የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በሰኔ ወር 2017 ዓ.ም. በቃሊቲ የሴቶች ማረፊያ እና ማረሚያ ማእከል፣ በቂሊንጦ የቀጠሮ ማረፊያ ማእከል፣ በከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ቤት እና በዝዋይ ማረሚያ ቤት የሚገኙ ታራሚዎች ታራሚዎች እና የጊዜ ቀጠሮ እስረኞች የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ ባከናወነው ክትትል የተለዩ ግኝቶችና ምክረ ሐሳቦችን መሠረት በማድረግ ሐምሌ 29 ቀን 2017 ዓ.ም. ከባለድርሻ አካላት ጋር በቢሾፍቱ ከተማ ውይይት አካሂዷል።




በውይይቱ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ከፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን፣ ከፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፣ ከፍትሕ ሚኒስቴር እና ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እንዲሁም ከአራቱ ማረሚያ ቤቶች የተወከሉ የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።
በውይይት መድረኩ ኢሰመኮ በ2017 በጀት ዓመት በ4 የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች የታራሚዎችን እና የጊዜ ቀጠሮ እስረኞች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ በሚመለከት ባከናወነው ክትትል የተለዩ ጠንካራ ጎኖች እና መሻሻል የሚገባቸው ጉዳዮች ቀርበው ከተሳታፊዎች ጋር ውይይት ተደርጎባቸዋል።




በክትትሉ በአዎንታዊነት ከተለዩ ግኝቶች መካከል የፌዴራል ከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ቤት ግንባታ መጠናቀቅ የታራሚዎችን አያያዝ ደረጃ ያሻሻለ መሆኑ፣ በሁሉም ማረሚያ ቤቶች የታራሚዎች እና የጊዜ ቀጠሮ እስረኞች መረጃ በዘመናዊ መልኩ እንዲደራጅ የሚያስችለው ሥርዓት (Prisoners Data Management System – PDMS) ጥቅም ላይ መዋሉ፣ በማረሚያ ቤቶቹ ታራሚዎች /የጊዜ ቀጠሮ እስረኞች/ እምነታቸውን በነጻነት እንዲያራምዱ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩ፣ ለታራሚዎች አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ የመማሪያ እና የማብሰያ ክፍሎች መኖራቸው፣ እንዲሁም የሙያ ስልጠናዎች መሰጠታቸው ለአብነት ተነስተዋል። በሌላ በኩል በማረሚያ ማእከላቱ ለአንድ ታራሚ የሚያዘው የቀን በጀት ብር 35 አነስተኛ በመሆኑ ጥራት ያለው፣ በቂና ተመጣጣኝ ምግብ ለማቅረብ አለማስቻሉ፣ የአእምሮ ሕሙማን ከሌሎቹ ታራሚዎች ጋር አብረው መታሰራቸውና የሚደረግላቸው የተለየ እንክብካቤ አለመኖሩ እንዲሁም ወቅታዊ የሆኑ የሕትመት ውጤቶች አለመቅረባቸው ሊሻሻሉ የሚገባቸው ተግዳሮቶች መሆናቸው ተገልጿል።




የውይይቱ ተሳታፊዎች ኢሰመኮ ያቀረባቸው ግኝቶች በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ያለውን የታራሚዎች የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሚዛናዊ በሆነ መንገድ የሚያሳይ መሆኑን አስረድተው ለምክረ ሐሳቦቹ አፈጻጸም ትኩረት በመስጠት እንደሚሠሩ ገልጸዋል። በተጨማሪም የተሰጡ ምክረ ሐሳቦችን በአጭር፣ በመካከለኛ እና በረዥም ጊዜ ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል የድርጊት መርኃ ግብር ተዘጋጅቷል።



በመድረኩ ኢሰመኮ እና የፌዴራል ማረሚያ ቤት አስተዳደር ኮሚሽን በዐቅም ግንባታ፣ በማረሚያ ቤቶች ሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያ እና በሰብአዊ መብቶች መከበርና ጥበቃ በጋራ መሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል። ሰነዱን የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ እና የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል የኑስ ሙሉ ፈርመዋል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የታራሚዎችን ሰብአዊ ክብር በመጠበቅ እና መሠረታዊ ፍላጎታቸውን አሟልቶ በመያዝ በአስተሳሰብና በሥነ ምግባር የተለወጡ፣ ሕግ አክባሪ፣ ሰላማዊ እና አምራች ዜጎች ሆነው ከማረሚያ ቤት እንዲወጡ በማከናወን ላይ ያሉ ሥራዎች አበረታች መሆናቸውን ጠቁመዋል። አክለውም በሁለቱ ተቋማት መካከል የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ የሰብአዊ መብቶች አያያዝንና ጥበቃን በተሻለ መንገድ ለመምራት እና ለመተግበር የሚያግዝ መሆኑን ጠቅሰው የታራሚዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ እንዲሻሻል ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።