የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኢትዮጵያ ብቸኛ በሆነው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ በወንጀል ነክ ነገር ውስጥ ገብተው የተገኙ ሕፃናት ማቆያና ተሐድሶ ተቋም ውስጥ ያለውን የሰብአዊ መብቶች አያያዝ አስመልክቶ ባከናወነው ክትትል ግኝቶች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ግንቦት 22 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ውይይት አካሂዷል። በውይይቱ ከማቆያና ተሐድሶ ተቋሙ፣ ከፍትሕ ሚኒስቴር፣ ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን፣ ከሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ከአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ እንዲሁም ከልደታ ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽሕፈት ቤት የተውጣጡ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።

በውይይቱ በወንጀል ነክ ነገር ውስጥ ገብተው የተገኙ ሕፃናትን (ከ9 – 15 ዓመት) ከተለያዩ ክልሎች በሚቀበለው በዚህ የማቆያና ተሐድሶ ተቋም ውስጥ ጥበቃ የማግኘት፣ ቅሬታ የማቅረብ፣ የሴቶችና አካል ጉዳተኞችን ልዩ ፍላጎት ያገናዘበ መሠረታዊ አገልግሎት የማግኘት እንዲሁም የትምህርት፣ የጤና፣ የጨዋታና የመዝናኛ አገልግሎቶችን የማግኘት መብቶችን ከማረጋገጥ አንጻር በክትትሉ የተለዩ ክፍተቶች እና የተጠቆሙ ምክረ ሐሳቦች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ በዚህም መሠረት የሰብአዊ መብቶች መርሖችና ድንጋጌዎችን ያከበረ እንዲሁም ዓለም አቀፍ መመዘኛዎችን ያገናዘበ አያያዝን በማረጋገጥ፣ ሕፃናቱ  በመልካም ባሕሪ ታንጸው ወደ ማኅበረሰቡ የሚቀላቀሉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ጉዳዩ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ ተቋማት ሊወስዷቸው ስለሚገቡ የመፍትሔ እርምጃዎች ምክክር ለማድረግ ተችሏል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች

የውይይቱ ተሳታፊዎች በክትትሉ የተለዩት ግኝቶች በተቋሙ ያለውን የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ በዝርዝር ያመላከቱ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ የተሰጡትን ምክረ ሐሳቦች በሚገባ ለመተግበርና የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታውን ለማሻሻል እንደሚሠሩ ገልጸዋል። በተጨማሪም ክፍተቶችን በዘላቂነት ለመፍታት በአጭር እና በረጅም ጊዜ መተግበር ያለባቸውን አስተዳደራዊና መዋቅራዊ እርምጃዎች አመላክተዋል።

የኢሰመኮ የሴቶች እና የሕፃናት መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር የምስራች ለገሰ ክትትሉ የተደረገበት የማቆያና ተሐድሶ ተቋም እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሌሎች መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በክትትሉ ለተለዩት ክፍተቶች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ምክረ ሐሳቦችን በተሻለ ቅንጅት ተግባራዊ ሊያደርጉ እንደሚገባ ገልጸዋል። አክለውም፣ “በወንጀል ነክ ነገር ውስጥ ገብተው የተገኙ ሕፃናት አያያዝን በሰብአዊ መብቶች መርሖችና ድንጋጌዎች የተቃኘ በማድረግ ከጥፋታቸው ተምረውና በመልካም ባሕሪ ታንጸው ወደማኅበረሰቡ የሚቀላቀሉበትን ሁኔታ ማረጋገጥ ይገባል” ብለዋል።