የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በዋና ዋና ተግባራት እና ኃላፊነቶቹ እንዲሁም ትኩረት በሚሹ የሰብአዊ መብቶች ዘርፎች ዙሪያ ሰኔ 22 እና 23 ቀን 2017 ዓ.ም. ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ተቋማት ቋሚ ኮሚቴ አመራሮች እና አባላት ጋር ስልጠናዊ ውይይት አካሂዷል። ስልጠናዊ ውይይቱ ኢሰመኮ ከምክር ቤቱ ጋር ያለውን የሥራ ግንኙነት ለማሳደግ፣ በአዋጅ በተሰጡት ተግባራትና ኃላፊነቶች ላይ ግልጽነት ለመፍጠር፣ እያከናወናቸው የሚገኙ ዋና ዋና ተግባራትን ማስገንዘብ እና ትኩረት በሚሹ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባትን ለመፍጠር ያለመ ነው፡፡ 

በመድረኩ በብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ምንነት፣ በኢሰመኮ የሪፎርም ሥራዎች፣ የትኩረት መስኮች እና ተግዳሮቶች፣ የሰብአዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራ ሥራ፣ ኮሚሽኑ የሚሰጣቸው ምክረ ሐሳቦች አፈጻጸም እንዲሁም በሽግግር ፍትሕ ላይ የኢሰመኮ ሚና እና እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት፣ በኢሰመኮ የተለያዩ የዘርፍ መብቶች የሥራ ክፍሎች እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች እንዲሁም ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን የሚመለከት ገለጻ የቀረበ ሲሆን ኢሰመኮ ሰብአዊ መብቶችን ይበልጥ ለማስፋፋት እና ለማስጠበቅ ውጤታማ ሥራ ማከናወን በሚችልባቸው መንገዶች ላይ ከቋሚ ኮሚቴው አባላት ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡ 

በተጨማሪም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተ.መ.ድ.) የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት (United Nations Human Rights Council – UNHRC) ለኢትዮጵያ የተሰጡ ምክረ ሐሳቦችን ምላሽ መስጠት፣ የስደተኞች፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና የፍልሰተኞች መብቶች፣ በአካል ጉዳተኞች፣ በአረጋውያን፣ በሴቶች እና በሕፃናት መብቶች ላይ ኢሰመኮ በማከናወን ላይ የሚገኙ ሥራዎች፣ ትኩረት የሚፈልጉ የመብት ሁኔታዎች እንዲሁም ከነዚህ አንጻር ምክር ቤቱ እና ኮሚሽኑ አብረው ሊሠሩ በሚችሉባቸው መንገዶች ላይ ውይይቶች ተደርገዋል።

ተሳታፊዎች ስልጠናው ለሰብአዊ መብቶች መስፋፋት፣ መከበር እና ጥበቃ በመናበብና ይበልጥ በመተጋገዝ ለመሥራት የሚያስችል መሆኑን ገልጸው፤ የኢሰመኮ ቁልፍ ተግባራት እና ኃላፊነቶች ላይ ግልጽነት እንዲፈጠር ዕድል የሰጠ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ በተጨማሪም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መሰል ስልጠና እና ውይይቶች እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡ 

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ ኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶችን እና ድንጋጌዎችን በሚመለከት በቂ ግንዛቤ መስጠት እና ባለድርሻ አካላት የሚጠበቀውን አስተዋጽዖ እንዲያበረክቱ፤ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት በመሥራት ጥሰቶች እንዳይፈጸሙ የመከላከል እንዲሁም ሕጋዊ የአሠራር ሥርዓቶችን ተከትሎ በመሥራት የሀገሪቱን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታን ለማሻሻል የበኩሉን ኃላፊነት ይወጣል ብለዋል። የምክረ ሐሳቦችን አፈጻጸም በሚመለከተ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አጣርቶና ተከታትሎ ማስፈጸም እንዲሁም ለኮሚሽኑ ሥራ ግብአት የሚሆኑ አስፈላጊ ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ በበኩላቸው ለሰብአዊ መብቶች መስፋፋት፣ ጥበቃ እና መከበር ውጤታማ ሥራ ለማከናወን እና ሰብአዊ መብቶች ባህል የሆኑባት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የፌዴራል መንግሥቱ ከፍተኛ የሥልጣን አካል ከሆነው ምክር ቤቱ ጋር ተቀራርቦ መሥራት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው ስልጠናዊ የውይይት መድረኩ ከቋሚ ኮሚቴው ብሎም ከምክር ቤቱ ጋር በቀጣይ ይበልጥ አብሮ በመሥራት ተጨባጭ የሰብአዊ መብቶች ስኬቶችን ለማስመዝገብ የሚያስችል የጋራ መግባባት ላይ ለመደረስ ያስቻለ መሆኑን አስረድተዋል።