የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሚያዝያ 19 እና 20 ቀን 2015 ዓ.ም. በወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ ለሚያልፉ ሰዎች የሚሰጥ ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ተደራሽነትና ጥራትን አስመልክቶ አካሂዶት ከነበረው ሀገራዊ ኮንፈረንስ የቀጠለ የባለሙያዎች ውይይት ጥቅምት 1 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ አካሂዷል።
ኢሰመኮ የባለሙያዎች ውይይቱን ያካሄደው ባለፈው ዓመት በተከናወነው ሀገራዊ ኮንፈረንስ ማብቂያ ላይ የተቀረጸውን የድርጊት መርኃ ግብር ፈትሾ እና አሻሽሎ ወደ ሥራ ለማስገባት በማለም ነው። ይህንን ሂደት በዓለም አቀፍ ደረጃ ካሉ በጎ ተሞክሮዎች እና ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎቶችን ውጤታማነት ለመገምገም ከሚጠቅሙ የንድፈ-ሐሳብ ማዕቀፎች አንጻር ለመፈተሽ የባለሙያዎቹ አስተዋጽዖ ከፍተኛ መሆኑን በውይይቱ ተመላክቷል። በውይይቱ 28 ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት የሚሰጡ የሙያ ማኅበራት፣ በሕግ ት/ቤቶች ውስጥ የሚገኙ የሕግ ድጋፍ መስጫ ማእከላት እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች የተሳተፉ ሲሆን ከነዚህም ግማሹ ሴቶች ናቸው።
በመድረኩ የኮሚሽኑ አጋር የሆነው የፕሮጀክት ኤክስፔዳይት ጀስቲስ (Project Expedite Justice-PEJ) ባለሙያዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ተሞክሮና አግባብነት ያላቸው የንድፈ-ሐሳብ ማዕቀፎችን በመጠቀም የተለያዩ ሀገራትን ልምድ በመውሰድ ከሕግ ድጋፍ አሰጣጥ መርሖች፣ የፖሊሲ ማዕቀፍ እንዲሁም የአወቃቀር አማራጮች እና የዐውድ ትንተና ላይ ያተኮረ የመነሻ ሐሳብ አቅርበው ውይይት ተደርጓል። በኢትዮጵያ የሚሰጠው ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ተደራሽነት፣ ጥራት፣ ትስስርና ቅንጅትን እንዲሁም ዘላቂነትን ለማሻሻል ሊወሰዱ የሚገባቸው ተግባራትን የመለየትና የማቀድ ሥራ ተሠርቷል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች ፍትሕ ሚኒስቴር ያወጣው ነጻ የሕግ ድጋፍ ስትራቴጂ በመጽደቁ በኢሰመኮ አስተባባሪነት እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ከስትራቴጂው ትግበራ ጋር ሊቀናጁ እንደሚገባ አስገንዘበዋል። ይህንን ሂደት በዓለም አቀፍ ደረጃ ካሉ በጎ ተሞክሮዎች እና ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎቶችን ውጤታማነት ለመገምገም ከሚጠቅሙ የንድፈ-ሐሳብ ማዕቀፎች አንጻር ለመፈተሽ የባለሙያዎቹ አስተዋጽዖ ከፍተኛ መሆኑን በውይይቱ ተመላክቷል።
የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ በዚህ ውይይት በአገልግሎት ሰጭ ተቋማት የዳበረው መርኃ ግብር ፍትሕ ሚኒስቴር ባወጣው ነጻ የሕግ ድጋፍ ስትራቴጂያዊ ዕቅድ መሠረት ወደፊት የሚቀረጹ ተግባራዊ እርምጃዎችን የሚያጠናክር ነው ብለዋል። አክለውም መርኃ ግብሩ ከሀገራዊ ጥረቱ ጎን ለጎን ጥራቱን የጠበቀ ነጻ የሕግ ምክር አገልግሎትን በተለይ በወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ውስጥ ለሚያልፉ በተለያዩ የሀገሪቷ ክፍል ለሚገኙ የማኅበረሰቡ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ ኮሚሽኑና ሌሎች አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ያላቸውን ድርሻ የሚጠቁም እንደሆነ በመግለጽ በቀጣይ በወንጀል ሥርዓት ሂደት ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎቶች ያላቸው ተደራሽነትና ጥራትን አስመልክቶ ሀገራዊ ኮንፍረንስ እንደሚዘጋጅ ጠቁመዋል።