የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በቴክኒክ እና ሙያ ስልጠና ተቋማት ለሚሠሩ ባለሙያዎች በአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች መብቶች ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ መስከረም 27 እና 28 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ አካሂዷል። መድረኩ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ከጉዳት አልባ አቻዎቻቸው እኩል የትምህርት መብታቸው እንዲጠበቅላቸው፣ የአካቶ ትምህርት ማእከላት በቴክኒክ እና ሙያ ስልጠና ተቋማት ውስጥ እንዲስፋፉ፣ እንዲሁም በዘርፉ የሚታየውን የአመለካከት ክፍተት ለማጥበብ የሚያስችል ግንዛቤ ለመፍጠር ያለመ ነው።


በመድረኩ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ቴክኒክ እና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩትን ጨምሮ በአዲስ አበባ ከሚገኙ ስድስት የመንግሥት የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የተውጣጡ መምህራን፣ ርዕሳነ መምህራን እና ሠራተኞች የተሳተፉ ሲሆን በዋናነት የሰብአዊ መብቶች መሠረታዊ ፅንሰ ሐሳቦች እና የአካል ጉዳተኞች የትምህርት መብትን አስመልክቶ ግንዛቤ ተሰጥቷል።


በተጨማሪም፣ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች በቴክኒክ እና ሙያ ተቋማት ውስጥ የሚጋጥሟቸው ተግዳሮቶች፣ የአካል ጉዳተኞች አካቶ ቴክኒክ እና ሙያ መመሪያ ይዘት፣ እንዲሁም የመፍትሔ ሐሳቦች ቀርበው ከተሳታፊዎች ጋር ውይይት ተደርጓል። ተሳታፊዎቹ አካታች የቴክኒክ እና ሙያ ማኅበረሰብ ለመፍጠር የባለድርሻ አካላትን ሚና ለመለየት የሚያስችል እንዲሁም የትምህርት ቤቶቻቸውን የተደራሽነት ሁኔታ ከቀረበው ገለጻ እና የመመዘኛ መስፈርት አንጻር የመመዘን ተግባራዊ ልምምድ አድርገዋል። በልምምዱ የተለዩ የተደራሽነት ክፍተቶችን ለመፍታት በየተቋማቱ ሊከናወኑ የሚችሉ የተመጣጣኝ ማመቻቸት እርምጃዎችን በዝርዝር የያዘ የድርጊት መርኃ ግብር አዘጋጅተዋል።


የኢሰመኮ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር ጥበቡ ኃይሉ “የቴክኒክ እና ሙያ ስልጠና ተቋማት አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች በኢኮኖሚ ራሳቸውን የመቻል እና የሥራ መብታቸውን ጨምሮ ሌሎችም ሰብአዊ መብቶቻቸው እንዳይሟሉ እንቅፋት ይፈጥራሉ” ብለዋል። አክለውም ክፍተቶቹን ለማስወገድ ሁሉም ባለድርሻዎች የበኩላቸውን እንዲወጡ፣ በተለይም የቴክኒክ እና ሙያ ተቋማት መዋቅራዊ አካታችነታቸውን ለማሳደግ የአካቶ ትምህርት ማእከላትን ማደራጀትን ጨምሮ ሁሉንም አስፈላጊ እርምጃዎች እንዲወስዱ አሳስበዋል።