የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ያለውን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ መከታተሉን የቀጠለ ሲሆን፣ በተለይም እገታን በሚመለከት የቀረቡለትን አቤቱታዎች መነሻ በማድረግ እንዲሁም በራሱ ተነሳሽነት ተጎጂዎችን፣ የተጎጂ ቤተሰቦችን፣ ምስክሮችን እንዲሁም የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን በማነጋገር በጉዳዩ ላይ ክትትልና ምርመራ ሲያደርግ ቆይቷል።
በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ከተራዘሙ የትጥቅ ግጭቶች ጋር ተያይዞ በአንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠረው የሕግ ማስከበር እና የመንግሥት መዋቅር መላላት ሳቢያ በሰላማዊ ሰዎች ላይ በታጣቂ ኃይሎች፣ ለዘረፋ በተደራጁ ቡድኖች እንዲሁም በአንዳንድ የመንግሥት የጸጥታ አካላት አባሎች የሚፈጸሙ እገታዎች ተባብሰውና ተስፋፍተው የቀጠሉ መሆኑን የኢሰመኮ የክትትልና ምርመራ ውጤት ያመላክታል። አጋቾች ሰላማዊ ሰዎችን በአብዛኛው በጉዞ (ትራንስፖርት) ላይ እያሉ አንዳንዴም ከመኖሪያ ቤታቸው ወይም ከሥራ ቦታቸው አግተው ወዳልታወቀ ቦታ በመውሰድ ከፍተኛ የማስለቀቂያ ገንዘብ ክፍያ ይጠይቃሉ። ገንዘብ መክፈል ያልቻሉ በርካታ ታጋቾች ግድያን ጨምሮ በርካታ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ተፈጽሞባቸዋል። እገታው በአብዛኛው እንደ ገቢ ማስገኛ የተወሰደ መሆኑን፤ በተደጋጋሚ፣ በተንሰራፋና በተደራጀ መልኩ እንደሚፈጸም፤ አልፎ አልፎም እንደ በቀል፣ ለፖለቲካ ዓላማ ወይም የታገተ ሌላ ሰውን ለማስለቀቅ በሚል በአጸፋ መልኩ የሚፈጸም መሆኑን ለመረዳት ተችሏል። ይህም በሲቪል ሰዎች መሠረታዊ መብቶችና ነጻነቶች በተለይም በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደኅንነት፣ የንብረት መብት እና የመዘዋወር ነጻነት ላይ ጥሰት የሚያደርስ እንዲሁም በታጋቾችና ቤተሰቦቻቸው ላይ ከፍተኛ ሥነ ልቦናዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት የሚያስከትል እና ለተራዘመ ጊዜ በፍርሃት እና በሥጋት ውስጥ እንዲኖሩ የሚያደርግ ነው። በተጨማሪ ታጋች ሴቶች ለአስገድዶ መደፈር እና ለተለያየ ጾታዊ ጥቃት ይዳረጋሉ። በማኅበረሰቡ ደኅንነት እና ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ መብቶች እንዲሁም በሕግ የበላይነት መከበር ላይ የሚያስከትለው አሉታዊ ተጽዕኖም ከፍ ያለ ነው። ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ እንደታየው በዚህ ዐይነት መንገድ የሚገኝ ገንዘብ ለመሣሪያ ግዢ ሊውል የሚችል ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት ግጭቶቹን ሊያራዝም እንዲሁም ግጭቶቹን በዘላቂነት ለማስቆም በሚደረገው ድርድር ተግዳሮት ሊሆን ይችላል።
ኢሰመኮ በዚህ መግለጫ ያካተታቸው የእገታ ጉዳዮች ለማሳያነት ብቻ የተመረጡ ሲሆን ሌሎች በርካታ ጉዳዮችን በእገታ ሥር ለሚገኙ ተጎጂዎች እንዲሁም ከእገታ ለተለቀቁ ሰዎች እና ቤተሰቦቻቸው ደኅንነት ሲባል ይፋ ከማድረግ ተቆጥቧል። በተጨማሪም በተለያዩ ምክንያቶች ምርመራቸውና ክትትላቸው ያልተጠናቀቁ የእገታ ጉዳዮች ወደፊት ሊገለጹ ይችላሉ።
ሰኔ 25 ቀን 2016 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ገርበ ጉራቻ ከተማ አካባቢ ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በማለት በሚጠራው ቡድን (በተለምዶ ‘ኦነግ ሸኔ’) ታጣቂዎች ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ ላይ የነበሩ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶችን በማስቆም በአብዛኛው የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሆኑ መንገደኞችን አግተው ወስደዋል። ኢሰመኮ ከተለቀቁ ታጋቾች፣ ከታጋች ቤተሰቦች፣ ከአካባቢው አስተዳደር፣ ከመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና ከደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ምንጮች መረጃዎችን ሲያሰባስብ ቆይቷል። በዕለቱ እገታ ከተፈጸመባቸው መካከል አንድ የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ስለሁኔታው ስታስረዳ ታጣቂዎቹ እርሷ የተሳፈረችበትን አውቶቡስ በማስቆም ካስወረዷቸው በኋላ ብዛታቸው በግምት 15 የሚሆን የቀድሞ የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ዩኒፎርም የለበሱ፣ አብዛኞቹ እጆቻቸው ላይ ከአረንጓዴ እና ቀይ ጨሌ የተሠራ የእጅ ጌጥ ያደረጉ ታጣቂዎች ተሽከርካሪዎቹን ከበው የነበረ መሆኑን ማየቷን፤ ተሳፋሪዎች ከተሽከርካሪዎቹ ከወረዱ በኋላ በፍጥነት እየሮጡ ወደ ጫካ እንዲገቡ መታዘዛቸውን እና በዚህ ወቅት የተወሰኑት ተሳፋሪዎች በተለያየ አቅጣጫ እንደሮጡ፣ ተሽከርካሪዎቹ ከቆሙ በግምት ከ20 ደቂቃ በኋላ ከዋናው መንገድ አቅጣጫ የተኩስ ልውውጥ መስማቷን እና ታጣቂዎቹ “መከላከያ እየመጣ ነው” በማለት ሲታኮሱ የነበረ መሆኑን እና የታገቱትን ተማሪዎች እያስሮጡ ወደ ጫካ ይዘው መሄዳቸውን አስረድታለች። ታጣቂዎቹ ታጋቾቹን ለሰዓታት በጫካ ውስጥ እንዲጓዙ ካደረጉ በኋላ ስልክ እና መታወቂያዎቻቸውን መሰብሰባቸውን፣ እንዲሁም የኦሮሞ ብሔር ተወላጆችን ከሌሎች በመለየት በሁለት ቡድን ሲያደርጉ እርሷ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ነን ካሉት በግምት 40 ሰዎች ከሚገኙበት ቡድን መቀላቀሏን ገልጻለች። ይህ ከሆነ በኋላ እስከ ምሽቱ 1፡00 ሰዓት ድረስ በእግር ጉዞ መቀጠላቸውን እና አንድ የአካባቢው ነዋሪ ቤት እራት እንዲመገቡ እና እንዲተኙ ከተደረገ በኋላ በቀጣዩ ቀን ጠዋት ከወለጋ፣ ጅማ፣ አምቦ እና ሐረርጌ የመጡ ተሳፋሪዎችን በመለየት ስልክ፣ ገንዘብ እና መታወቂያቸውን በመመለስ እንዲሁም ከ300 – 500 ብር የትራንስፖርት ገንዘብ በመስጠት የለቀቋቸው መሆኑን፤ እርሷን ጨምሮ 4 ተማሪዎችን ግን ገንዘብ የመክፈል ዐቅም እንዳላቸው በማመን እንዳስቀሯቸው ከነዚህ ውስጥ 3 ተማሪዎች እስከ ሰኔ 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ እያንዳንዳቸው 150,000 ብር ከፍለው መለቀቃቸውን፣ እርሷ ደግሞ ሐምሌ 2 ቀን 2016 ዓ.ም. የተጠየቀችው 400,000 ብር ከተከፈለ በኋላ ወደ ገበያ ከሚሄዱ የአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ተቀላቅላ እንድትወጣ መደረጉን እና ወደ አዲስ አበባ መምጣቷን አስረድታለች።
በተመሳሳይ አንድ ከእገታ ያመለጠ የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የነበረውን ሁኔታ ሲያስረዳ በዕለቱ እርሱ የተሳፈረበት ተሽከርካሪ ወደ ገርበ ጉራቻ ከተማ ሲቃረብ በመንገዱ ላይ ከፊት ለፊታቸው ተማሪዎችን እና ሌሎች መንገደኞችን ያሳፈረ አውቶብስ ቆሞ በርካታ ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በማለት የሚጠራው ቡድን (በተለምዶ ‘ኦነግ ሸኔ’) ታጣቂዎች መንገደኞችን በማስወረድ ወደ ጫካ ሲያስገቧቸው እንደነበረ እና እርሱ የተሳፈረበትን አውቶብስም በማስቆም እንዲወርዱ ካደረጉ በኋላ፣ ሜዳማ እና የተወሰኑ ዛፎች ወዳሉበት አካባቢ እንዲገቡ እየመሩ እና ትእዛዝ ለመፈጸም ፈቃደኛ ያልሆኑትን ታጋቾች በዱላ በመምታት እንዲጓዙ ሲያደርጉ እንደነበረ ገልጿል። በመቀጠልም የሚሊሻ ዩኒፎርም እና ሲቪል የለበሱ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በቦታው በመድረስ ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በማለት የሚጠራው ቡድን (በተለምዶ ‘ኦነግ ሸኔ’) ታጣቂዎች ላይ ተኩስ መክፈታቸውን፣ በሁለቱ መካከል በነበረው ተኩስ ልውውጥ ወቅት እርሱን ጨምሮ በርካታ ታጋቾች በማምለጥ ወደ አስፋልት መውጣታቸውን እና ብዛታቸው በግምት 30 የሚሆኑት ወደ አዲስ አበባ በሚጓዝ መኪና ላይ መሳፈራቸውን አስረድቷል።
ኢሰመኮ ነሐሴ 3 ቀን 2016 ዓ.ም. ያነጋገራት የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ተወካይ እንዳስረዳችው በዕለቱ ከረፋዱ 5፡00 ሰዓት አካባቢ እገታ ከተፈጸመባቸው አውቶብሶች ኋላ የነበረ አውቶብስ ውስጥ ተሳፍረው የነበሩ ተማሪዎች ስልክ ደውለው ከፊት የነበሩ 2 አውቶብሶች ውስጥ የነበሩ ተማሪዎችን የታጠቁ ሰዎች ይዘዋቸው መሬት ላይ በጭቃ ለውሰዋቸው እንደተመለከቱ እና እነርሱ የነበሩበት አውቶብስም በተኩስ መካከል በፍጥነት ያመለጠ መሆኑን እንደነገሯት አስረድታለች። ታጣቂዎች ተሳፋሪዎችን በማስወረድ ወደጫካ እንዲገቡ በማድረግ ላይ ሳሉ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በቦታው ደርሰው ታጣቂዎች ላይ ተኩስ በመክፈታቸው በተፈጠረው ግርግር ውስጥ ያመለጡ 7 ተማሪዎችን ጨምሮ፣ ገንዘብ ከፍለው እንዲሁም ያለክፍያ የተለቀቁ 14 ተማሪዎችን በስልክ ማነጋገሯን እና ከእነዚህ ተጨማሪ 3 ተማሪዎች እንዳመለጡ እንደምታውቅ ለኢሰመኮ ገልጻለች። አሁንም ታግተው ያሉ ተማሪዎች ብዛት ስንት እንደሆነ በውል እንደማይታወቅ እና ተማሪዎች ከአውቶብሶቹ ከወረዱ በኋላ በተለያየ ቡድን ተከፋፍለው የተወሰዱ በመሆኑ ታጋች ተማሪዎች እራሳቸው ከነበሩበት ቡድን ውስጥ የቀሩትን ታጋቾች ብዛት እንጂ ሌላውን ቡድን ስለማያውቁ አጠቃላይ ብዛቱን ማወቅ እንዳልተቻለ፤ ሆኖም ቢያንስ 50 ተማሪዎች ስለመለቀቃቸው መረጃ እንዳላት እና ያልተለቀቁት ተማሪዎች ብዛት ከ7 እንደሚበልጥ አስረድታለች።
አንድ የታጋች ተማሪ ቤተሰብ ስለነበረው ሁኔታ ሲያስረዳ የአክስቱ ልጅ የሆነችው የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ 4ኛ ዓመት የሕግ ተማሪ ከደባርቅ ወደ አዲስ አበባ መንገድ ላይ እያለች ከባሕር ዳር ወደ አዲስ አበባ በአውሮፕላን የመጣች የትምህርት ቤት ጓደኛዋ ስልክ ደውላ የአክስቱ ልጅ ታግታ እንደተወሰደች እንደነገረችው፤ በወቅቱ ወደ ስልኳ ቢደውልም እንደማይነሳ እና በነጋታው ኅሙስ ዕለት በሌላ ስልክ ሲደውልላት “ታግተናል፤ 700,000 ብር ካልከፈልሽ አትወጭም አሉኝ፤ ለቤተሰብ ንገርልኝ” ማለቷን አስረድቷል። ከዚያ በኋላም በተለያዩ ቀናት በመደወል “ብሩ ስንት ደረሰላችሁ?” ብላ ስትጠይቅ የነበረ መሆኑን እና ቤተሰብ ከ50,000 ብር በላይ መሰብሰብ ያለመቻሉ ከተነገረ በኋላ አጋቾቹ የገንዘቡን መጠን በመጀመሪያ ወደ 500,000 ቀጥሎም 200,000 ብር ዝቅ ማድረጋቸውን እና ገንዘቡ ከተከፈለ በኋላ ሐምሌ 24 ቀን 2016 ዓ.ም. ከሌሎች ከ100,000 – 200,000 ብር ከከፈሉ 9 ሴቶች እና 2 ወንዶች ጋር መለቀቋን አስረድቷል።
ይህንን ጉዳይ በተመለከተ በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን የአካባቢው አስተዳደር አካላት አጠቃላይ የታገቱት የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ቁጥር 156 መሆኑን እና እስከ ሐምሌ 2 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ 138 ታጋቾች ተለቀው፣ 18 ታጋቾች እንደሚቀሩ ለኢሰመኮ ገልጸው የነበረ ሲሆን፣ የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ በበኩሉ ሐምሌ 3 ቀን 2016 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ ‘በሕዝብ እና መንግሥት የተቀናጀ ኦፕሬሽን’ ከታገቱት 167 ተማሪዎች መካከል 160 የሚሆኑትን ማስለቀቅ መቻሉን ገልጿል። ሆኖም እገታው ከተፈጸመ በኋላ ታጣቂዎቹ ታጋቾችን ወደ ተለያዩ ቡድኖች በመከፋፈል ወደ ገጠራማ አካባቢዎች ይዘው የገቡ በመሆኑ ምስክሮች በነበሩበት ቡድን ውስጥ የነበረውን ሁኔታ ከማስረዳት ባለፈ በሌሎች ቡድኖች ውስጥ የነበሩ ታጋቾችን ሁኔታ ሊያውቁ የማይችሉ በመሆኑ በአጠቃላይ የታገቱ፣ ገንዘብ ከፍለውም ሆነ ሳይከፍሉ የተለቀቁ እንዲሁም በወቅቱ በነበረ የተኩስ ልውውጥም ሆነ ከዚያ በኋላ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ጥረት የተለቀቁ ተማሪዎችን ቁጥር መለየት አስቸጋሪ መሆኑን ማወቅ ተችሏል። ለምሳሌ የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሐምሌ 3 ቀን 2016 ዓ.ም. ከ7 ተማሪዎች የማይበልጡ በእገታ ሥር እንደሚገኙ የገለጸ ቢሆንም ሐምሌ 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ከእገታ የተለቀቀች የአንድ ተማሪ ቤተሰብ አባል ታጋቿ ከነበረችበት ቡድን ብቻ 14 ወንዶች እና 26 ሴቶች በድምሩ 40 ሰዎች ታግተው ይገኙ እንደነበር መረዳታቸውን ገልጸዋል። በርካታ ከእገታ የተለቀቁ ተማሪዎች እንዲሁም የታጋች ቤተሰቦች ከፍ ያለ የደኅንነት ሥጋት ያለባቸው በመሆኑ ለኢሰመኮ ሙሉ መረጃዎችን ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ማስረጃ ማሰባሰቡን አስቸጋሪ አድርጎታል። በመሆኑም ይህ ሪፖርት ይፋ እስከተደረገበት ዕለት ድረስ ስንት ተማሪዎች በእገታ ሥር እንደሚገኙ እንዲሁም ምን ያክሉ በተለያየ አግባብ እንደተለቀቁ ለማረጋገጥ አልተቻለም።
በተመሳሳይ ነሐሴ 22 ቀን 2016 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ገርበ ጉራቻ ከተማ አቅራቢያ ልዩ ስሙ ቱሉ ሚልኪ በሚባል አካባቢ ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በማለት የሚጠራው ቡድን (በተለምዶ ‘ኦነግ ሸኔ’) ታጣቂዎች በጉዞ ላይ የነበረ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ በማስቆም ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ መንገደኞችን አግተው የወሰዱና ሹፌሩና ረዳቱን የገደሏቸው መሆኑን ለመረዳት ተችሏል። ኢሰመኮ በዚህ ጉዳይ ዝርዝር ሁኔታዎችን ለማወቅ የሚያደርገውን ምርመራ የሚቀጥል ይሆናል።
የካቲት 26 ቀን 2016 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል፣ ሰሜን ሸዋ ዞን፣ ደብረሊባኖስ ወረዳ ባቡ ኢተያ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ሕፃናት፣ ሴቶች እና አረጋውያንን ጨምሮ 20 ሰዎች ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በማለት በሚጠራው ቡድን (በተለምዶ ‘ኦነግ ሸኔ’) ታጣቂዎች ታግተው ከተወሰዱ በኋላ 18 ሰዎች እስከ ግንቦት 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ የተለያየ መጠን ያለው ገንዘብ በመክፈል መለቀቃቸውን እንዲሁም 2 ታጋቾች ከግንቦት 10 እስከ 22 ቀን 2016 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ እያንዳንዳቸው 120,000 ብር በመክፈል መለቀቃቸውን ለማወቅ ተችሏል።
ሰኔ 25 ቀን 2016 ዓ.ም. በግምት ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት አካባቢ የምሥራቅ ወለጋ ዞን ዲጋ ወረዳ ዲዴሳ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ 2 ሰዎች (ወንዶች) በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በማለት በሚጠራው ቡድን (በተለምዶ ‘ኦነግ ሸኔ’) ታጣቂዎች ከመኖሪያ ቤታቸው ተወስደው ለ1 ወር ታግተው ከቆዩ በኋላ ለእያንዳንዳቸው 100,000 ብር ተከፍሎ ሐምሌ 25 ቀን 2016 ዓ.ም. ተለቀዋል። በተመሳሳይ በዚሁ ወረዳ ጉዳቱ አርጆ ከተማ ቀበሌ 2 አስተዳደር ሰኔ 24 ቀን 2016 ዓ.ም. በግምት ከረፋዱ 5፡00 ሰዓት አካባቢ ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በማለት በሚጠራው ቡድን (በተለምዶ ‘ኦነግ ሸኔ’) ታጣቂዎች አንድ ሰው ከመንገድ ላይ ከታገተ በኋላ ሐምሌ 27 ቀን 2016 ዓ.ም. መጠኑ ያልታወቀ ገንዘብ ተከፍሎ ከእገታ ተለቋል።
በሰኔ ወር 2016 ዓ.ም. የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ሰደን ሶዶ ወረዳ አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ በቀለ ካቻ ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በማለት በሚጠራው ቡድን (በተለምዶ ‘ኦነግ ሸኔ’) ታጣቂዎች ታግተው ቤተሰቦቻቸው ለማስለቀቂያ ገንዘብ እንዲከፍሉ ተጠይቀው ገንዘቡ ከተከፈለ ከቀናት በኋላ ተገድለው ተገኝተዋል።
ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም. በአማራ ክልል ሰሜን ጎጃም ዞን ደቡብ ሜጫ ወረዳ በሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ ‘ፋኖ’) “ከዚህ በፊት የሀገር መከላከያ ሰራዊት ወደ አካባቢው ሲገባ መንገድ አሳይታችኋል፤ ሰዎችን ጠቁማችሁ አስይዛችኋል እንዲሁም የሰጠናችሁን ማስጠንቀቂያ በመተላለፍ ለፖለቲካ ሥራ ባሕር ዳር ከተማ ድረስ በመሄድ ስብሰባ ተሳትፋችኋል” በማለት 17 የአካባቢው ነዋሪዎችን ይዘው ገርጨጭ ከተማ ውስጥ አንበርክከው እንዲጓዙ እንዳደረጓቸው፤ በማግስቱ ሐምሌ 16 ቀን 2016 ዓ.ም. ከእነዚህ ውስጥ 4 ሰዎች (1 ሴት እና 3 ወንዶች (2 የሀገር ሽማግሌዎችና 1 የወረዳው ቤተ ክህነት ተወካይ ቄስ)) ተገድለው አስከሬናቸው ተጥሎ እንደተገኘ እና የቀሩት ሰዎች ደግሞ ገንዘብ በመክፈል ከቀናት በኋላ እንደተለቀቁ ኢሰመኮ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች አስረድተዋል።
ሐምሌ 19 ቀን 2016 ዓ.ም. ምሽት ላይ የአማራ ክልል አድማ ብተና ዩኒፎርም የለበሱ ማንነታቸው ያልታወቀ የታጠቁ ሰዎች በባሕር ዳር ከተማ የሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዓለ እግዚአብሔር ቅርንጫፍ 3 ሠራተኞችን በየመኖሪያ ቤታቸው በመሄድና በማገት በፒካፕ መኪና ጭነው ከወሰዷቸው በኋላ ሐምሌ 20 ቀን 2016 ዓ.ም. በባሕር ዳር ከተማ ቀበሌ 16 በሚገኘው ሜዳ ላይ እጅ እና እግራቸውን ታስረው ተጥለው መገኘታቸውን ለመረዳት ተችሏል። እገታው ዒላማ ያደረገው የቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ፣ ኦዲተር እና ካሸር የባንኩን ጥሬ ገንዘብ የሚቆጣጠሩ እና ቁልፍ የሚይዙ በመሆናቸው አስገድደው ባንኩን እንዲከፍቱ በማድረግ በባንኩ የነበረውን ጥሬ ገንዘብ ለመውሰድ እንደነበር ኢሰመኮ ያነጋገራቸው የመረጃ ምንጮች አስረድተዋል። ይሁንና እገታው እንደተፈጸመ መረጃው ወዲያውኑ ለሚመለከታቸው አካላት በመድረሱ እና የጸጥታ ኃይል በመሰማራቱ ዝርፊያውን ማስቀረት እንደተቻለ እና ታጋቾቹም በማግስቱ መገኘታቸውን ለመረዳት ተችሏል።
ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም. Action for Social Development and Environmental Protection Organization (ASDEPO) የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት 4 ሠራተኞች በሰሜን ወሎ ዞን መቄት ወረዳ የሚሠሩትን ሥራ ወደ ሌላኛው የሰሜን ወሎ ዞን ወረዳ ዳውንት ለማስፋፋት በሚካሄድ የዳሰሳ ጥናት ተሰማርተው በነበረበት ወቅት ኩርባ ከተማ ከተኙበት ክፍል በታጠቁ ሰዎች በሌሊት ታፍነው ከተወሰዱ በኋላ አሠሪው ከአጋቾች ጋር ባደረገው ተደጋጋሚ የስልክ ውይይት በአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች እገዛ 3 ታጋቾችን ማስለቀቅ የተቻለ ቢሆንም አቶ ያሬድ መለሰ የተባለው ሠራተኛ ግን ታግቶ እንደቆየ እና የሀገር መከላከያ ሰራዊት ወደ አካባቢው መንቀሳቀሱን ተከትሎ አጋቾች ሠራተኛውን ከአካባቢው ይዘውት እንደሄዱና በጥይት ተገድሎ ነሐሴ 3 ቀን 2016 ዓ.ም. አስክሬኑ እንደተገኘ ለማወቅ ተችሏል። አጋቾች ከአሠሪው ጋር በነበራቸው የስልክ ልውውጥ ገንዘብ እንዲከፈላቸው ሲጠይቁ እንደነበር ኢሰመኮ ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለማወቅ ችሏል።
ሰኔ 28 ቀን 2016 ዓ.ም. በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውሃ ከተማ 4 የወርልድ ቪዥን የጤና ባለሙያዎች (3 ወንዶች እና 1 ሴት) ለሕክምና ሥራ ከኩመር ወደ አውላላ የስደተኞች ካምፕ በመጓዝ ላይ እያሉ ማንነታቸው ባልታወቀ ታጣቂዎች ታግተው ተወስደዋል። ከታጋቾቹ መካከል 1 ሴት ታጋች በድካም ምክንያት መጓዝ ባለመቻሏ በታጣቂዎች ከተደበደበች በኋላ ጥለዋት እንደሄዱ፣ ቀሪዎቹ 3 ወንዶች ለአጋቾች ገንዝብ ከፍለው ከሳምንታት እገታ በኋላ እንደተለቀቁ ለመረዳት ተችሏል።
ሰኔ 28 ቀን 2016 ዓ.ም. በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ ዳስ ጉንዶ ቀበሌ ጉንደዶ በተባለ ቦታ ላይ ማንነታቸው ያልታወቀ የታጠቁ ሰዎች በእርሻ ሥራ ላይ ተሰማርተው የነበሩ 25 ሰዎችን አግተው ወደ ጉንዶ በረሃ ከወሰዷቸው በኋላ 22 ታጋቾች ሲያመልጡ የተቀሩት 3 ሰዎች ደግሞ እያንዳንዳቸው 150,000 ብር ከፍለው ሐምሌ 14 ቀን 2016 ዓ.ም. እንደተለቀቁ የታጋች ቤተሰቦች አስረድተዋል።
ሚያዝያ 22 ቀን 2016 ዓ.ም. በምዕራብ ጎንደር ዞን የመተማ ወረዳ ሚሊሻዎች 4 የመተማ ወረዳ መቃ ቀበሌ ነዋሪዎችን አግተው ወደ ያልታወቀ ቦታ ከወሰዷቸው በኋላ 2 ሰዎችን ሚያዝያ 24 ቀን 2016 ዓ.ም. የለቀቋቸው ሲሆን፣ ቀሪዎቹን 2 ታጋቾች ደግሞ ‘ልጃችሁ የእኛን ዘመዶች አግቷል’ በሚል ለቀናት አግተው እንዳቆዩዋቸው እና ግንቦት 2 ቀን 2016 ዓ.ም. ከእገታው እንዳመለጡ ታጋቾች አስረድተዋል።
በዓለም አቀፉ የሲቪል እና ፖለቲካ መብቶች ቃልኪዳን እንዲሁም ሌሎች አግባብነት ያላቸው ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ማዕቀፎች መሠረት ሀገራት የነጻነት፣ አካላዊ ደኅንነት፣ ከጭካኔ እና ኢ-ሰብአዊ አያያዝ የመጠበቅ እና በሕይወት የመኖር መብቶች በመንግሥት አካላት ብቻ ሳይሆን በሦስተኛ ወገኖች ወይም ድርጅቶች ጭምር እንዳይጣሱ በሚገባ መከላከል አለባቸው። ለዚህም አስፈላጊውን የመከላከል እና የጥበቃ እርምጃ ሁሉ መውሰድ የሚገባቸው ሲሆን፣ ጥሰቶች ሲፈጸሙም ተገቢውን ምርመራ በማድረግ የአጥፊዎችን ተጠያቂነት እና የተጎጂዎችን ተገቢውን ፍትሕ የማግኘት መብት ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል። በተጨማሪም፣ በጦርነት ዐውድ ውስጥ የሚፈጸም እገታ በዓለም አቀፍ የሰብአዊነት እንዲሁም የወንጀል ሕግ መሠረት የጦር ወንጀልን ሊያቋቁም የሚችል በመሆኑ፣ መንግሥት ብቻ ሳይሆን የታጠቁ ቡድኖችም ድርጊቱን ከመፈጸም የመታቀብ ዓለም አቀፍ ግዴታ አለባቸው።
በዚህም መሠረት፣ ለችግሩ መፍትሔ ለመስጠት፦
- መንግሥት በጸጥታ አካላቱ አባላት ብቻ ሳይሆን የታጠቁ ቡድኖችን ጨምሮ በ3ኛ ወገኖች ከእገታ ጋር በተያያዘ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ለመከላከል እንዲሁም የአጥፊዎችን ተጠያቂነት እና የተጎጂዎችን ፍትሕ የማግኘት መብት ለማረጋገጥ ውጤታማ እርምጃዎችን እንዲወስድ፤
- በተለይም የፌዴራል እንዲሁም የክልል መንግሥታት ለችግሩ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት በተለይም በተደጋጋሚ እገታ በሚፈጸምባቸው አካባቢዎች እገታን ለመከላከል ውጤታማ የጥበቃና ቁጥጥር ሥራዎችን ከማከናወን በተጨማሪ የታጋቾችን ደኅንነት በጠበቀ መልኩ የማስለቀቅ ሥራዎችን እንዲያጠናክሩ፤
- የታጠቁ ኃይሎች ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕጎችን እንዲሁም የሰብአዊ መብቶች መርሖችንና ድንጋጌዎችን እንዲያከብሩ እና ከእገታ ድርጊቶች እንዲታቀቡ ኢሰመኮ ያሳስባል።
የኢሰመኮ ተጠባባቂ ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ በዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊ እና ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ማዕቀፎች መሠረት ማንኛውም ሰው የተሟላ ነጻነትና ደኅንነት የማግኘት መብት እንዳለው እና ይህንንም ነጻነት በዘፈቀደ ሊነፈግ እንደማይገባ አስታውሰዋል። አክለውም፣ “በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች አሳሳቢ ሆኖ ለቀጠለው የእገታ ተግባር ዘላቂ በሆነ መልኩ እልባት ለመስጠት ለሰዎች እገታ መነሻና አባባሽ ምክንያት የሆነውን የሰላም መደፍረስና የትጥቅ ግጭትን በዘላቂነት በሰላማዊ መንገድ መፍታትን ጨምሮ ውጤታማ እርምጃዎችን መውሰድ ይገባል” ብለዋል።