የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በድኅረ ጦርነት ዐውድ የእናቶች እና የጨቅላ ሕፃናት የጤና መብቶች ሁኔታን አስመልክቶ ከየካቲት 11 እስከ 20 ቀን 2016 ዓ.ም. በአፋር ክልል ባከናወነው ክትትል የተለዩ ግኝቶች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ሰኔ 20 ቀን 2016 ዓ.ም. በሰመራ ከተማ ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱ የጤና ሚኒስቴር እና የአፋር ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊዎችን ጨምሮ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የክልሉ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል። ኢሰመኮ በድኅረ ጦርነት ዐውድ የእናቶች እና የጨቅላ ሕፃናት መብቶችን ሁኔታ በተመለከተ ያደረገው ክትትል የቅድመ ወሊድ፣ የወሊድና የድኅረ ወሊድ ወቅት መሠረታዊ እና አስፈላጊ የጤና አገልግሎቶች መሟላት (availability of essential package of health services) ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።
በውይይቱ ክትትል በተደረገባቸው ዞኖች በተለይም በጤና ተቋማት የተለዩ ግኝቶች እና ምክረ ሐሳቦች የቀረቡ ሲሆን የውይይቱ ተሳታፊዎች ኢሰመኮ በጉዳዩ ላይ የሰብአዊ መብቶች ክትትል ማከናወኑ አበረታች መሆኑን ገልጸው ለክትትል ሪፖርቱ ጠቃሚ ግብአት የሚሆኑ አስተያየቶችን እና ክትትሉ ከተደረገ በኋላ የመጡ መሻሻሎችን ጠቁመዋል።
የኢሰመኮ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ “በአፋር ክልል በድኅረ ጦርነት ዐውድ የእናቶች እና የጨቅላ ሕፃናት ሞትን ለመቀነስ መንግሥት ለአጭር ጊዜ እና ለዘላቂ መፍትሔ የሚሆኑ እርምጃዎችን በመቅረፅ የማስፈጸም ኃላፊነቱን እንዲወጣ፤ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም የእናቶች እና የሕፃናትን ጤና መብቶች ሁኔታን ሊያሻሽሉ የሚችሉ ተጨባጭ እርምጃዎችን ሊወስዱ ይገባል’’ ብለዋል። አክለውም ኢሰመኮ የምክረ ሐሳቦቹን ተፈጻሚነት እንደሚከታተል እና የውትወታ ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።