የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በድኅረ ግጭት ዐውድ የእናቶችና የጨቅላ ሕፃናት የጤና መብቶች ሁኔታን አስመልክቶ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባከናወነው ክትትል በተለዩ ግኝቶች እና በተሰጡ ምክረ ሐሳቦች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ሐምሌ 4 ቀን 2016 ዓ.ም. በአሶሳ ከተማ ውይይት አካሂዷል። በውይይቱ የጤና ሚኒስቴር፣ የክልሉ ጤና ቢሮ እና የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ቢሮ ኃላፊዎችን ጨምሮ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ተወካዮች ተሳትፈዋል።  

የእናቶችና የጨቅላ ሕፃናት የጤና መብቶችን በተመለከተ ኢሰመኮ ከየካቲት 11 እስከ 20 ቀን 2016 ዓ.ም. ያካሄደው ክትትል በመተከል ዞን በሚገኙ ማንዱራ፣ ቡለን፣ ዳንጉር፣ ድባጤ፣ ጉባ እና ፓዌ ወረዳዎች የጤና አገልግሎት መስጫ ማእከላት ላይ ያተኮረ ነው።  የክትትሉ ወሰን በድኅረ ግጭት ዐውድ በቅድመ ወሊድ፣ በወሊድ እና በድኅረ ወሊድ ወቅት የሚሰጡ መሠረታዊ እና አስፈላጊ የጤና አገልግሎቶች ተገኚነት (Availability of Essential Package of Health Services) የተመለከተ ነው።

በዚሁ መሠረት የክልሉ የጤና ተቋማት በመሠረተ ልማት፣ በሰው ሀብት፣ በመድኃኒት፣ በክትባትና በምግብ አቅርቦት፣ በድጋፍና በበጀት እንዲሁም በጤና ነክ መረጃ አገልግሎት ተደራሽነት ረገድ በክትትሉ የተለዩ አበረታች እርምጃዎች፣ አሳሳቢ ሁኔታዎች እና የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል።  

የውይይቱ ተሳታፊዎች

የውይይቱ ተሳታፊዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት መቆራረጥና አለመኖር፣ በክልሉ እና በአጎራባች ክልሎች በሚከሰቱ ግጭቶች ምክንያት የሚዘጉ መንገዶች ለእናቶችና ጨቅላ ሕፃናት አስፈላጊውን እርዳታ ለመስጠት ተጨማሪ ተግዳሮት መሆናቸውን አንስተዋል። በክትትሉ የተለዩ ግኝቶች በክልሉ ሌሎች አካባቢዎች በሚገኙ የጤና ተቋማትም የሚስተዋሉ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ኢሰመኮ በእናቶችና ጨቅላ ሕፃናት የጤና መብቶች  ላይ ክትትል ማከናወኑ አበረታች መሆኑን ገልጸው የፌዴራል እና የክልሉ መንግሥት በችግሩ ልክ ትኩረት እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።    

በምክክር መድረኩ የተገኙት የኢሰመኮ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአካል ጉዳተኞችና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ “በድኅረ ግጭት ዐውድ ክትትል በተደረገባችው ጤና ተቋማት ያለው የእናቶችና የጨቅላ ሕፃናት የጤና መብቶች ሁኔታ የመንግሥት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት ልዩ ድጋፍ ያስፈልገዋል” ብለዋል። አያይዘውም  አስፈላጊውን የእናቶችና የጨቅላ ሕፃናት ጤና አገልግሎት ለመስጠት ከፍተኛ ተግዳሮት የሆኑት የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እና በአጎራባች ክልሎች የሚስተዋለው የጸጥታ ችግር የመንግሥትን አፋጣኝ ምላሽ የሚፈልግ መሆኑን ገልጸዋል። ኢሰመኮ በክልሉ ያለውን የጤና መብቶች ሁኔታ ለማሻሻል ጉዳዮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የሚያደርገውን ውትወታ  እንደሚቀጥልም ኮሚሽነሯ ተናግረዋል።