የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከ“ኢንተርናሽናል ሚዲያ ሰፖርት” (International Media Support)ጋር በመተባበር የጋዜጠኞች የሕግ ጥበቃ (ከለላ) በተለይም በምርጫ ዐውድ ውስጥ የጋዜጠኞች ደኅንነት መረጋገጥ እና የሚዲያነጻነት ጥበቃ አስፈላጊነት ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ የማጠቃለያ ውይይት በኅዳር 23 እና 24 ቀን 2018 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማአካሂዷል። የውይይት መድረኩ ሐምሌ 17 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4 ቀን 2018 ዓ.ም. በአርባ ምንጭ እንዲሁም ጥቅምት 25 ቀን 2018 ዓ.ም. በድሬዳዋ ከተሞች በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ የተካሄዱ ውይይቶች ማጠቃለያ ሲሆን፣ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት፣ የመረጃ ነጻነት እንዲሁም የጋዜጠኞች የሕግ ጥበቃ (ከለላ) ላይ ያሉ ዓለም አቀፍ እና ሀገራዊ ሕጎችን በተመለከተ የባለድርሻ አካላትን ግንዛቤ ለማሳደግ ያለመ ነው።በውይይቱ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ከአማራ፣ ከማእከላዊ ኢትዮጵያ፣ ከኦሮሚያ፣ ከሲዳማ፣ ከሶማሊ፣ ከደቡብ ኢትዮጵያ እና ከትግራይ ክልሎች የተወጣጡ የሕግ አስፈጻሚ አካላት፣ የግል እና የመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችና ማኅበራት ተሳትፈዋል።

በመድረኩ አምስት የውይይት መነሻ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።ኢሰመኮ በክትትሉ የለያቸው አበረታች እና አሳሳቢ ጉዳዮች በውይይቱ የቀረቡ ሲሆን፣ የመገናኛ ብዙኃን ነጻነት እና የመረጃ ነጻነትጥበቃን ለማጠናከር እንዲሁም የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጡ አዋጆች መኖራቸው፣ በበይነ መረብ የሚሠሩ የመገናኛ ብዙኃን ፈቃድ አግኝተው እንዲንቀሳቀሱ የሚያስችል ሕግ እና አሠራር መዘርጋቱ፣እንዲሁም የመረጃ ተደራሽነትን ለማስፋፋት ጠቀሜታ ያላቸው ዝግጅቶች በመገናኛ ብዙኃን ተቋማት በተለያዩ ቋንቋዎች መሠራታቸው በአበረታችነት ተጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል የመንግሥት ተቋማት ለመገናኛ ብዙኃን መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆን፣ በባለሙያዎች ላይ የሚፈጸም የቅድመክስ እስራት፣ ሚዛናዊነትን እና ሐሰተኛና የጥላቻ ንግግሮችን ያለማሰራጨት ኃላፊነትን በተሟላ ሁኔታ በማክበር ረገድ መገናኛብዙኃን ክፍተቶች ያሉባቸው መሆኑ እንዲሁም የግንዛቤና የሕግ ክፍተቶች መኖራቸው በተሳታፊዎች በአሳሳቢነት የቀረቡጉዳዮች ናቸው።

የውይይቱ ተሳታፊዎች

በተጨማሪም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን እና የመገናኛ ብዙኃን ነጻነትን በማረጋገጥ ረገድ ሊያከናውኗቸው የሚገቡ ተግባራት ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡ ከ7ኛው ዙር ሀገር አቀፍ ምርጫ ጋር በተያያዘ መገናኛ ብዙኃንና ጋዜጠኞች ሚዛናዊ እና ትክክለኛ ዘገባዎችን ለሕዝብ በማድረስ የዜጎችን በፖለቲካ እና በሕዝባዊ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ የማድረግእንዲሁም መረጃ የማግኘት መብቶች በማረጋገጥ በኩል የሚጠበቅባቸዉን ሚና እንዲጫወቱ፤ ከምርጫ በፊት፣ በምርጫ ወቅት እና ከምርጫ በኋላ ያሉ ጉዳዮችን በሚዘግቡበት ጊዜ ሁሉ ለመብቶቻቸው ተገቢው ጥበቃ ሊደረግ እንደሚገባ በዉይይቱተገልጿል።የኢሰመኮ የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ የማኀበራዊ እና የኢኮኖሚ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ እና መረጃ የማግኘት መብቶች ለሌሎች ሰብአዊ መብቶች መከበር ዋና ምሶሶ መሆናቸውን አስታውሰው፤ ነጻ የሲቪክ ምህዳር እናየመገናኛ ብዙኃንና ጋዜጠኞች ጥበቃ ያላቸውን ጠንካራ ትስስር በማስታወስ፣ በምርጫ ወቅት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና ጋዜጠኞች ጠንካራ ተሳትፎ ማድረግ እንዲችሉ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።