በኢትዮጵያ ከ9 እስከ 15 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሕፃናት በወንጀል ነክ ነገር ውስጥ ገብተው ሲገኙ የሚወሰኑባቸው ቅጣቶችና የጥንቃቄ እርምጃዎች ለአካለ መጠን ለደረሱ አጥፊዎች ከተደነገጉት መደበኛ ቅጣቶች የተለዩ ሲሆኑ፣ ከእነዚህ ውስጥ በዓለም አቀፍ የሕፃናት መብቶች መሠረት እንደየመጨረሻ አማራጭ ተደርጎ እንዲወሰድ የተቀመጠው ወደ ጠባይ ማረሚያ ተቋም መላክ ነው። ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 18 ያሉ ሕፃናት በመደበኛው የወንጀል ሕግ የሚዳኙ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ ወደ ጠባይ ማረሚያ ተቋም እንዲላኩ ሊወስን ይችላል። የተሐድሶ ተቋማት መሠረታዊ ዓላማ በወንጀል ነክ ነገር ውስጥ ገብተው የተገኙ ሕፃናትን በማረም እና በማነጽ ወደ ማኅበረሰቡ መልሶ ማቀላቀል ነው። በእነዚህ ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ሕፃናት በቆይታቸው ሊደረግላቸው ስለሚገባው የሰብአዊ መብቶች አያያዝና ጥበቃ በብሔራዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች፣ መመሪያዎች እና ሌሎች ሰነዶች ተደንግጓል። ከአቀባበልና ምዝገባ ጀምሮ ዕድሜን፣ ጾታን፣ የጥፋተኝነት ዐይነትን፣ የልዩ እንክብካቤ ፍላጎትን ወዘተ. መሠረት ያደረገ ልዩ ጥበቃ ሊደረግላቸው የሚገባ ሲሆን፤ የተሐድሶ ማእከላቱ የተሟላ የምግብ፣ የቀለምና የሙያ ትምህርት፣ የስፖርትና መዝናኛ፣ የንጽሕና፣ የጤና ወዘተ. አገልግሎቶችን በበቂ ሁኔታ ለማቅረብ የሚያስችል አካባቢያዊ ሁኔታ፣ መሠረተ ልማት እና የሰው ኃይል፣ እንዲሁም ሌሎች ዝቅተኛ መስፈርቶችን ያሟሉ መሆን አለባቸው።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከመጋቢት 4 እስከ መጋቢት 6 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በወንጀል ነክ ነገር ውስጥ ገብተው በማቆያና ተሐድሶ ተቋም ውስጥ በሚገኙ ሕፃናት የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ ክትትል አከናውኗል። መረጃዎችና ማስረጃዎችን ለማሰባሰብ በተሐድሶ ተቋሙ ከሚኖሩ 16 ሕፃናት፣ 14 የተሐድሶ ተቋሙ ኃላፊዎችና ሠራተኞች እንዲሁም 5 ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች በአጠቃላይ ከ35 ሰዎች ጋር ቃለ መጠይቆች ተደርገዋል። በተጨማሪም በተሐድሶ ተቋሙ ከሚኖሩ ሕፃናት እና ከተቋሙ ሠራተኞች ጋር 2 የቡድን ውይይቶች እንዲሁም በሕፃናት ማደሪያ ክፍሎች፣ በሕክምና አገልግሎት መስጫ ሥፍራዎች፣ በመማሪያ ክፍሎች፣ በመጸዳጃ እና መታጠቢያ ቤቶች፣ በምግብ ማብሰያ ክፍሎች እና በምድረ ግቢው አጠቃላይ አካባቢያዊ ሁኔታ ላይ ያተኮሩ 6 የመስክ ምልከታዎች ተካሂደዋል። ኢሰመኮ በክትትሉ የደረሰባቸውን ቀዳሚ ግኝቶች ለባለድርሻዎች ለማጋራትና ተግባራዊ ሊደረጉ የሚገባቸው መፍትሔዎች ላይ ምክክር ለማድረግ ግንቦት 22 ቀን 2016 ዓ.ም. የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ የነበረ ሲሆን፤ መጋቢት 9 ቀን 2017 ዓ.ም. የምክረ ሐሳብ አፈጻጸም ክትትል አከናውኗል።