የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በግንባታ ዘርፍ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ጤናማ የሥራ ሁኔታ መብት አተገባበርን አስመልክቶ ባከናወነው ክትትል ሪፖርት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ሰኔ 2 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዳማ ከተማ የውይይት መድረክ አካሄደ። በመድረኩ ከሚመለከታቸው የፌዴራል እና የክልል ተቋማት፣ በግንባታ ዘርፍ ከተሰማሩ የንግድ ድርጅቶች እና ማኅበራት፣ ከሠራተኛ ማኅበራት እና እንዲሁም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት የተውጣጡ ተወካዮች ተሳትፈዋል።
በምክክር መድረኩ በግንባታ ዘርፍ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ጤናማ የሥራ ሁኔታ መብት አተገባበርን በሚመለከት በኮሚሽኑ በአምስት ከተሞች በተደረገው ክትትል የተለዩ ግኝቶች እና የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች ቀርበዋል፡፡ በዚህም መሠረት ባለድርሻ አካላት ስለመብቱ ያላቸውን ግንዛቤ፣ የሥራ ደኅንነት እና ጤንነት መብት የአተገባበር ኀላፊነት ያለባቸውን ተቋማት ተቋማዊ አደረጃጀት፣ የአደጋ ሥጋትን ወይም በጤና ላይ ሊደርሱ የሚችሉ አሉታዊ ተጽዕኖዎችን ለመከላከል እና ለማስቀረት በአሠሪዎች የሚወሰዱ እርምጃዎችን፣ በዘርፉ ያለውን የሠራተኛ ማኅበራት እና የሠራተኞች ተሳትፎ እንዲሁም ለጉዳት ተጋላጭ ለሆኑ ሠራተኞች የሚደረግ ልዩ ጥበቃን በተመለከተ የክትትሉ ግኝቶች ለተሳታፊዎች ቀርበዋል።
በተጨማሪም የሥራ ሁኔታ ክትትል፣ ቁጥጥር እና ድጋፍ ተግባራት፣ በዘርፉ በብዛት የሚስተዋሉ አደጋዎች፣ በሽታዎች እና ምክንያቶቹ፣ በዘርፉ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ጤናማ የሥራ ሁኔታ መብትን ለማረጋገጥ የሚያግዙ መልካም ተሞክሮዎች እና ተስፋ ሰጪ ጅምሮችን የሚመለከቱ ጉዳዮችም ተነስተው ከተሳታፊዎች ጋር ውይይት ተደርጎባቸዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎችም በክትትሉ የተለዩ ችግሮችን እንዴት መቅረፍ እንደሚቻል፣ በክትትል ሪፖርቱ የቀረቡ ምክረ ሐሳቦች ስለሚተገበሩባቸው መንገዶች እና በቀጣይም ከእያንዳንዱ ባለድርሻ አካል ምን እንደሚጠበቅ ያላቸውን አስተያየት ሰጥተዋል።
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የኢሰመኮ የሲቪል፣ የፖለቲካ እና ማኅበራዊ-ኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል “በዘርፉ ከአደጋ ነጻ የሆነና ጤናማ የሥራ ሁኔታ መብትን መጠበቅ፣ ማክበር እና ማስከበርን በተመለከተ ባለድርሻ አካላትን አስተባብሮ እና አቀናጅቶ የሚመራ ጠንካራ ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ” መሆኑን አስረድተዋል።