በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ እና ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ የተመራ ቡድን የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ከሚያስተዳድራቸው 6 ማረሚያ ቤቶች መካከል በቃሊቲ ከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ማእከል በተለምዶ “አባ ሳሙኤል” በመባል በሚጠራው ማረሚያ ቤት የካቲት 11 ቀን 2017 ዓ.ም. የሥራ ጉብኝት አድርጓል።  ቡድኑ በጉብኝቱ የተመለከታቸውን በጎ ጅማሮዎች፣ የታዘባቸውን ቀሪ ክፍተቶች እና ኢሰመኮ ከዚህ በፊት በማረሚያ ቤቶች ባካሄደው የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል በለያቸው ግኝቶች መነሻነት የሰጣቸው ምክረ ሐሳቦች አፈጻጸም ላይ ከፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ ጋር ተወያይቷል።

ከጉብኝቱ በኋላ በተካሄደ ውይይት ከታራሚዎች ቁጥር አንጻር በቂ ማረፊያ ክፍሎች፣ አልጋ እና ፍራሽ፣ መጸዳጃ እና መታጠቢያ ክፍሎች፣ የተሟላ ማብሰያ ክፍሎች እና ታራሚዎች የሚንቀሳቀሱበት ሰፊ ስፍራ ያለው መሆኑ ተገልጿል።  እንዲሁም ቤተ መጻሕፍት፣ ነጻ የሕግ ድጋፍ እና የሕክምና አገልግሎት መስጫ ማእከልን ጨምሮ ታራሚዎች የቀለምና የሙያ ዕውቀት የሚገበዩባቸው የትምህርትና የስልጠና ማእከላትን ያሟላ በመሆኑ ማረሚያ ቤቱ ከመሠረተ ልማት አኳያ ለሌሎች የፌዴራልና የክልል ማረሚያ ቤቶች ማሳያ ሊሆን እንደሚችል ተጠቅሷል።

በሌላ በኩል በማረሚያ ቤቱ የንጹሕ ውሃ አቅርቦት አነስተኛ መሆን እና በቂ የምግብ አቅርቦት አለመኖር በታራሚዎች አስቸኳይ መፍትሔ ሊሰጣቸው ከሚገቡ ችግሮች መካከል የተጠቀሱ ናቸው።  በዚህም ታራሚዎች የራሳቸውንም ሆነ የማረሚያ ቤቱን ንጽሕና ለመጠበቅ መቸገራቸውን ጠቁመዋል። በተጨማሪም ታራሚዎች አልፎ አልፎ በሆስፒታሎች እና በፍርድ ቤቶች ቀጠሮ በተሰጣቸው ቀን አጃቢ የለም በሚል ምክንያት የማይቀርቡባቸው ሁኔታዎች እንዳሉ ተናግረዋል።

የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል የኑስ ሙሉ የማረሚያ ቤቱ መሠረተ ልማት ታራሚዎች ከዚህ በፊት ከነበሩበት ማእከል በበርካታ መስፈርቶች የሚሻል እንደሆነ ገልጸው በታራሚዎች የተነሳው የውሃ አቅርቦት ችግርን ለመፍታት ከፌዴራል ውሃ ሥራዎች ድርጀት ጋር የሥራ ውል የተገባ እና የከርሰ ምድር ውሃ ለማውጣት ቁፋሮ ሊጀመር መሆኑን አብራርተዋል።  ከምግብ አቅርቦት ጋር ለተነሱ ችግሮች ለአንድ ታራሚ የቀን ወጪ በመንግሥት የተመደበ በጀት 35 ብር ብቻ መሆኑን፤ ከወቅታዊ የገበያ ዋጋ መጨመር ጋር ተያይዞ የመጣ ችግር እንደሆነ፣  የማረሚያ ቤቱ የሰው ኃይል ቁጥር ማነስ እና የመርኃ ግብር መደራረብ የአጃቢዎች እጥረት እንዲፈጠር በማድረጉ ታራሚዎች በቀጠሯቸው ፍርድ ቤት እና ሆስፒታል እንዳይሄዱ ተግዳሮት መሆኑን አመላክተዋል። የበጀት ማስተካከያ ለምክር ቤቱ አቅርበው ምላሽ በመጠበቅ ላይ መሆናቸውን በመጠቆም ታራሚዎች ሰብአዊ መብቶቻቸው ተከብረው፣ ታርመውና ታንጸው ከማኅበረሰቡ ጋር እንዲቀላቀሉ ለማድረግ ኢሰመኮ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል የሪጅን ዳይሬክተር ሰላማዊት ግርማይ (በግራ) እና የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ (በቀኝ)

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ በበኩላቸው ኢሰመኮ እና ማረሚያ ቤቶች ታራሚዎች ሰብአዊ መብቶቻቸው ተከብረውና ተጠብቀው ለሀገራዊ እድገት፣ ሰላም እና ማኅበራዊ መስተጋብር በጎ አስተዋጽዖ እንዲያበረክቱ ለማስቻል ለአንድ ዓላማ የሚሠሩ መሆናችውን አስረድተው ኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ክትትል ማድረጉን፣ በግኝቶች መነሻነት ለሚመለከታቸው አስፈጻሚ አካላት ምክረ ሐሳብ መስጠቱን እና ለአፈጻጸሙም ውትወታ ማድረጉን በትብብር መርሕ እንደሚቀጥል ገልጸዋል። ዋና ኮሚሽነር አክለውም “የሰብአዊ መብቶች ሥራ የባለድርሻ አካላትን ትብብርና ቅንጅት የሚጠይቅ በመሆኑ ባለድርሻ አካላት በዚሁ እሳቤ በትጋት ሊሠሩ ይገባል” ብለዋል።