የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ያለውን አጠቃላይ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ በተመለከተ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እና ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች ጋር ኅዳር 24 ቀን 2018 ዓ.ም. በአሶሳ ከተማ ውይይት አካሂዷል። ውይይቱ ኢሰመኮ በክልሉ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ላይ በተለያዩ ጊዜያት ባካሄዳቸው ክትትሎችና ምርመራዎች የደረሰባቸውን ግኝቶች በማቅረብ መልካም እመርታዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እና በአሳሳቢ ጉዳዮች ላይ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ለመወትወት ያለመ ነው። በውይይቱ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አሻድሊ ሃሰንን ጨምሮ የክልሉ ምክር ቤት ዋና እና ምክትል አፈ ጉባኤ፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት፣ የፍትሕ ቢሮ ኃላፊ፣ የሰላምና ጸጥታ ም/ቢሮ ኃላፊ እንዲሁም የክልሉ ፖሊስ፣ ማረሚያ ቤቶች እና አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን እና የሴቶች፣ ሕፃናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች

በመድረኩ ኢሰመኮ በክልሉ ባደረጋቸው ክትትሎችና ምርመራዎች የተለዩ ግኝቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። የክልሉ መንግሥት ከታጠቁ ኃይሎች ጋር ባደረገው የሰላም ስምምነት የሰዎች ሞት፣ የአካል ጉዳት እና መፈናቀል መቀነሱ፤ በማዕድን እና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ለሰላም ተመላሾች የሥራ ዕድል መፈጠሩ፤ የክልሉ መንግሥት ስደተኞችን ለመቀበል ያለው ዝግጁነት፤ የተሻለ የተፈናቃዮች እያያዝ መኖሩ ወደ ቀያቸው መለስ መጀመራቸው፤ በሴቶችና ሕፃናት መብቶች ላይ የግንዛቤ ማሳደጊያ ሥራዎች መሠራታቸው እና ለጾታዊ ጥቃት ተጎጂዎች ማገገሚያና ተሐድሶ ማእከል መቋቋሙ በምልካም እመርታነት ተገልጸዋል።

በተመሳሳይ በክልሉ የዲሲፕሊን ጉድለት የተገኘባቸው የጸጥታ አካላትን ተጠያቂ ማድረግ መጀመሩ፤ ያላግባብ የታሰሩ ሰዎችን መልቀቅ መጀመሩ፤ በፖሊስ ጣቢያዎች የማቆያ ክፍሎች ንጽሕናና የንጹሕ ውሃ አቅርቦት መሻሻሉ፤ ተጠርጣሪዎችን በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት የማቅረብ ሂደት ተጠናክሮ መቀጠሉ፤ በማረሚያ ቤት የለሊት ሕክምና አገልግሎት መጀመሩ፣ የታራሚዎች የቀን ምግብ በጀት ከ41 ብር ወደ 65 ብር መሻሻሉ እና ለታራሚዎች የሥራ ዕድል መፈጠሩ አበረታች መሆኑ ተጠቅሷል።

በሌላ በኩል የተራዘመ የቅድመ ክስ እስራት መኖሩ፣ የዋስትና መብት በወቅቱ አለመተግበሩ፤ አልፎ አልፎ በፍትሐብሔር ጉዳይ ሰዎችን ማሰር፣ ፖሊስ ጣቢያዎች የምግብ በጀት እና የሕክምና አገልግሎት አለመኖር፣ የታራሚ ክፍሎች መጨናነቅ፣ በቂ የውሃ፣ የሕክምና ባለሙያና የመድኃኒት አቀርቦት አለመኖር፤ ታራሚዎችን ከጾታ ውጪ በእስራት መጠን፣ ዓይነት እና ዕድሜ ለይቶ አለመመደብ የተመለከቱ ጉዳዮች በቂ ትኩረት እና እርምት እንደሚፈልጉ ቀርቧል።

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አሻድሊ ሃሰን ኢሰመኮ በዝርዝር ያነሳቸው የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮችን በበጎ እንደሚመለከቷቸው ገልጸው በጥንካሬ የቀረቡትን በማስቀጠል እንዲሁም ሊስተካከሉ የሚገቡ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮችን በተሰጡ ምክረ ሐሳቦች መሠረት ምላሽ ለመስጠት ክልሉ እንደሚሠራ ገልጸዋል። አክለውም ኢሰመኮ በክልሉ ለተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሰብአዊ መብቶች ጉድዮችን በተመለከተ ግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን በመስጠት ክልሉን እንዲያግዝ ጠይቀዋል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ክልሉ ታጣቂዎችን ወደ ሰላማዊ ኑሮ በመመለስ እና ተፈናቃዮችን በተሻለ ሁኔታ በመያዝ የሚበረታታ ተግባር ማከናወኑን ጠቅሰው አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ግጭቶችና ጥቃቶች ዳግም እንዳይከሰቱ ጠንካራ የቅድመ መከላከል ሥራ እንዲሠራ፤ የስደተኞች፣ የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች እና የሕፃናት መብቶች ሁኔታ ተገቢው ትኩረት እንዲሰጠው፤ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ፈጻሚዎችን በመለየት ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ሥራዎች እንዲከናወኑ፤ በማረሚያ ቤቶች እና በፖሊስ ጣቢያዎች ያሉ ሰዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ እንዲሻሻል ለማድረግ የሚያስችሉ እርምጃዎች እንዲወሰዱ፤ ተጠርጣሪዎች ለተራዘመ ቅድመ ክስ እስራት የሚዳረጉበት ሁኔታ እንዲታረም እንዲሁም የተጠርጣሪዎችና የተከሰሱ ሰዎች የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብት በተሟላ ሁኔታ እንዲተገበር አሳስበዋል። ክልሉ እያደረገ ያለውን ጥረት እንደአስፈላጊነቱ የፌዴራል መንግሥት እንዲደግፍም ጠይቀዋል። አያይዘውም ኢሰመኮ በክልሉ የሚያከናውናቸውን የሰብአዊ መብቶች ስልጠና፣ ግንዛቤ ማስጨበጥ፣ የክትትል፣ የምርመራና የውትወታ ሥራዎችን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል።