የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሐምሌ 1 ቀን 2016 ዓ.ም. እስከ መስከረም 30 ቀን 2017 ዓ.ም. በሰብአዊ መብቶች እና በሽግግር ፍትሕ፣ በታራሚዎችና በተጠርጣሪዎች ሰብአዊ መብቶች እንዲሁም በሕፃናት መብቶች ላይ ያተኮረ ስልጠና እና የአሰልጣኞች ስልጠናዎች በተለያዩ ከተሞች ሰጥቷል።

በሰብአዊ መብቶች እና በሽግግር ፍትሕ ላይ አዲስ አበባን ጨምሮ በዲላ፣ በሰመራ እና በሻሸመኔ  ከተሞች የስልጠና መድረኮችን በማዘጋጀት ለ209 ወጣቶች፣ የሃይማኖት መሪዎች እና የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች የተሳተፉበት የአሰልጣኞች ስልጠናዎች በተለያዩ ጊዜያት ተሰጥተዋል። ስልጠናው ተሳታፊዎቹ በሰብአዊ መብቶች እና በሽግግር ፍትሕ ፅንሰ-ሐሳቦች ላይ ያላቸውን ግንዛቤ ለማጎልበትና በኢትዮጵያ ሊተገበር በታቀደው የሽግግር ፍትሕ ሂደት ውስጥ ሊኖራቸው የሚችለውን ሚና ለማስገንዘብ ያለመ ነው።

በሌላ በኩል ኢሰመኮ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከሚገኙ ማረሚያ ቤቶች ለተውጣጡ 27 የማረሚያ ቤት አመራሮችና ባለሙያዎች በሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ ከነሐሴ 27 እስከ ጳጉሜን 1 ቀን 2016 ዓ.ም. በአርባ ምንጭ ከተማ ስልጠና  ሰጥቷል። ስልጠናው የማረሚያ ቤት አመራሮችና ባለሙያዎች ከሥራቸው ጋር ተዛማጅ ስለሆኑ የሰብአዊ መብቶች ዕሴቶች ምንነት እና የታራሚዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝን በተመለከተ ዕውቀታቸውን፣ አመለካከታቸውን እና ክህሎታቸውን ለመገንባት የሚያግዝ ነው። ተሳታፊዎቹ ተግባራዊ ሊያደርጓቸው በሚገቡ መሠረታዊ የሰብአዊ መብቶች መመዘኛዎች ላይ የተሻለ ግንዛቤ እንዲያዳብሩም ዕድል ፈጥሯል።

በተመሳሳይ ስለተጠርጣሪዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ እና የፖሊስ ተጠያቂነትን በተመለከተ ለፖሊስ የሥራ ኃላፊዎች ከመስከረም 27 እስከ ጥቅምት 1 ቀን 2017 ዓ.ም. በጋምቤላ ከተማ ስልጠና ተሰጥቷል። በስልጠናው በጋምቤላ ክልል ከሚገኙ የተለያዩ ዞኖች እና ወረዳዎች የተውጣጡ 35 የፖሊስ መካከለኛ አመራሮች የተሳተፉ ሲሆን ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር በሚያውሉበት፣ የወንጀል ምርመራ በሚያደርጉበት እንዲሁም የኃይልና የጦር መሣሪያ በሚጠቀሙ ጊዜ ተግባራዊ ሊያደርጓቸው የሚገቡ መሠረታዊ የሰብአዊ መብቶች መመዘኛዎች ላይ በጥልቀት ተወያይተዋል። በተጨማሪም ኢሰመኮ በሕፃናት መብቶች ዙሪያ የሰብአዊ መብቶች ስልጠና በሲዳማ ክልል ሃዋሳ ከተማ አካሂዷል። ስልጠናው ከተለያዩ ወረዳዎች ለተወጣጡና በተለይም ሕፃናትን ከጥቃት የመከላከል ግዴታ ላለባቸው 31 የፓሊስ አባላት እና አመራሮች ከሰኔ 25 እስከ 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ተሰጥቷል። ስልጠናው የተሳታፊዎችን የሰብአዊ መብቶች ዕውቀት ከማጎልበት በተጨማሪ ሕፃናትን እንደጠለፋ ከመሳሰሉ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ለመጠበቅ እና ለመከላከል ያለመ ነው።