዋሉ የከባቢያዊ ተደራሽነት ዕንቅፋቶችን እንዲሁም ከመረጃና የተግባቦት መንገዶች ጋር የተገናኙ መሰናክሎችን በማስወገድ፤
  • የተለያዩ ሰነዶችና ሌሎች ሂደቱን የተመለከቱ መረጃዎች ሁሉ ለአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ተደራሽ በሆነ መንገድ መተላለፋቸውን በማረጋገጥ (ለምሳሌ፡- በፍትሕ ሚኒስቴር በኩል ለውይይት የቀረበው የፖሊሲ ማዕቀፍ አማራጮች ሰነድ በብሬል ወይም በድምጽ ቅጂ አማራጭ እንዲኖረው በማድረግ፣ ሰነዱን አስመልክቶ በሚደረጉ ምክክሮች ላይ የምልክት ቋንቋ አስተርጓሚዎች እንዲኖሩ በማድረግ…)፤
  • በሁሉም የሽግግር ፍትሕ ሂደቱን በተመለከቱ ምክክሮች ላይ በየደረጃው ያሉ የአረጋውያን እና የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት ተወካዮች መሳተፋቸውን በማረጋገጥ፤
  • አረጋውያን እና አካል ጉዳተኛ ተጎጂዎች የሽግግር ፍትሕ ሂደትን አስመልክቶ በሚደረጉ ውይይቶችና ምክክሮች ሁሉ የሚሳተፉበት፣ የሚወከሉበትና የደረሰባቸውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት የሚናገሩበት አሠራር/ዘዴ በማዘጋጀት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን በማረጋገጥ (ለምሳሌ፡- ተጎጂዎችን ለመለየት በየአካባቢው ከሚገኙ የአረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ጋር ግንኙነት በመፍጠር፣ ምቹና ተደራሽ የመሰብሰቢያ አዳራሾችን በማመቻቸት፣ በምክክሮች ላይ ተሳታፊ ለሆኑ አካል ጉዳተኞች እንደ ጉዳት ዓይነታቸው የተመጣጣኝ ማመቻቸት እርምጃዎች ለመውሰድ የሚያስችል በጀት እንዲያዝ በማድረግ…)፤ እንዲሁም
  • በሽግግር ፍትሕ ሂደቱ እውነትን ከማፈላለግ እና ይፋ ከማውጣት፣ እርቅ ከመፈጸም፣ ምሕረት ከማድረግ፣ ለተጎጂዎች ተገቢውን ማካካሻ ከመስጠት እና ተቋማዊ ማሻሻያ ከማድረግ  አንጻር በሚተገበሩ ማናቸውም እርምጃዎች አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች ሊካተቱ ይገባል። እንዲሁም በሽግግር ፍትሕ ሂደቱ የሚጠበቁ ውጤቶች በአጠቃላይ የአረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች ሰብአዊ መብቶችን እና ዓይነተ-ብዙ ፍላጎቶችን አገናዛቢ መሆናቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ መለኪያዎችን በመቅረጽ በሂደቱ የሚኖራቸውን ሙሉ፣ ውጤታማ እና ትርጉም ያለው ተሳትፎ ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡

በአጠቃላይ የሽግግር ፍትሕ ሂደቱ የሚመራባቸው የአካታችነት፣ ርትዕ እና አድሎ ያለማድረግ መርሆች የሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች ተሳትፎ የሚበረታታ እና ፍላጎታቸውንም የሚያሟላ እንዲሆን የሚያስገድድ በመሆኑ፣ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች ለመብት ጥሰቶች ካላቸው የተጋላጭነት ሁኔታ የተነሳ ቅድሚያ የሚሰጧቸው ጉዳዮች እና ያሉባቸውን ስጋቶች ትኩረት መስጠት የሚገባ በመሆኑ፣ በተለይም በባህላዊ ፍትሕ ሥርዓቶች ላይ አረጋውያን ያላቸውን ተሳትፎ ማጎልበት የሚገባ በመሆኑ፤ የሽግግር ፍትሕ ሥርዓቱን በማቀድ፣ በመተግበር፣ በመከታተልና በመገምገም ሂደቶች ውስጥ ሙሉ፣ ውጤታማ እና ትርጉም ያለው ተሳትፎ እና ተካታችነት ሊኖራቸው ይገባል፡፡


[1] ለተጨማሪ ማብራሪያ ቀደም ሲል ኢሰመኮ በሽግግር ፍትሕ ዙሪያ ይፋ ያደረገውን ማስታወሻ (advisory note) እዚህ ይመልከቱ፡፡