የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ እና የማስፋፋት ሥራን ለማጎልበት ትብብር እና ቅንጅት መፍጠር የሚያስችል የመግባቢያ/ስምምነት ከፌዴራል ሕግና ፍትሕ ኢንስቲትዩት (ፌሕፍኢ)፣ ከሴንተር ፎር ጀስቲስ (ሲጄ) (Center for Justice, CJ) እና ከጀስቲስ ፎር ኦል ፒ ኤፍ ኢትዮጰያ (Justice for All – Prison Fellowship Ethiopia, JFA-PFE) ጋር ጥቅምት 25 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ተፈራርሟል። ሰነዶቹን የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ እና የፌዴራል ሕግ እና ፍትሕ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ደግፌ ቡላ፣ የሲጄ ዋና ዳይሬክተር ኩምሳ ጉተታ እንዲሁም የጄስቲስ ፎር ኦል ፒ ኤፍ ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ፓስተር ዳንኤል ገብረስላሴ ፈርመዋል።




ኢሰመኮ ከፌዴራል ሕግ እና ፍትሕ ኢንስቲትዩት ጋር ያደረገው ስምምነት የሰብአዊ መብቶች ዕይታ (Perspectives/ Approach) ወደ ሕግና ፍትሕ ሥርዓተ ትምህርት፣ የስልጠና ፕሮግራሞችና ምርምር ውስጥ እንዲገባ የማረጋገጥ፤ የኤሌክትሮኒክ (E-Learning/digital) እና የገጽ ለገጽ ትምህርት መስጫ ዘዴን በመጠቀም የሰብአዊ መብቶች ትምህርትን ተደራሽ የማድረግ እንዲሁም ጥናትና ምርምር፣ መረጃ የማደራጀት እና ተደራሽነት ሥራዎችን በቅንጅት የመፈጸም ግብ ያለው መሆኑ ተገልጿል።




በሌላ በኩል ለመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች፣ ለማኅበረሰብ መሪዎች፣ ለፀጥታ ዘርፍ ባለሙያዎች እና ለምርጫ አስተባባሪዎች በሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች እና ሰላማዊ የምርጫ ሂደት ላይ የዐቅም ግንባታ ስልጠና ለመስጠት፤ በሠራዊቱ ውስጥ ሀገራዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሕግጋት መከበራቸውን ለማረጋገጥ የወታደራዊ የፍትሕ ሥርዓትን ዐቅም ለማጠናከር፤ የወንጀል ፍትሕ ማሻሻያ በተሟላ ሁኔታ እንዲተገበር ለመደገፍ፣ ሰብአዊ መብቶችን ማዕከል ያደረገ አማራጭ የግጭት አፈታት እና የተሃድሶ ፍትሕ ሥርዓቶችን ለማጎልበት፤ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቶችን በመዘርጋት በማኅበረሰብ መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶችን እና አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት፤ የታራሚዎች ሰብአዊ መብቶች የሚከበሩበት ማረሚያ፣ ማገገሚያ እና መልሶ ማቋቋም ሥራዎችን ለመደገፍ፤ የአካል ጉዳተኞች መብቶች በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚ እና ፖለቲካ ዘርፎች እንዲተገበሩ ለማገዝ፤ የሽግግር ፍትሕ ትግበራን ውጤታማነት የሚያሳድጉ የዐቅም ግንባታ ስልጠናዎችን ለመስጠት እና በአጠቃላይ በሀገሪቱ በሰብአዊ መብቶች፣ በሕግ የበላይነት፣ በመልካም አስተዳደር እና በሠላም ግንባታ ላይ ትኩረት ያደረጉ የጋራ ፕሮጀክቶችን በብቃት ለማከናወን የሚያስፈልጉ የሀብት ማሰባሰብያ ስትራቴጂዎች ላይ ትብብር ለማድረግ ኢሰመኮ ከጀስቲስ ፎር ኦል ፒ ኤፍ ኢትዮጵያ ጋር ተስማምቷል።




በተጨማሪም የታራሚዎች እና የተጠርጣሪዎች ሰብአዊ መብቶችን በተመለከተ ኢሰመኮ ከሲጄ ጋር በተፈራረመው የመግባቢያ ስምምነት የባለድርሻ አካላትን ግንዛቤ ለማሳደግ፣ በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ሥርዓት ውስጥ ለሚያልፉ የመብቶች ጥሰት ተጋላጮች እና ተጠቂዎች የፍትሕ ተደራሽነትን ለማሻሻል፣ ከታሰሩ ቤተሰቦቻቸው ወይም አሳዳጊዎቻቸው ጋር የሚኖሩ ሕፃናትን መብቶች/ጥቅም በሚያስጠብቁ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት፤ አማራጭ የቅጣት ዐይነቶች እንዲተገበሩ ለመወትወት፣ ታራሚዎች በመልካም ሥነምግባር ታንጸው፣ ሕግ አክባሪ፣ ሰላማዊ እና አምራች ዜጋ ሆነው ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ለመደገፍ እና የማረሚያ ቤቶችን ሁኔታ ለማሻሻል የሚያስፈልጉ ተግባራትን በቅንጅት እና በትብብር ለማከናወን ያለመ ነው።

የፌዴራል ሕግ እና ፍትሕ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ደግፌ ቡላ ኢሰመኮ እና የፌሕፍኢ በቅንጅት እና በትብብር ለመሥራት የጋራ ስምምነት መፈረማቸው በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የተደነገጉ እንዲሁም ሀገሪቱ ያጸደቀቻቸውን ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች በስፋት ለማስተማር፤ መብቶቹ ሳይጣሱ እና ሳይሸራረፉ ተግባር ላይ ለማዋል እንዲሁም የዳኝነትና የፍትሕ አካላት ባለሙያዎች እና አመራሮች በዕውቀት፣ በክህሎት፣ በአመለካከት እና በሥነምግባር የታነጹ እንዲሆኑ ለማስቻል ተቋማዊ ዐቅም እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

የጄስቲስ ፎር ኦል ፒ ኤፍ ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ፓስተር ዳንኤል ገብረስላሴ አማራጭ የግጭት አፈታት እና የተሃድሶ ፍትሕ ሥርዓቶችን ለማጎልበት፣የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቶችን ለመዘርጋት፣ የምርጫ ሂደት እና የሽግግር ፍትሕ ትግበራ ላይ በዘርፉ ከሚንቀሳቀሱ መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር የዐቅም ግንባታ ሥራዎችን በትብብር መሥራት በተቋም ደረጃ የተያዙ ግቦችን ለማሳካት ያለውን ፋይዳ አብራርተው ስምምነቱ ለጄስቲስ ፎር ኦል ፒ ኤፍ ኢትዮጵያ ዓላማዎቹን የማስፈጸሚያ ጉልበት እንደሚሆን አመላክተዋል።

የሲጄ ዋና ዳይሬክተር ኩምሳ ጉተታ በበኩላቸው ተቋማቸው የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት እንዲሁም የታራሚዎች እና የተጠርጣሪዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝን ለማሻሻል በሚያከናውኗቸው ተግባራት ላይ ከኢሰመኮ ጋር በትብብር መሥራታቸው በዘርፉ አዎንታዊ ተጽዕኖ መፍጠርና ውጤታማ ሥራዎችን መሥራት እንደሚያስችላቸው አብራርተዋል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ የሰብአዊ መብቶች ሥራ ዘርፈ ብዙ እና የሁሉም ባለድርሻ አካላት ትብብር የሚጠይቅ መሆኑን ጠቁመው፤ ተቋማዊ ነጻነትን እና ገለልተኝነትን ጠብቀው የተዘጋጁ እና የተፈረሙት የጋራ መግባቢያ ሰነዶች በሙሉ ኃላፊነት እንዲተገበሩ ሁሉም የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል። አክለውም ኢሰመኮ በሦስቱ ተቋማት የተፈረሙት የመግባቢያ ሰነዶች የሰብአዊ መብቶች አያያዝንና ጥበቃን በተሻለ መንገድ ለመምራት እና ለመተግበር የሚያግዙ መሆናቸውን ገልጸዋል።