የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባለፉት 4 ዓመታት በተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች ላይ ያቀረባቸው ምክረ ሐሳቦች በዘርፍ ተከፋፍለው የተጠቃለሉበትን ሰነድ ጥቅምት 10 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ በተካሄደ የውይይትና ርክክብ መርኃ ግብር ለባለድርሻ አካላት በይፋ አስረክቧል።

መርኃ ግብሩ ኢሰመኮ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ዘርፎች ማለትም በሲቪልና ፖለቲካዊ፣ በማኅበራዊና ኢኮኖሚ ፣ በሴቶችና ሕፃናት፣ በአካል ጉዳተኞችና አረጋውያን፣ በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች፣ ስደተኞችና ፍልሰተኞች ወዘተ መብቶች በሚያከናወናቸው የግንዛቤ ማሳደጊያ ስልጠናዎች፣ ክትትሎች፣ ምርመራዎች፣ ጥናቶች እንዲሁም ሌሎች የውትወታ ዘዴዎች አማካኝነት የሚሰጣቸው ምክረ ሐሳቦች ትግበራና ክትትል የበለጠ የሚጠናከርበትን የባለድርሻ አካላት ትብብር ለመፍጠር ያለመም ነው። በመርኃ ግብሩ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ከፍትሕ፣ ከትምህርት እንዲሁም ከሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከፌዴራልና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ከፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን፣ ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎችና ተወካዮች እንዲሁም የኢሰመኮ-ሲቪል ማኅበራት የትብብር መድረክ የሥራ ኃላፊዎችና ዓለም አቀፍ አጋር ተቋማት ተሳትፈዋል።

ሰነዱ ኢሰመኮ በተለያዩ ጊዜያት ባወጣቸው ሪፖርቶችና ሌሎች ሰነዶች ያቀረባቸው ምክረ ሐሳቦች በየዘርፉ ተከፋፍለው፣ በዓለም አቀፍና አህጉራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ከተሰጡ ምክረ ሐሳቦች እና የምክረ ሐሳቦቹ ትግበራ ከሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ጋር ተያይዘው በዝርዝር የተመላከቱበት መሆኑ ተገልጿል። ይህም ኢሰመኮ ምክረ ሐሳቦቹን ተከትሎ የዜጎች የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ እንዲሻሻል የሚያስችሉ የመፍትሄ ሥራዎችን ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትም ሆነ ከአጋር ተቋማት ጋር በጋራ በመሆን ለመሥራት የሚያግዝ መሆኑ ተመላክቷል። በየጊዜው የሚሰጡ ምክረ ሐሳቦችን በማካተት የሚዳብር መሆኑ የተገለጸው ይህ ሰነድ ሰፊ ውይይት ከተካሄደበት በኋላ፣ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እንዲረከቡት ተደርጓል።

ዶ/ር አብዲ ጅብሪል፣ የኢሰመኮ የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ እና የኢኮኖሚ መብቶች ኮሚሽነር

የኢሰመኮ የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ እና የኢኮኖሚ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል ኢሰመኮ በተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች ላይ የሰጣቸው ምክረ ሐሳቦች በዘርፍ ተከፋፍለው እና ከአፍሪካ ኅብረትና ተ.መ.ድ. የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ምክረ ሐሳቦች ጋር ተሰናስለው በዚህ መልኩ መቅረባቸው ምክረ ሐሳቦቹ በአግባቡ እንዲተገበሩ ከሚያበረክተው አስተዋጽዖ በተጨማሪ ተጠያቂነትን ለማስፈን እንደሚጠቅም አመላክተዋል።