የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በግል ሥራ እና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ ሠራተኞች ላይ የተሠሩ ጥናቶችን እና የቀረቡለትን በርካታ ቅሬታዎችን መሠረት በማድረግ በግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ ሠራተኞች ሰብአዊ መብቶች አተገባበር ዙሪያ ያከናወነውን የክትትል ሥራ ሪፖርት ኅዳር 2 ቀን 2015 ዓ.ም. ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። በሪፖርቱ የተካተቱ ግኝቶች እና ምክረ ሃሳቦች አፈጻጸምን በተመለከተ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በአራት ከተሞች ማለትም በአዲስ አበባ፣ በባሕር ዳር፣ በሃዋሳ እና በጅማ ተከታታይ የምክክር መድረኮች ተካሂደዋል።
በመድረኮቹ ላይ ከፍርድ ቤቶች፣ አግባብነት ካላቸው የአስፈጻሚ አካላት፣ ከሠራተኛ ማኅበራት፣ ከአሠሪዎች፣ ከግል ሥራ እና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች፣ እንዲሁም ከሲቪል ማኅበራት የተውጣጡ አካላት ተሳትፈዋል።
በምክክር መድረኮቹ በሪፖርቱ የተለዩ የክትትል ግኝቶች እና የተሰጡ ምክረ-ሃሳቦች በኮሚሽኑ የሰብአዊ መብቶች ባለሞያዎች የቀረቡ ሲሆን በኢትዮጵያ የሠራተኞች ሰብአዊ መብቶችን የሚመለከቱ የሕግ ማዕቀፎችን የተመለከተ ገለጻ ለተሳታፊዎች ቀርቧል። የኤጀንሲ ሠራተኞች መብቶች በተለይም ምቹ የሥራ ሁኔታዎችን የማግኘት፣ እኩልነትና ከአድልዎ ነጻ የመሆን፣ የሥራ ዋስትና የማግኘት፣ ማኅበራዊ ዋስትና የማግኘት፣ የመደራጀት፣ ቅሬታ የማሰማት እንዲሁም ፍትሕ የማግኘት መብቶች እየተጣሱ እንደሆነ በመድረኮቹ ተነስቷል፡፡ እነዚህ ጉዳዮችን መሠረት በማድረግ ከሠራተኞች መብቶች ጋር በተገናኘ የሚስተዋሉ ችግሮችን እንዴት መቅረፍ ይቻላል፣ የክትትል ሪፖርቱ ከወጣ በኋላ ስለተወሰዱ እርምጃዎች እና በቀጣይም ከእያንዳንዱ ባለድርሻ አካላት ምን ይጠበቃል በሚሉ ጉዳዮች ላይ ከተሳታፊዎች ጋር ውይይት ተደርጓል።
የኢሰመኮ የሲቪል እና ፖለቲካ፣ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል በመድረኮቹ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፤ መድረኮቹ የተዘጋጁት በክትትል ሪፖርቱ የተገኙትን ግኝቶች እና የተሰጡትን ምክረ-ሃሳቦች በመተግበር የግል ሥራ እና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ ሠራተኞች የሰብአዊ መብቶችን በተሻለ ሁኔታ ተግባራዊ እንዲሆኑ ለማስቻል ያለመ እንደሆነ ገልጸው፤ ሀገሪቱ የሠራተኞች የሰብአዊ መብቶችን በሚመለከት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕገ-መንግሥት ውስጥ ከማካተትም በላይ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊና ባህላዊ መብቶች ቃል ኪዳንን፣ አግባብነት ያላቸው የዓለም ሥራ ድርጅት ስምምነቶችን እና የተለያዩ የሠራተኞች መብቶችን የሚመለከቱ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ተቀብላ ማጽደቋን አብራርተዋል። አክለውም መንግሥት እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በእነዚህ የሰብአዊ መብቶች የሕግ ማዕቀፎች ለተደነገጉት የሠራተኞች መብቶች መከበር እና መረጋገጥ እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡