የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በድኅረ ጦርነት ዐውድ የእናቶች እና የጨቅላ ሕፃናት የጤና መብቶች ሁኔታን አስመልክቶ ከየካቲት 11 እስከ 23 ቀን 2016 ዓ.ም. በትግራይ ክልል ባከናወነው ክትትል የተለዩ ግኝቶች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ግንቦት 29 ቀን 2016 ዓ.ም. በመቐለ ከተማ ውይይት አካሂዷል። በውይይቱ የጤና ሚኒስቴር እና ብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽንን ጨምሮ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፌዴራል እና የክልሉ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ተወካዮች ተሳትፈዋል።

በውይይቱ ኢሰመኮ በድኅረ ጦርነት ዐውድ የእናቶች እና የጨቅላ ሕፃናት መብቶችን በተለይም የቅድመ ወሊድ፣ የወሊድና የድኅረ ወሊድ ወቅት መሠረታዊ እና አስፈላጊ የጤና አገልግሎቶች ተገኝነትን (availability of essential package of health services) በተመለከተ በክትትሉ የለያቸውን ግኝቶች አጋርቷል። በዚሁ መሠረት በየደረጃው ያሉ የጤና ተቋማት መሠረተ ልማት፣ የሰው ሀብት፣ የመድሃኒት፣ የክትባትና የምግብ አቅርቦት፣ የድጋፍና የበጀት ተገኝነት እንዲሁም ተደራሽነት ረገድ ያሉ አበረታች እርምጃዎች እና አሳሳቢ ሁኔታዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በተጨማሪም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተሰጡ ምላሾች፣ ኢሰመኮ ባቀረባቸው ምክረ ሐሳቦች እንዲሁም ተፈጻሚነታቸውን ለማረጋገጥ በሚደረጉ የውትወታ ስልቶች ላይ ምክክር ተደርጓል። የውይይቱ ተሳታፊዎች ኢሰመኮ በጉዳዩ ላይ የሰብአዊ መብቶች ክትትል ማከናወኑ አበረታች መሆኑን ገልጸው ለክትትል ሪፖርቱ ጠቃሚ ግብአት የሚሆኑ አስተያየቶችን ሰጥተዋል።

የኢሰመኮ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ “በትግራይ ክልል በድኅረ ጦርነት ዐውድ ያለው የእናቶች እና የጨቅላ ሕፃናት ሞት እንዲሁም የጤና እክል ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ እና መንግሥትን ጨምሮ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ርብርብ የሚጠይቅ ነው” ብለዋል። አክለውም ኢሰመኮ የምክረ ሐሳቦቹን ተፈጻሚነት እንደሚከታተል እና የውትወታ ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።