1.  አስገድዶ መሰወር ምንድን ነው?

ሰዎችን አስገድዶ መሰወር በርካታ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን የሚያስከትል ሲሆን፣ ስልታዊ እና መጠነ ሰፊ በሆነ መልኩ ሲፈጸም በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸም ዓለም አቀፍ ወንጀልን ያቋቁማል። ሁሉንም ሰዎች ከአስገድዶ መሰወር ለመጠበቅ በተደረገው ዓለም አቀፍ ስምምነት (International Convention for the Protection of All Persons from Enforced Disappearance) መሠረት፣ አስገድዶ መሰወር ማለት “በመንግሥት ወኪሎች ወይም ከመንግሥት ፈቃድ ወይም ድጋፍ በተሰጣቸው ሰዎች ወይም ቡድኖች ወይም በመንግሥት ስምምነት አንድን ሰው በማሰር፣ አፍኖ በመውሰድ፣ ወይም በሌላ በማናቸውም መንገድ ነጻነቱን በማጥፋትና በቁጥጥር ሥር መዋሉን በመካድ፣ በመደበቅ፣ ያለበትን ቦታ ባለማሳወቅ ወይም ደብዛውን በማጥፋት ፈጽሞ ከሕግ ጥበቃ ውጪ እንዲሆን ማድረግ’’ ነው።[1]

በዚህ መሠረት፣ ይህንን ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት የሚያቋቁሙት የሚከተሉት 3 መሠረታዊ አላባዎች (constitutive elements) ናቸው፦

  • ነጻነትን መንፈግ/ማጥፋት፦ በእስር፣ በጠለፋ፣ በእገታ ወይም በሌላ በማናቸውም ዐይነት መንገድ አንድን ሰው  ከፈቃዱ ውጭ ነጻነቱን መንፈግ ወይም ማጥፋት፣
  • የመንግሥት ተሳትፎ፦ መንግሥት በጉዳዩ ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ፈቃድ ወይም ድጋፍ ወይም ስምምነት በመስጠት ተሳታፊ መሆን፣ እና
  • አለመቀበል/መካድ፦ ተገዶ የተሰወረውን ሰው ነጻነት መነፈግ እንዲሁም ያለበትን ቦታ እና ሁኔታ መካድ፣ አለመቀበል ወይም ለማሳወቅ ፈቃደኛ አለመሆን።

የአስገድዶ መሰወር ድርጊት ተጎጂውን ከሕግ ጥበቃ ውጭ የሚያደርገው በመሆኑ ከነጻነቱ እና አካላዊ ደኅንነቱ ባሻገር ሌሎች ሰብአዊ መብቶቹንም በከፍተኛ ሁኔታ አደጋ ላይ የሚጥል ነው። ድርጊቱ በቀጥታ ከሚፈጸምባቸው ሰዎች ባሻገር በተጎጂዎች ቤተሰቦችና የቅርብ ሰዎች እንዲሁም በአጠቃላይ በማኀበረሰቡ ላይ አሳሳቢ የሰብአዊ መብቶች አደጋዎችን ይፈጥራል።

2.  አስገድዶ መሰወር የሚያስከትላቸው የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ወይም ሥጋቶች ምንድን ናቸው?

ማንኛውም ሰው ከአስገድዶ መሰወር የመጠበቅ መብት አለው። ድርጊቱ ቀጣይነት ባለው እና ውስብስብ በሆነ መንገድ በርካታ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ወይም በሕይወት ላይ የሚደርስ አደጋን ጨምሮ ሌሎች ሥጋቶችን ያስከትላል።

በአስገድዶ መሰወር ድርጊት ምክንያት ጥሰት ወይም ሥጋት ከሚደርስባቸው ሰብአዊ መብቶች መካከል፦

  • በሕይወት የመኖር መብት፣
  • የነጻነት መብት፣
  • የአካል ደኅንነት እና ሰብአዊ ክብር፣
  • ከማሰቃየት ወይም ጭካኔ ከተሞላበት፣ ኢ-ሰብአዊ ወይም አዋራጅ ከሆነ አያያዝ ወይም ቅጣት የመጠበቅ መብት፣
  • ከሕገ-ወጥ ወይም የዘፈቀደ እስር ነጻ የመሆን መብት፣
  • በሕግ ፊት እንደሰው የመቆጠር መብት፣
  • ፍትሐዊ የፍርድ ሂደት እና የዳኝነት ዋስትና የማግኘት መብት፣
  • በቤተሰብ የመጠየቅ መብት፣ እና
  • የተጎጂው ቤተሰብ እውነቱን የማወቅ መብት ተጠቃሽ ናቸው።

አስገድዶ መሰወር ድርጊቱ በተፈጸመበት ሰው እና በቤተሰቦቹ ላይ ከሚያደርሳቸው የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ጥሰቶች ባሻገር ሌሎች ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ መብቶችንም አደጋ ላይ ይጥላል። በተለይም የድርጊቱ ሰለባ የሆነው ሰው የመሥራት፣ ገቢ የማግኘት እና ንብረት የማፍራት መብት በከፍተኛ ሁኔታ ስለሚገደብ በራሱም ሆነ በእሱ ድጋፍ በሚተዳደሩ ቤተሰቦቹ የኢኮኖሚ፣ የጤና፣ የትምህርት እና የመሳሰሉት መብቶች ላይ ከፍተኛ አሉታዊ አንድምታ አለው።

3.  ሰዎችን ከአስገድዶ መሰወር ለመጠበቅ የተዘረጉ የሕግ ማዕቀፎች ምንድናቸው? በመንግሥት ላይ የሚጥሏቸው ግዴታዎችስ?

ሰዎችን ከአስገድዶ መሰወር ለመጠበቅ የተለያዩ ዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊና ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ማዕቀፎች አሉ። ሁሉንም ሰዎች ከአስገድዶ መሰወር ለመጠበቅ የወጣው የተ.መ.ድ. መግለጫ[2] (Declaration on the Protection of All Persons from Enforced Disappearance) የአስገድዶ መሰወር ተግባራት በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መግለጫ (Universal Declaration of Human Rights)፣ በሲቪል እና ፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃልኪዳን (International Covenant on Civil and Political Rights) እንዲሁም የማሰቃየት እና ሌሎች የጭካኔ፣ ኢ-ሰብአዊ የሆነና ክብርን የሚያዋርድ አያያዝ ወይም ቅጣት ለማስቀረት የተደረገ ስምምነት (Convention against Torture and Other Cruel, Inhuman or Degrading Treatment or Punishment) ጥበቃ የተደረገላቸውን ሰብአዊ መብቶች የሚጥስ መሆኑን ይገልጻል።[3] መግለጫው ድርጊቱ ስልታዊ በሆነ ሁኔታ ሲፈጸም በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀልን (crime against humanity) እንደሚያቋቁም በማስታወስ፣ ሀገራት የአስገድዶ መሰወር ተግባራትን በከባድ ወንጀልነት የሚፈርጁ ማዕቀፎችን እንዲዘረጉ ያሳስባል። የድርጊቱን መፈጸም ለመከላከልና ለመቅጣት የሚረዱ መመዘኛዎችንም ያስቀምጣል።

ሁሉንም ሰዎች ከአስገድዶ መሰወር ለመጠበቅ የተደረገው ዓለም አቀፍ ስምምነት(International Convention for the Protection of All Persons from Enforced Disappearance) የአስገድዶ መሰወርን ምንነት እና አላባዎች፣ የአባል ሀገራትን ግዴታዎች እንዲሁም የተጎጂዎችን ጥበቃ በተመለከተ ዝርዝር ድንጋጌዎች ይዟል። ስምምነቱ ከአስገድዶ መሰወር የመጠበቅ መብት በምንም ሁኔታ የማይገደብ (non-derogable) ሰብአዊ መብት መሆኑን በመደንገግ፣ አባል ሀገራት ላይ የተለያዩ ግዴታዎችን ይጥላል። ከነዚህም መካከል፦

  • የሕግ እርምጃ (Legislative Measure)አባል ሀገራት አስገድዶ መሰወርን ራሱን የቻለ አንድ የወንጀል ድርጊት አድርገው በሕግ መደንገግ እና ከክብደቱ ጋር ተመጣጣኝነት ያለው ቅጣት ማስቀመጥ፤ እንዲሁም መጠነ ሰፊ እና ስልታዊ የአስገድዶ መሰወር ድርጊት በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል መሆኑን በሕጎቻቸው ዕውቅና መስጠት አለባቸው።
  • ውጤታማ ምርመራ እና ተጠያቂነት፦ በስምምነቱ አንቀጽ 2 በተሰጠው የአስገድዶ መሰወር ትርጓሜ የተጠቀሱት ተግባራት በመንግሥትም ሆነ ያለመንግሥት አካላት ፈቃድ፣ ድጋፍ ወይም ዕውቅና ሲፈጸሙ፣ አባል ሀገራት ተገቢውን ምርመራ ማድረግ አለባቸው። አግባብነት ያላቸው የመንግሥት ተቋማት በማንኛውም ሰው የሚቀርብ የአስገድዶ መሰወር አቤቱታን መቀበል እና ፈጣን፣ ውጤታማ፣ ነጻ እና ገለልተኛ ምርመራ ማከናወን አለባቸው። ጥፋተኞች ተገቢው ክስ ሊመሠረትባቸውና ተመጣጣኝ ቅጣት ሊጣልባቸው የሚገባ ሲሆን፣ አባል ሀገራት የአስገድዶ መሰወር የይርጋ ድንጋጌ ረጅም ጊዜ የሚሰጥ እና ድርጊቱ መፈጸም ካቆመበት ጊዜ ጀምሮ የሚቆጠር እንዲሆን ማድረግ አለባቸው።
  • የመከላከል ተግባራት፦ አባል ሀገራት በሕግ አውጪ፣ ሕግ አስፈጻሚ እና ሕግ ተርጓሚ ተቋሞቻቸው በኩል አስገድዶ መሰወርን ለመከላከል የሚረዱ እርምጃዎችን መውሰድ አለባቸው። በተለይም በተደራጀ ምዝገባ ላይ የተመሠረተ የእስረኞች አያያዝን ማረጋገጥ እንዲሁም ለአስገድዶ መሰወር ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ባሕሪ ያለውን አንድን ሰው የሚገኝበትን ቦታና ሁኔታ ሳይታወቅ በእስር የመያዝ ተግባር (Incommunicado Detention) ማስወገድ ይገባቸዋል።
  • የተጎጂዎችና ቤተሰቦች ጥበቃ፦ አባል ሀገራት አጥፊዎችን በሕግ ከመጠየቅ ባሻገር ተጎጂዎች እና ቤተሰቦቻቸው ላይ የሚደርሱ ጥሰቶችን የማቆም፣ ግልጽ እና አሻሚ ያልሆነ መረጃ የመስጠት፣ ተመጣጣኝ ካሳና መልሶ የማቋቋም እርምጃን ጨምሮ የተሟላ ፍትሕ ለማረጋገጥ የሚያስችሉ እርምጃዎችን መውሰድ አለባቸው።

4.  በኢትዮጵያ ያለው የአስገድዶ መሰወር ሁኔታ እና የሕግ ማዕቀፉ ምን ይመስላል?

ኢትዮጵያ ሁሉንም ሰዎች ከአስገድዶ መሰወር ለመጠበቅ የወጣውን ዓለም አቀፍ ስምምነት አላጸደቀችም። ሆኖም፣ አስገድዶ መሰወር በፌዴራል ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 28 መሠረት የይርጋ ገደብ ከማይጣልባቸው እና በሀገሪቱ ሕግ አውጭም ሆነ በማንኛውም የመንግሥት አካል ውሳኔ በይቅርታ ወይም በምሕረት ሊታለፉ ከማይችሉ ዋና ዋና ዓለም አቀፍ ወንጀሎች መካከል ነው። በተጨማሪም፣ አስገድዶ የመሰወር ድርጊት የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ዓለም ቃልኪዳን፣ የአፍሪካ የሰዎች እና የሕዝቦች መብቶች ቻርተር፣ የማሰቃየት እና ሌሎች የጭካኔ፣ ኢ-ሰብአዊ የሆነና ክብርን የሚያዋርድ አያያዝ ወይም ቅጣት ለማስቀረት የተደረገው ስምምነት እንዲሁም ሌሎች  ኢትዮጵያ ፈርማ የተቀበለቻቸው የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች ድንጋጌዎችን የሚጥስ በመሆኑ በጥብቅ የተከለከለ ነው።  በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ አስገድዶ መሰወር ራሱን ችሎ እንደ ወንጀል የተጠቀሰ ባይሆንም፣ በበርካታ ድንጋጌዎች መሠረት ተጠያቂነትን የሚስከትል ድርጊት ነው።[4]

በኢትዮጵያ በተለያየ ጊዜና ቦታ የአስገድዶ መሰወር ተግባራት በስፋት እንደሚፈጸሙ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በተለያየ ጊዜ ያወጣቸው የሰብአዊ መብቶች ሪፖርቶች[5] እና መግለጫዎች ያረጋግጣሉ። ለምሳሌ የ2015 ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሪፖርት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የአስገድዶ መሰወር ድርጊት ሰለባ የሆኑ ሰዎች ከመኖሪያ ቤታቸው፣ ከሥራ ቦታ ወይም ከመንገድ ላይ የሲቪልና የደንብ ልብስ በለበሱ የመንግሥት ጸጥታና ደኅንነት ሠራተኞች ያለ ፍርድ ቤት የመያዣ ትእዛዝ ተይዘው ከታሰሩ በኋላ ወዳልታወቀ ስፍራ እየተወሰዱ እንዲሰወሩ መደረጋቸውን፣ ከፊሎቹ ከተወሰኑ ቀናት፣ ሳምንታት ወይም ወራት መሰወር በኋላ ሲገኙ በርካቶች በግዳጅ እንደተሰወሩ የቀጠሉ መሆናቸውን ይገልጻል።

ኢሰመኮ የችግሩን ከፍተኛ አሳሳቢነት ከግንዛቤ በማስገባት አስገድዶ መሰወርን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመከላከል ይረዳ ዘንድ ኢትዮጵያ ሁሉንም ሰዎች ከአስገድዶ መሰወር ለመጠበቅ የተደረገውን ዓለም አቀፍ ስምምነት በአስቸኳይ ተቀብላ እንድታጸድቅ ጥሪ ሲያቀርብና ተግባራዊ የሚደረግበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ባለድርሻዎች የሚሳተፉበትን መድረክ ማካሄድን ጨምሮ በርካታ የውትወታ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል።



[1] ሁሉንም ሰዎች ከአስገድዶ መሰወር ለመጠበቅ የተደረገው ዓለም አቀፍ ስምምነት (International Convention for the Protection of All Persons from Enforced Disappearance)፣ አንቀጽ 2

[2] እ.ኤ.አ. ታኅሣሥ 18፣ 1992 የወጣው ይህ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መግለጫ ሀገራት ሰነዱን መፈረምም ሆነ ማጽደቅ ሳይጠበቅባቸው በመመሪያነት ሊገለገሉባቸው የሚችሏቸውን አስገዳጅ ያልሆኑ ድንጋጌዎችን ይዟል።

[3] ለምሳሌ የሰብአዊ መብቶች ኮሚቴ አጠቅላይ ትንታኔ ቁጥር 35 አስገድዶ መሰወር ብዙዎቹን የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን መሠረታዊ መብቶች እና ነጻነቶች የሚጥስ እንደሆነ ይገልጻል።

[4] ለምሳሌ የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 585፣ 586፣ 595፣ 270፣ 423 እና 425

[5] ኢሰመኮ ለ3 ተከታታይ ዓመታት ያወጣቸው የ2014፣ 2015 እና 2016 በጀት ዓመት ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሪፖርቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የአስገድዶ መሰወር ተግባራት መፈጸማቸውን ይገልጻሉ።