የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ አካባቢዎች እየጨመረ የመጣውን የአስገድዶ መሰወር (Enforced Disappearance) እና ተይዘው የሚገኙበት ሁኔታ ሳይታወቅ በእስር ላይ የሚገኙ (Incommunicado Detention) ሰዎችን ጉዳይ ሲከታተል  ቆይቷል።

በተለይም ይህ አሳሳቢ ሁኔታ በተከሰተባቸው የአዲስ አበባ ከተማ፣ የኦሮሚያ ክልል እና የአማራ ክልል ኮሚሽኑ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን መንግሥታዊ ኃላፊዎች በማነጋገር፣ በልዩ ልዩ የተጠርጣሪዎች ማቆያ ቦታዎች በመዘዋወር እና ከቤተሰቦችና ከሌሎች የመረጃ ምንጮች መረጃዎችን ሲያሰባስብ ቆይቷል።

ኢትዮጵያ ገና ያላጸደቀችው ቢሆንም ሁሉንም ሰዎች ከአስገድዶ መሰወር ለመጠበቅ በተደረገው ዓለም አቀፍ ስምምነት (International Convention for the Protection of All Persons from Enforced Disappearance) መሠረት አስገድዶ መሰወር ማለት ‘’በመንግሥት ወኪሎች ወይም ከመንግሥት ፈቃድ ወይም ድጋፍ በተሰጣቸው ሰዎች ወይም ቡድኖች ወይም በመንግሥት ስምምነት አንድን ሰው በማሰር፣ አፍኖ በመውሰድ፣ ወይም በሌላ በማናቸውም መንገድ ነጻነቱን በማጥፋትና፤ በቁጥጥር ስር መዋሉን በመካድ፣ በመደበቅ፣ የአለበትን ቦታ ባለማሳወቅ ወይም ደብዛውን በማጥፋት ፈጽሞ ከሕግ ጥበቃ ውጪ እንዲሆን ማድረግ’’ ነው።

በሌላ በኩል አንድን ሰው የሚገኝበትን ቦታና ሁኔታ ሳይታወቅ በእስር መያዝ (Incommunicado Detention) ማለት በተለይ በከባድ ወንጀል ተጠርጥሯል የተባለን ሰው ለወንጀል ምርመራ በሚል ምክንያት ከቤተሰብ እና ከጠበቃ እንዳይገናኝ አድርጎ በእስር የማቆየትን ተግባር የሚገልጽ ፅንሰ ሐሳብ ሲሆን፤ እነዚህ ሁለቱም ድርጊቶች ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ናቸው።

በተለይ በአስከፊነቱ የሚታወቀው የአስገድዶ መሰወር ተግባርን የሚያቋቁሙት ዋነኛ አላባዎች (Elements of the Crime) ሦስት ዋና ጉዳዮች ሲሆኑ፤ እነዚህም:-

(ሀ) በማናቸውም ዓይነት መንገድ ቢሆን አንድን ሰው ከፈቃዱ ውጪ ነጻነቱን መንፈግ/ማጥፋት፣

(ለ) መንግሥት በጉዳዩ ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ፈቃድ ወይም ድጋፍ ወይም ስምምነት በመስጠት ተሳታፊ መሆን፣ እና

(ሐ) አስገድዶ የተሰወረውን ሰው ያለበትን ቦታ እና ሁኔታ መካድ፣ አለመቀበል ወይም ለማሳወቅ ፈቃደኛ አለመሆን ናቸው።

ኢሰመኮ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ፣ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ከደረሱት አቤቱታዎችና ጥቆማዎች በመነሳት ሲያደርግ በነበረው ክትትል መሠረት በርካታ  የአስገድዶ መሰወርን ድርጊት የሚያቋቁሙ ድርጊቶች መከሰታቸውን አረጋግጧል።

አብዛኛውን ጊዜ የዚህ ድርጊት ሰለባ የሆኑ ሰዎች ከመኖሪያ ቤታቸው፣ ከሥራ ቦታ ወይም ከመንገድ ላይ የሲቪልና የደንብ ልብስ በለበሱ የመንግሥት ጸጥታና ደኅንነት ሠራተኞች ያለ ፍርድ ቤት የመያዣ ትእዛዝ ተይዘው ከታሰሩ በኋላ ወዳልታወቀ ስፍራ እየተወሰዱ  እንዲሰወሩ የተደረጉ ሲሆን፤ ከፊሎቹ ከተወሰኑ ቀናት፣ ሳምንታት ወይም ወራት መሰወር በኃላ የተገኙ መሆናቸው የተገለጸ ቢሆንም፣ ሌሎች  ይህ መግለጫ እስከተሰጠበት ጊዜ ድረስ በግዳጅ እንደተሰወሩ የቀጠሉ ናቸው።

ከእነዚህ ተጎጂዎች መካከል የተወሰኑት ሲያዙ በወንጀል ተጠርጥረው የሚፈለጉ መሆኑ ተነግሯቸው ወደ መደበኛ ፖሊስ ጣቢያ ከተወሰዱ በኋላ የተሰወሩ ሲሆን ከፊሎቹ ደግሞ ምንም ሳይነገራቸው በጸጥታ ኃይሎች ተወስደው የተሰወሩ ናቸው፡፡

ለምሳሌ በአዲስ አበባ ከተማ ከሚያዝያ 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ በማስገደድ ተሰውረው ከነበሩ ሰዎች ውስጥ ከተለያየ የጊዜ መጠን መሰወር በኃላ ወደ ፌዴራል ፖሊስ ጣቢያ ተወስደው የተገኙ ሲኖሩ፣ አስገድደው በተሰወሩበት ወቅት በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ውስጥ ገላን ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኝ የቀድሞው ልዩ ኃይል ካምፕ ውስጥ ተይዘው እንደቆዩ ለመረዳት ተችሏል። በአስገድዶ መሰወሩ ወቅት ተፈጽሟል ስለተባለ ተገቢ ያልሆነ አያያዝ ወይም የማሰቃየት ተግባር ኮሚሽኑ ምርመራውን የቀጠለ ሲሆን የምርመራ ሥራው እንደተጠናቀቀ ትክክለኛው ሁኔታ የሚገለጽ ይሆናል።

በአማራ ክልል በባሕር ዳር እና በደብረ ብርሃን ከተማ የአስገድዶ መሰወር ሰለባዎች የሆኑ ሰዎችን ጉዳይ ኮሚሽኑ ሲከታተል ቆይቶ የነበረ ሲሆን፤ ከነዚህም ውስጥ አንድ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባል ከሠራዊቱ ከድቷል በሚል በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ወረብ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑትን ወላጅ አባቱን ልጅህን አምጣ በሚል ሚያዝያ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. በግዳጅ ተወስደው ተሰውረው ከቆዩ በኋላ ግንቦት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. ተለቀዋል፡፡

አንድ የቀድሞ የሶማሊ ክልል ልዩ ኃይል አባል ታኅሣሥ 6 ቀን 2015 ዓ.ም. ከቀኑ 11፡00 ከቢሮ ተደውሎለት ለሥራ ጉዳይ ወደ ቢሮ እንዲመጣ ተጠርቶ ከሄደ በኋላ በዕለቱ ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት ጅምሮ ስልኩ የተዘጋ ሲሆን፣ ከዚያ ቀን ጀምሮ የት እና ምን ሁኔታ ላይ እንዳለ ለማወቅ አልተቻለም፡፡

በሌላ በኩል ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ቦታዎች ቢያንስ ሰባት ሰዎች የአስገድዶ መሰወር ድርጊት ሰለባ መሆናቸው ለኢሰመኮ አቤቱታ ቀርቦ ክትትል እየተደረገባቸው ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል በምዕራብ ወለጋ ዞን ጎቡ ሰዮ ወረዳ ነዋሪ የሆነ አንድ ሰው ይገኝበታል፡፡ ይህ ግለሰብ ግንቦት 24 ቀን 2014 ዓ.ም. በወረዳው ፖሊስ ከሌሎች ሦስት ጓደኞቹ ጋር ተይዞ ፖሊስ ጣቢያ ከገባ በኋላ ሰኔ 9 ቀን 2014 ዓ.ም. ከሌሎቹ ታሳሪዎች ተለይቶ ነቀምት ከተማ የሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ መዘዋወሩን ለቤተሰብ የተነገረ ቢሆንም ከዚያ ቀን ጀምሮ ያለበትን ቦታ እና ሁኔታ ማወቅ አልተቻለም፡፡

በተመሳሳይ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የምሥራቅ ወለጋ ዞን የኦፌኮ አስተባባሪ የሆነ ሌላ ሰው ጥቅምት 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ከቀኑ 10፡00 ሰዓት አካባቢ ከሚሠራበት መሥሪያ ቤት በመንግሥት የደኅንነት ኃይሎች ተይዞ ነቀምት ከተማ በሚገኘው የጸጥታ ቢሮ ውስጥ ታስሮ ከፍተኛ ድብደባ ደርሶበት እንደነበረና እጁ በሰንሰለት በመታሰሩ ምክንያት ከቤተሰብ የሚሄድለትን ምግብ ተቀብሎ መመገብ ሲያቅተው ሰዎች የተመለከቱት መሆኑን ከመረጃ ምንጮች ማወቅ ተችሏል። ግለሰቡ ከጥቅምት 13 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ሊገኝ አልቻለም።

ከእነዚህ ተጎጂዎች መካከል የተወሰኑት መጀመሪያ ከተመዘገቡበት ፖሊስ ጣቢያ የተወሰዱት ከመደበኛው የተጠርጣሪ እና የእስረኛ የዝውውር ሂደት ውጪ እና በምሽት በመሆኑ ፍለጋቸውን አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡

ቡራዩ ከተማ በተለምዶ አሸዋ ሜዳ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ  በኦሮሚያ ልዩ ኃይል ፖሊሶች ተይዞ በቡራዩ ወረዳ 3 ፖሊስ ጣቢያ በቁጥጥር ስር ውሎ የቆየ አንድ ሰው ከሁለት ወራት የፖሊስ ጣቢያ ቆይታ በኋላ አንድ ቀን ከምሽቱ 4፡00 ሰዓት አካባቢ (ቀኑ በትክክል አልታወቀም) ከሌሎች እስረኞች ተለይቶ  መወሰዱ የታወቀ ቢሆንም ፣ ከዚያን ቀን ጀምሮ ያለበትን ቦታ እና ሁኔታ ማወቅ አልተቻለም፡፡

ሚያዚያ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት ላይ ቁጥራቸው ከሃያ ያላነሱ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት በሰሜን ሸዋ ዞን፣ ሱሉልታ ወረዳ፣ ለገሄጦ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር፣ ልዩ ስሙ ረቡዕ ገበያ፣ 04  ቀበሌ ተብሎ ከሚጠራው ቦታ በመምጣት አንድ ሰው ይዘው የሄዱ ሲሆን፤ በማግስቱ ቤተሰቦቹ ታሳሪውን ለመፈለግ ወታደሮቹ ይኖሩበት ወደነበረው ደርባ ቶኒ፣ አበባ ልማት ካምፕ ቢሄዱም፣ ወታደሮቹ የተያዘው ግለሰብ ያበትን ሁኔታ ሊያሳውቁ ፍቃደኛ አለመሆናቸውን፤ ይልቁንም ለመጠየቅ የሄዱ ሰዎች እስር እና ማስፈራርያ የደረሰባቸው መሆኑን ገልጸዋል።  የተያዘው ግለሰብም እስከ አሁን ድረስ ያለበት ሁኔታ እና ቦታ ማወቅ አልተቻለም፡፡

የአስገድዶ መሰወር ድርጊት እጅግ አስከፊ የሆነ በርካታ የሰብአዊ መብቶች ጥሰትን በተሰወረው ሰውና በቤተሰቦቹ ላይ የሚያስከትል ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ የነጻነት መብት፣ በሕይወት የመኖር መብት፣ ከሚስጥራዊ እስር እና የማሰቃየት ተግባር የመጠበቅ መብት፣ ፍትሕ የማግኘት መብት እንዲሁም የጤና፣ የሥራ፣ የትምህርትና የቤተሰብ መብትን ጨምሮ በርካታ የሰብአዊ መብቶች የሚጥስ ተግባር ነው።

የዚህ ዓይነቱ ጥቃት ሰለባ በሆኑ ሰዎች ላይ በቀጥታ ከሚደርሰው የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በተጨማሪም በቤተሰብ ላይ የደረሰውን ዘርፈ ብዙ ጉዳት፣ የሥነ ልቡና ጉዳት እና ጭንቀት እንዲሁም በአጠቃላይ ማኅበረሰብ በሕግ ሥርዓት ላይ ያለውን እምነት የመሸርሸር አደጋ ኢሰመኮ በቅርበት ተመልክቷል።

በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ እጅግ ውስብስብ የሆነ የጸጥታና ደኅንነት ሥጋት፣ ዘርፈ ብዙ ወንጀሎች፣ በመንግሥትና የሕዝብ አገልጋዮች ላይ በሚፈጸም ጥቃትና ግድያ ፈታኝ የሆነ የወንጀል መከላከልና የአጥፊዎችን ተጠያቂነት የማረጋገጥ ሥራ መኖሩ እንደተጠበቀ ሆኖ ማናቸውም የወንጀል መከላከልና አጥፊዎችን የመቅጣት ሥራ ሙሉ በሙሉ በሕጋዊና ሰብአዊ መብቶችን ባከበረ ሥርዓት ብቻ ሊመራ የሚገባው ነው።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “ይህ አስከፊ የሆነ የአስገድዶ መሰወር ድርጊት በአስቸኳይ እንዲቆም መንግሥት አስፈላጊውን ጊዜያዊ እና ዘለቄታዊ እርምጃዎች ሁሉ እንዲወስድ፣ የተሰወሩ ሰዎች ሁሉ በአስቸኳይ ከእስር እንዲለቀቁ፣ በተሰወሩበት ጊዜ ሁሉ የተፈጸሙ ድርጊቶች ላይ የተሟላ ማጣራት ተደርጎ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ እንዲሁም ችግሩ የደረሰበትን አሳሳቢ ሁኔታ ከግምት በማስገባት  ሀገር አቀፍ ገለልተኛ አጣሪ የሥራ ቡድን በማዋቀር የድርጊቱ ሰለባ የሆኑ ሰዎችን ማፈላለግ እና ፍትሕን ማረጋገጥ ይገባል” በማለት አሳስበዋል።

ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም “መንግሥት የአስገድዶ መሰወር ወንጀል ሰለባ ለሆኑ ሰዎች መፍትሔ መስጠቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ይህንን ወንጀል ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመከላከል ይረዳ ዘንድ፤ ሁሉንም ሰዎች ከአስገድዶ መሰወር ለመጠበቅ የተደረገውን ዓለም አቀፍ ስምምነት (International Convention for the Protection of All Persons from Enforced Disappearance) ኢትዮጵያ በአስቸኳይ ተቀብላ እንድታጸድቅ ጥሪ እናቀርባለን” ብለዋል።