የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ለደረሰባቸው ተጎጂዎች ተጓዳኝ ድጋፍ ለመስጠት እስካሁን እየተገበረ በሚገኘው የቅብብሎሽና ቅንጅት ማእቀፍ ላይ የተሠራውን የዳሰሳ ጥናት መነሻ በማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር የካቲት 28 ቀን 2017 ዓ.ም. ውይይት አካሂዷል። የውይይቱ ዓላማ በሥራ ላይ ያለውን የቅብብሎሽ አሠራር በተሻለ መልኩ ለማደራጀት እና ለማጠናከር በዳሰሳ ጥናቱ ግኝቶች ላይ እንዲሁም ኢሰመኮ ወደፊት ለሚተገብረው መደበኛ የቅብብሎሽ ሥርዓት ከባለድርሻ አካላት ግብአት ማሰባሰብ ነው።

በውይይቱ ለተጎጂዎች ድጋፍ የሚሰጡ ከ35 በላይ የሚሆኑ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላትን ጨምሮ በሴቶች፣ በሕፃናት፣ በአካል ጉዳተኞች እና በሌሎች ዘርፎች ላይ የሚንቀሳቀሱ ተቋማት ተሳትፈዋል።

በውይይት መድረኩም በዳሰሳ ጥናቱ የተለዩ ቁልፍ ግኝቶች የቀረቡ ሲሆን ኢሰመኮ ተጎጂዎችን ከሕግ፣ ከሥነ ልቦና፣ ከመጠለያ፣ ከማኅበራዊ ወዘተ. ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች ጋር ማገናኘት መቻሉ፤ ተጎጂዎች በተቻለ መጠን ለዳግም ጥቃት ተጋላጭ እንዳይሆኑ፤ ሰብአዊ መብቶች እንዲጠበቁ ከማድረግ አንጻር መልካም ሥራ ማከናወን መቻሉ ተጠቃሽ ናቸው። እንዲሁም የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በተቀናጀ እና በፍጥነት ምላሽ ለመስጠት ኢሰመኮ ከመቼውም ጊዜ በላይ የተጠናከረ መደበኛ የቅብብሎሽ ሥርዓት (Referral System) መዘርጋቱ በይበልጥ አስፈላጊ መሆኑ ተመላክቷል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ካነሷቸው ተግዳሮቶች መካከል በቅብብሎሽ ሥራ ላይ የሚሳተፉ ድርጅቶች የሚሰጧቸው አገልግሎቶች ዐይነቶች ግልጽ አለመሆናቸው፣ ቃል የተገቡ አገልግሎቶች በተገቢ ሁኔታ አለመፈጸማቸው፣ ባለጉዳዩ ሊያገኘው የሚገባው አገልግሎት በሚገባው ጥራት መሰጠቱ አለመጣራቱ፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ያለባቸው የሀብት ውስንነት፣ እና ለአንዳንድ ተጎጂዎች ለምሳሌ ጥቃት ለደረሰባቸው ወንዶች አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት አለመኖር ይገኙበታል። በሌላ በኩል ኢሰመኮ ጥናት ላይ የተመሠረተ መደበኛ የቅብብሎሽ ሥርዓት ከመዘርጋት ባለፈ ድጋፍ እንዲያገኙ የሚልካቸውን አቤቱታ አቅራቢዎች የሚለይበት መስፈርት፣ የቅብብሎሽ ሥርዓት መመሪያ፣ አገልግሎት ሰጪ ድርጀቶችና የሚሰጡት የአገልግሎት ዐይነት ማመላከቻ (Service Providers and Service Type Mapping) ቢዘጋጅ፣ የቅብብሎሽ ሥርዓቱ የፍትሕ ተደራሽነትን ቢያካትት እንዲሁም የቅብብሎሹን ሂደት መከታተልና የተጠቃሚዎችን አስተያየቶች መሰብሰብ የሚቻልበት አሠራር ቢዘረጋ ኢሰመኮ ለተጎጂዎች የሚሰጠውን አገልግሎት የተሻለ ሊያደርገው እንደሚችል የውይይቱ ተሳታፊዎች ገልጸዋል።

የኢሰመኮ የፕሮግራም እና አጋርነት ሥራ ክፍል ከፍተኛ ዳይሬክተር መብራቱ ገበየሁ ተጎጂዎች ከደረሰባቸው የሰብአዊ መብት ጥሰት አንጻር የሚያስፈልጋቸውን ሁሉን አቀፍ አገልግሎት ለመስጠት በሀገር አቀፍ ደረጃ የተደራጀ፣ የተቀናጀና ጠንካራ የቅብብሎሽ ሥርዓት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። አክለውም ተጎጂዎችን ያማከለና የተሻለ ጥበቃ የሚሰጥ፣ ከዳግም ጥቃት የሚጠብቅ የቅብብሎሽ እና የቅንጅት አሠራር/ሥርዓት ለመዘርጋት ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት ጋር በመቀራረብ በአጋርነት መሥራት እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።