የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የግል የጤና ተቋማት የፋይናንስ ተደራሽነት እና የጤና መብት አተገባበር ዙሪያ ባከናወነው ክትትል ሪፖርት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ግንቦት 10 ቀን 2015 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ የምክክር መድረክ አካሄደ። በመድረኩ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ ከተመረጡ የክልል ጤና ጥበቃ ቢሮዎች፣ ከኢትዮጵያ የምግብና የመድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን፣ ከኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ፣ ከኢትዮጵያ ጤና መድኅን ኤጀንሲ፣ ከተለያዩ የግል ጤና ተቋማት፣ ከመንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና በጤና አገልግሎት ቁጥጥርና አቅርቦት ላይ ከሚሠሩ ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተውጣጡ ተወካዮች ተሳትፈዋል።
በምክክር መድረኩ የግል የጤና ተቋማት የፋይናንስ ተደራሽነት እና የጤና መብትን በሚመለከት በኮሚሽኑ የተደረገው ክትትል ሪፖርት ግኝቶች እና የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች ቀርበዋል፡፡ በዚህም መሠረት የግሉ የጤና ዘርፍ ለጤና አገልግሎት ዋጋ ንረት ያላቸው ሚና፣ በግሉ የጤና ዘርፍ የሚጠየቁ ክፍያዎች መጠን ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ጉዳዮች፣ ግለሰቦች በግል ተቋማት አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስገድዱ ምክንያቶች ለተሳታፊዎች ቀርበዋል። እንዲሁም ለግሉ የጤና ዘርፍ የመንግሥት ድጋፍ፣ የግል የጤና ዘርፍ ቁጥጥር እና ክትትል፣ የፋይናንስ ተደራሽነትን ለማሻሻል የሚረዱ የግል የጤና ዘርፉ ተግባራት፣ የግል የጤና ዘርፉን እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን የሚመለከቱ ጉዳዮችም ተነስተው ከተሳታፊዎች ጋር ውይይት ተደርጓል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም በግል የጤና ዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን እንዴት መቅረፍ እንደሚቻል፣ ኮሚሽኑ በክትትል ሪፖርቱ የለያቸው ምክረ ሐሳቦች ስለሚተገበሩባቸው መንገዶች እና በቀጣይም ከእያንዳንዱ ባለድርሻ አካላት ምን እንደሚጠበቅ ያላቸውን አስተያየት ሰጥተዋል።
የኢሰመኮ የሲቪል፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል በምክክር መድረኩ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፤ የጤና መብት በኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት ከመካተቱም በተጨማሪ ኢትዮጵያ ባጸደቀቻቸው በተለያዩ የዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቃል ኪዳኖች እና ስምምነቶች ዕውቅና ያገኘ መብት መሆኑን አስታውሰዋል። አክለውም መንግሥት እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ይህን መብት በተሟላ መልኩ ተግባራዊ እንዲሆን ለማስቻል መሥራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡ እንዲሁም መድረኩ የተዘጋጀው በክትትል ሪፖርቱ የተገኙትን ግኝቶች እና የተሰጡትን ምክረ ሐሳቦች በመተግበር የግል የጤና ተቋማት ለሕብረተሰቡ በገንዘብ ተደራሽ እንዲሆኑ የሚያስችሉ ሥራዎችን በመሥራት የጤና መብትን በተሻለ ሁኔታ ተግባራዊ እንዲሆን ለማስቻል ያለመ እንደሆነ ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡