የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) “የምግብ መብት በኢትዮጵያ፤ የምገባ መርኃ ግብሮች የምግብ መብትን ለማሟላት ያላቸው ሚና እና የሰብአዊ መብቶች ተኮር አቀራረብን መከተላቸው” በሚል ርዕስ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የምገባ መርኃ ግብሮች ላይ ትኩርት በማድረግ ባከናወነው ጥናት ላይ ሚያዝያ 22 ቀን 2016 ዓ.ም. ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።
በውይይት መድረኩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አባላት፣ የሚመለከታቸው የሚኒስቴር እና የአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር መሥሪያ ቤቶች ተወካዮች እንዲሁም የምገባ መርኃ ግብሮቹ አካል የሆኑ የግሉ ዘርፍ ተወካዮች ተሳትፈዋል። ጥናቱ የኢትዮጵያ የሕግ እና የፖሊሲ ማዕቀፎች ከዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ የምግብ መብት ማዕቀፎች ጋር የሚጣጣሙ መሆናቸውን በመዳሰስ እና በአዲስ አበባ ከተማ የሚከናወኑ የትምህርት ቤት እና የተስፋ ብርሃን ማእከላት የምገባ መርኃ ግብሮችን በሰብአዊ መብቶች ተኮር አቀራረብ በመገምገም የተከናወነ ነው፡፡
የምግብ መብትን የተመለከቱ ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ የሰብአዊ መብቶች ማዕቀፎች፣ የጥናቱ ግኝቶች እንዲሁም ምክረ ሐሳቦች በዝግጅቱ ወቅት ለተሳታፊዎች ቀርበዋል። በተመሳሳይ ለጥናቱ ግብአት የሆኑ መረጃዎችን የማሰባሰብ ሥራ ከተጠናቀቀ በኋላ በተፈጠሩ አዳዲስ ጉዳዮች ላይ ከተሳታፊዎች አስተያየቶች ተሰብስቧል፡፡ በተጨማሪም በጥናቱ የተለዩ ክፍተቶች እንዲስተካከሉ እና የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች እንዲተገበሩ መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች ዙሪያ ባለድርሻ አካላቱ ሰፊ ውይይትና ምክክር አድርገዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በጥናቱ የተለዩ ክፍተቶች እና የቀረቡ ምክረ ሐሳቦች የምግብ መብት ትግበራ ችግርና ነባራዊ ሁኔታውን የሚያሳዩ መሆናቸውን ገልጸዋል። አክለውም በኢትዮጵያ የመብቱ ጥሰት መንስኤዎች እንዲቀረፉ ኮሚሽኑ ተጨማሪ ውትወታዎችን እንዲያደረግና በጥናቱ የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች እንዲፈጸሙ በቅርበት እንዲከታተል ጠይቀዋል።
የኢሰመኮ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር ዶ/ር ብራይትማን ገብረሚካኤል በውይይቱ ወቅት ባስተላለፉት መልእክት፤ “ከዐቅማቸው በላይ በሆነ ምክንያት የምግብ ፍላጎታቸውን ማሟላት ለማይችሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች መንግሥት የተለያዩ መርኃ ግብሮችን በሰብአዊ መብቶች ዘዴዎች በመቅረጽና በመተግበር ምግብ የማግኘት መብትን የማረጋገጥ ግዴታውን እንዲወጣ ሌሎች ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዎጽዖ ማድረግ አለባቸው” ብለዋል። አክለውም በመድረኩ የተሰጡ ተጨማሪ ግብአቶችን በማካተት በክትትሉ የቀረቡ ምክረ ሐሳቦች ሙሉ ተፈጻሚነት ለማረጋገጥ የውትወታ ሥራዎች እንደሚቀጥሉ አመላክተዋል።