የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በ2014 ዓ.ም. በጋምቤላ ክልል በሚገኙ 4 ማረሚያ ቤቶች እና 14 ፖሊስ ጣቢያዎች የታራሚዎችን እና የተጠርጣሪዎችን አያያዝና ሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ ላይ ባደረጋቸው የክትትል ሥራዎች በተለዩ ግኝቶች እና በተሰጡ ምክረሃሳቦች ላይ ነሐሴ 11 ቀን 2014 ዓ.ም. ከአራቱም ማረሚያ ቤቶች ከመጡ ኃላፊዎች፣ የእስረኛ አስተዳደር እና ሴት የማረሚያ ቤት ፖሊሶች፣ ከአስራ አራት ፖሊስ ጣቢያዎች ከመጡ የጣቢያ አዛዦች፣ መርማሪ ፖሊሶች እና የሴት ፖሊሶች፣ ከሦስቱ ዞኖች የተውጣጡ የፍትሕ መምሪያ ኃላፊዎች፣ ከክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና የዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ኃላፊዎች እንዲሁም ከፍትሕ ቢሮ ከፍተኛ ኃላፊ ጋር በጋምቤላ ከተማ የውይይት መድረክ አዘጋጅቷል።
በውይይት መድረኩ ላይ በማረሚያ ቤቶች እና ፖሊስ ጣቢያዎች የታራሚዎች እና ተጠርጣሪዎች መረጃ አያያዝ፣ ሕግና ደንብ ማሳወቅ፣ የቀለም ትምህርትና የሙያ ስልጠናዎችን እና ሌሎች አንኳር ጉዳዮችን በተመለከተ በታዩ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች፣ የተለዩ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እና ምክረ ሃሳቦችን ያካተቱ ሁለት የክትትል ሪፖርቶች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በውይይቱ ወቅት በክልሉ በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ ላሉ ታራሚዎች የማረሚያ ቤቱን ሥነ-ሥርዓትና ደንቦች ገለጻ መደረጉ፣ ታራሚዎች ከቤተሰቦቻቸው፣ ጠያቂ ዘመዶቻቸው እና የሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር የመገናኘት መብታቸው መጠበቁ እና የቀለም ትምህርት በማረሚያ ቤቶች ውስጥ መሰጠቱ እንደ ቁልፍ እምርታ የሚታዩ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
በሌላ ጎኑ በሪፖርቱ ከተካተቱ ትኩረት ከሚሹ ክፍተቶች መካከል በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ማረሚያ ቤቶች በኮምፒዩተር ዳታቤዝ የታገዘ የመረጃ አያያዝ አሠራር አለመኖሩ፣ ነባራዊ የኑሮ ሁኔታን ያላገናዘበ አነስተኛ የቀለብ ገንዘብ ለታራሚዎች እና ተጠርጣሪዎች መመደቡ፣ ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት እና የሙያ ስልጠናዎች በማረሚያ ቤቶች ውስጥ አለመሰጠቱ፣ በማረሚያ ቤት ውስጥ ያሉ ክፍሎች በቂ ካለመሆናቸው የተነሳ ታራሚዎች እና ተጠርጣሪዎች በፈርጅ ተለይተው አለመያዛቸው ተጠቃሽ ናቸው። በተጨማሪም በማረሚያ ቤቶች ውስጥ ያለው የሕክምና አገልግሎት አነስተኛ መሆን፣ ታራሚዎች በግል ሕክምና ለማግኘት የማጀቢያ ገንዘብ መጠየቃቸው እና በአንዳንድ ማረሚያ ቤቶች ላይ ኢ-ሰብአዊ የሆነ አያያዝ መኖሩ ካሉት አሳሳቢ ጉዳዮች መካከል መሆናቸውን በሪፖርቱ ውስጥ የተካተተ ሲሆን በውይይት መድረኩ ላይም በስፋት ተነስተዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በቂ የሆነ በጀት አለመኖር፣ የሰው ኃይል እጥረት እንዲሁም አስፈላጊ ቁሳቁሶች እና ሎጅስቲክ አለመሟላት ማረሚያ ቤቶችን እያጋጠመ ካሉ ተግዳሮቶች መካከል መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ በውይይት መድረኩ ላይ በፖሊስ ጣቢያዎች የተጠርጣሪዎች አያያዝና የሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ ረገድ በተሠራው የክትትል ሥራ ግኝቶች ሪፖርት ቀርቧል፡፡ በፖሊስ ጣቢያዎች ላይ ከታዩ ቁልፍ እምርታዎች መካከል ተጠርጣሪዎች ከቤተሰቦቻቸው እና የሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር የመገናኘት መብታቸው መጠበቁ ተጠቃሽ ነው፡፡
በፖሊስ ጣቢያዎች ክትትል ወቅት ከተለዩ ችግሮች እና አሳሳቢ ጉዳዮች መካከል መረጃዎችን በአግባቡ ያለመያዝ፣ በሁሉም ፖሊስ ጣቢያዎች በመንግሥት የሚቀርብ የምግብም ሆነ የሕክምና አገልግሎት አለመኖር እና አብዛኛው ፖሊስ ጣቢያዎች የውኃ አቅርቦት የሌላቸው መሆናቸው ይጠቀሳሉ፡፡ በተጨማሪም በአብዛኛው ፖሊስ ጣቢያዎች ተጠርጣሪዎች በ48 ሰዓት ውስጥ ለፍርድ ቤት አለመቅረባቸው፣ የተራዘመ የቅድመ-ክስ እስር መኖሩ፣ በብርበራ የተወሰዱ የተጠርጣሪዎች ንብረቶች ለግል ጥቅም ማስቀረት/ አለመመለስ፣ የሴት ተጠርጣሪዎች ማቆያ ሙሉ በሙሉ ከወንዶች የተለየ አለመሆን፣ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ወጣት ተጠርጣሪዎች ከሌሎች ተለይተው አለመያዛቸው እና ልዩ ትኩረት/ድጋፍ ለሚሹ ተጠርጣሪዎች የሚደረግ ድጋፍ አለመኖሩ በፖሊስ ጣቢያዎች ውስጥ ያሉ አሳሳቢ ጉዳዮች መሆናቸውን በውይይት መድረኩ ላይ በስፋት ተገልጿል፡፡
በተያያዘ መልኩ በመንግሥት በኩል ለፖሊስ ጣቢያዎች የሚሰጠው ትኩረት እና ድጋፍ አነስተኛ መሆን፣ አንዳንድ የሚታዩት ችግሮች ከጣቢያዎቹ አቅም በላይ መሆናቸውን፣ በሌሎች የመንግሥት አካል የሚደርስባቸው ጣልቃ ገብነት መኖርና የሰው ኃይል፣ የሎጀስቲክ እና መሰረታዊ ቁሳቁሶች እጥረት ፖሊስ ጣቢያዎችን እያጋጠሙ ካሉት ችግሮች መካከል መሆናቸውን ተሳታፊዎች አንስተዋል፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙ የማረሚያ ቤት ኃላፊዎች የጋምቤላ ከተማ ማረሚያ ቤት በ2015 ዓ.ም. አዲስና ዘመናዊ የማደሪያ ቤቶች ግንባታ ስለሚጀመር ይህ በሚጠናቀቅበት ጊዜ አሁን ላይ ያሉት የማደሪያ ቤት እጥረቶች እንደሚቀረፉ ገልጸዋል፡፡ አክለውም ከሦስት እስከ አራት ዓመት ድረስ አፋጣኝ ፍትሕ ሳያገኙ በማረሚያ ቤት የሚቆዩ ተጠርጣሪዎች መኖራቸውን አንስተው ለተጠርጣሪዎች እና ታራሚዎች የሚመደበው የቀለብ ገንዘብ ላይ ማሻሻያ ለማድረግ ፕሮፖዛል ተቀርጾ ለክልሉ መንግሥት ገቢ መደረጉን አመላክተዋል፡፡