የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከዴንማርክ የስደተኞች ምክር ቤት (Danish Refugee Council) ጋር በመተባበር የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች መብቶች በተለይም የመንቀሳቀስና መኖሪያ ቦታ የመምረጥ፣ ፍትሕ የማግኘት፣ ከሕግ አግባብ ውጪ እስር የመጠበቅ እና በግዳጅ ወደመጡበት ያለመመለስ ወይም ወደሌላ ሀገር ያለመዛወር መብቶች ላይ ትኩረት በማድረግ ኅዳር 22 እና 23 ቀን 2018 ዓ.ም. ከባለድርሻ አካላት ጋር በአዳማ ከተማ ዐውደ ጥናት አካሂዷል።
በዐውደ ጥናቱ ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ፣ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያና ከክፍለ ከተሞች ፖሊስ መምሪያዎች፣ ከኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነጻ የሕግ ድጋፍ ማእከል፣ ከፌዴራል ፍርድ ቤቶች፣ ከፍትሕ ሚኒስቴር እንዲሁም ከስደተኛ መር ድርጅቶች የተወከሉ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።

በዐውደ ጥናቱ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ስለሚመለከቱ መሠረታዊ የሕግ እና የፖሊሲ ማዕቀፎች እንዲሁም ከስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ውጭ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ያሉ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ስላሏቸው መብቶች እና ግዴታዎች ገለጻ ተደርጓል። ምዝገባ እና ሰነድ ካለማግኘት ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባ ከተማ በስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ላይ የሚደርሰውን ከሕግ አግባብ ውጪ እስር እና አስገድዶ ወደ መጡበት የመመለስ ወይም ወደ ሌላ ሀገር የማዛወር ድርጊትን ለመከላከል የሕግ አስፈጻሚ አካላት ኃላፊነት ላይ ማብራሪያ ተሰጥቷል።
በተጨማሪም በኢሰመኮና በዴንማርክ የስደተኞች ምክር ቤት ትብብር ከዚህ በፊት የተደረጉ የክትትል እና ምርመራ ግኝቶችን መሠረት በማድረግ ወቅታዊ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች መብቶች ላይ የተለዩ ተግዳሮቶች ለተሳታፊዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። ከቀረቡት አሳሳቢ ጉዳዮች ውስጥም በአንዳንድ የአዲስ አበባ ክፍለ ከተሞች በስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ላይ ከሕግ አግባብ ውጪ እስር መበራከቱና ተገቢውን ፍትሕ እያገኙ አለመሆኑ የሚጠቀስ ሲሆን ማንኛውንም ስደተኛ ወይም ጥገኝነት ጠያቂ ከሕግ አግባብ ውጭ መያዝ እና ማሰር፣ ያለፈቃዱ በግዳጅ ወደመጣበት መመለስ ወይም ወደ ሌላ ሀገር መላክ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንደሆነ አጽንዖት ተሰጥቷል።

የዐውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች እያጋጠሟቸው ያሉ ችግሮችን እና በየተቋሞቻቸው የሚያከናውኗቸውን ተግባራት በዝርዝር አጋርተዋል። በተለይም ከመጠለያ ጣቢያዎች ወደ አዲስ አበባ የሚገቡ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣት፣ ምዝገባ ባለመኖሩ ምክንያት መታወቂያ የሌላቸው (ሰነድ አልባ) ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች በከተማው ውስጥ መበራከታቸው፣ እንዲሁም በስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች አስተዳደር ላይ በሚሠሩ የመንግሥት ተቋማት መካከል ያለው ቅንጅት በሚጠበቀው ልክ አለመሆኑ በሥራቸው እንዲሁም በስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች መብቶች አያያዝ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን በማንሳት በመፍትሔዎች ላይ ትኩረት በማድረግ የተሻለ ሥራ ሊሠራ እንደሚገባ አመላክተዋል።